Wednesday, May 10, 2017

“ ሞት አይቀርም ስም ግን አይቀበርም ! ” – (ይድነቃቸው ከበደ)



“ ሞት አይቀርም ስም ግን አይቀበርም ! ” —
“ጨዋነትን የተላበሰ ሀገሩን ኢትዮጵያንና ልጆችዋን ከልብ የሚወድ፣ አስተያየቱን ሚዛናዊና ማስረጃ ላይ አሰደግፎ የሚሰጥ ጥሩ መምህር አጣን !”

ህይወት እንዲህ ናት ! እርግጥ ነው ለቤተሰብ. ለወዳጅ ዘመድ እንዲህ አይነቱ የሞት መርዶ እጅግ መራር ሐዘን ነው፡፡ እንደው ልብ ያልን እንደሆነ እስኪ አስቡት፣በፖለቲካ አመለካከት ብቻ አንድ ሰው ከእናት ሃገሩ በግዴታ ሕይወቱን ለማትረፍ ተሰዶ፤ከዛሬ ነገ ይሻሻላል በማለት ለስደቱ ምክንያት የሆነው ነገር ተለውጦ ወይም ተሻሽሎ ወደ እናት ሃገሩ ለመመለስ የሚኖረው ጉጉት፣ ምን ይሄ ብቻ የጉጉቱ ተጋሪ የሆኑት ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ፣ለረጅም ጊዜ የራቃቸውን ሰው ለማግኝት ሲማትሩ እንደው በድንገት አይቀሬው ሞት ቢጠራው የሚፈጠረው ቁጭት፣ ሐዘን እና ቂም እንዴት ያለ ይሆን ? ይህንንስ ሊያሽር የሚችል ምን ይሆን ?! እንዲህ ነው ለማት ይከብዳል ! ግን ለጥያቄዎች ሁሉ መልስ አለ፡፡

አሁን ግን !እጅግ በጣም ተወዳጁ መምህር ፈቃደ ሸዋቀና ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።የእኚህ ታለቅ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት መለየት መራር በሆነ ሐዘን በማህበራዊ ድረ ገፅ በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡ የእኚህን ታላቅ ሰው አብዛኛው ሰው መሞታቸውን ሲሰማ “ጨዋነትን የተላበሰ ሀገሩን ኢትዮጵያንና ልጆችዋን ከልብ የሚወድ፣ አስተያየቱን ሚዛናዊና ማስረጃ ላይ አሰደግፎ የሚሰጥ ጥሩ መምህር አጣን !” በማለት ሐዘናቸውን። ገልፀዋል፡፡ ይህ ስለሳቸው የተሰጠው ምስክርነት ፣እሳቸውን በቅርብ እንዲሁም በሩቅ የሚያውቃቸው ሁሉ የሚስማማበት ሃቅ ነው፡፡

እኚህ ምስጉን ሰው ቀደም ብሎ በሃገራቸው ፣በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ የሚታወቁ ናቸው ፡፡ በነበራቸውም ተሳትፎም አንቱታን አትርፈዋል! ይሁን እንጂ የህወሃት/ኢህአዴግ መንግሥት ወደ ስልጣን ሲመጣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካባረራቸው 42 መምህራን መካከል አንዱ እሳቸው ናቸው፡፡ ለመባረራቸው ምክነያት ለሃገር እና ለወገን ይጠቅማል ብለው በነፃነት ማሰባቸው እና እሱን ተከትሎ የመጣው የፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ ነው ፡፡ስለ ሃገር ማሰባቸው እና መቆርቆራቸው ሊያሸልማቸው እና ሊያስመስግናቸው ሲገባ ለስደት ዳረጋቸው፡፡

በስደት ላይ ሆነው ስለሚወዷት ሃገር እና ስለ-ኢትዮጵያዊያን አሁንም ደፋ ቀና ከማላት ወደኋላ ብለው አያቀውቁም፡፡ እዛም ሆነው እንደሚነገርላቸው እኚህ ታለቅ ሰው፣ የኢትዮጵያን ውስብስ የፖለቲካ ችግር፣በሰከነ የፖለቲካ ተሳትፎ መፍትሔ በመፈለግ፣ የደፈረሰው የሃገራችን ታሪክ እርስ በእርስ በመተማመን በወንድማማችነት ስሜት ሁሉም ለሃገሩ ዘብ እንዲቆም ሲጥሩ እንደነበረ አብዛኛወ ሰው ይመሰክርላቸዋል፡፡ አንድ በቅርብ የሚያውቃቸው ሰው “የኢትዮጵያን ትንሳዔ በዚህ ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ለመፈለግ ቀንዲሉን ኣብርቶ እንደኳተነ፣ እነሆ ፈቃደ ሸዋቀናም አመለጠን።” በማለት መራር ሐዘኑን ገልፆአል፡፡

እኔ ብቻ አውቃለው በማለት ሚዛናዊ የሆነን ሃሳብ ወደ ጎን በማድረግ፣ ሁሌም ሌላውን በማዋረድ እራስን አሸናፊ ለማድረግ እሽቅድድም በበዛበት የማህበራዊ ሚዲያ እና ድረ-ገፅ፣እኚህ ታላቅ ሰው የትንሹን የትልቁን ሰው ሃሳብ መዝነው ይጠቅማል ብለው የሚያስቡትን ሃሳብ የሌላውን ክብር ጠብቀው የእሳቸው ሃሳብ ምን እንደሆነ ለመግለፅ ሁሌም እንደደከሙ ነው፡፡ ሆኖም ግን ሌላውን ዝቅ በማድረግ እነሱ ከፍ ያሉ የሚመስላቸው ትንንሾች ለእኚህም ታላቅ ሰው ወደ-ኋላ አላሉም ፡፡ እሳቸው ግን ይህንንም ተቋቁመው በምክንያት እና በእውነት ሃሳባቸውን ይገልፁ ነበር፡፡ከእኔም ጋር በማህበራዊ ድረ-ገፅ (በፌስቡክ) ወዳጆች ስለነበርን ይህን እውነት ለመታዘብ አንዴ ሳይሆን በተደጋጋሚ ለመታዘብ ችያለው፡፡

ብዙ ሰው አቶ ፈቃደ ሸዋቀና ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዋር ተስማሚ ሰው አድርጎ ይቆጥራቸዋል፡፡ አቶ ፈቃደ ያመኑበትን እንደተናገሩ፣ የሚወዷትን ሃገርና የሚሳሱለትን የኢትዮጵያ ህዝብ የተሻለ ደረጃ ለማድረስ ለረጅም ዓመታት እንደደከሙ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ ! ግን እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሥራቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ እናም “ሞት አይቀርም ስም ግን አይቀበርም” ማለት ሌላ።አይደለም ይኸው ነው፤ መምህር ፈቃደ ሸዋቀና በሠሯቸው መልካም ሥራ ሁሌም ይታወሳሉ፡፡ እግዚአብሔር ነብስዎን ይማረው ! ለቤተሰባቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸዉ ፈጣሪ መፅናናትን ይስጥልን ፣አሜን !!! —
(ይድነቃቸው ከበደ)

No comments:

Post a Comment