ምን ይሆን የበላነው ፥ የጠጣነው ፡ ወይስ “በረከተ መርገም” ጭንቅላታችንን ደፈነው? አሁን አንድን ሰው የተወለደበትን አዲስ አበባን ፡ አገርህ አይደለም ፡ ቅም አያቶችህ ፡ ከዛኛው ማዶ ነው የመጡት ስንል ፡ አናፍርም? እውን እግዜር እኛንም ባምሳሉ ይሆን የፈጠረን ? ወይስ ሰርቶ በደንብ ሳይጨርስ እፍ ያለበት ፡ ጪቃ ውጤቶች ነን?
የናንተን እንዴት እንደሆን አላውቅም እንጂ ፡ እኔ የውጭ ዜጋነቴ በቆዳዬ ቀለም ፡ በዓይን ከሩቅ በሚለይበት ፥ እቤት ቀይ ውጥ ወጥ የተሰራ ቀን ፡ ወይም ቡናው በእጣን የታጀበ ቀን ፡ መአዛው (ሽታው) እኔ ላይ ተሳፍሮ ፡ እኔን ባፍንጫ ለይቶ አውጥቶ ፡ ከዚህ ከኛ ጎራ አይደለህም ለማለት በሚያስችልበት አገር ፥ “ሰው” በመሆኔ ብቻ ፡ የመኖር መብት ተጎናጽፌያለሁ።
ጎሳ የማይቆጠርበት ዜግነት ተሰቶኝ ፥ “ጎሳ” የሚል “የአፓርታይድ መለያ’ ያልሰፈረበት ማታወቂያ ይዤ ፥ በሃቅ የሚቆጠር የምርጫ የመብት ድምጽም ተጎናጽፌያለሁ ። ልብ በሉ ይህ ሁሉ ባባዕድ አገር ነው!ግን የአገሬ ሕዝብ ፡ “በድንጋይ ዘመን የወያኔ ሕይወት” ሲሰቃይ ፥ ተማርን የተባልነው ድንጋዮች ፡ ጎሰኝነት እንደ ሃሺሽ ናላችንን አዙሮት ሳይ ፥ ልቤ ይደማል!
ባለፈው እኔ በኋላ ማርሽ መኪናዬን ላቆም ፡ ፍሪቻ አብርቼ የኋላ ማርሽ አስገብቼ እያለሁ ፥ አንዱ ፈጣን አንስ ያለች መኪና የያዘ ፡ ከኋላዬ እንደመጣ ፡ መኪናውን ወደፌት አስገባና ላቆም ያሰብኩበትን ቦታዬን ነጠቀኝ። እኔ ምን እንደምል አስቤ ሳልጨርስ ፥ ነጩ ሽማግሌው ጎረቤቴ ቆሞ ቲያትሩን ያይ ነበርና ፡ ወደመኪናው ሹፌር ተጠግቶ ፡ በሕጉ መሰረት ቅድሚያ ያለኝ ፡ እኔ ስለሆንኩ ፡ ቦታውን እንዲለቅልኝ ነገረው። እኔ ንትርኩን ለመሸሽ ፡ ሌላ ቦታ ፡ መፈለግ እንደምችል ጎረቤተን ወርጄ ፡ ብነግረውም ፡ ጎረቤቴ በፍጹም አይሞከርም አለ። ሹፌሩም ሕጓን ያውቃታልና ፡ ቦታውን ለኔ አስረክቦ ፡ ተፈተለከ። እኔም አንድ ፈረንጅ ፡ እኔን አፍሪካዊውን ደግፎ ፡ ያለአግባብ ያቆመውን ሌላ ፈረንጅ ተቃውሞ ፡ ተከራክሮ ያስረከበኝ ቦታ ላይ ፡ መኪናዬን አቁሜ ፡ ጀነን ብዬ ፡ ባበሻ ደንብ ቁልፌን ጣቴ ላይ እያሽከረከርኩኝ ወረድኩ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ፡ ወሮበሎች ወያኔዎች ስልጣን ይዘው ፡ እንደ ገና ዳቦ ሲቆራርሱን ፡ እኛ እንደሰው ማሰብ አቁመን ፡ እንደ ዳቦ ቁራሽ ፡ በየተራ ለመበላት ተደርድረናል! ይህ ወራዳነታችን ሳያንሰን ፥ የተቆረስንበትን ቦታ ድንበር አርገን ፡ መናጨትም ይዘናል! እረ ምነው ሃኪም ጠፋ!
የዛሬ አራት መቶ ዓመት እንዲህ ነበር ፡ እንዲያ ነበር ፡ ብሎ ነገር! በዛ ላይ ቋንቋ መግባቢያነቱ ቀርቶ ፖለቲካ ሆንዋል! ፓርቲ በቋንቋ! እረ ተው አንት አምላክ ወይ ውረድ ወይ ፍረድ!
አማራ ፡ ኦሮሞ ፥ ትግሬ ፥ ጉራጌ …… ብሎ ነገር! መጀመሪያ “ሰው” ነን ፡ ከዛ ዝቅ ሲል “ኢትዮጵያዊ”!
ከዛ ወደታች ለመዝቀጥ ፡ ስብዓዊነቴ አይፈቅድም!
No comments:
Post a Comment