Tuesday, May 2, 2017

መንግስት በየቦታው የጀመራቸው ፕሮጀክቶች በአብዛኛው በጅምር በመቅረታቸው ሕዝቡን እያማረረ ነው | በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ፕሮጀክቱ የውሃ ሽታ መሆኑ የተለመደ ሆኗል



እንደ ትንሳኤ ሬዲዮ ዘገባ መሰረት በአገር ሃብት ዘረፋ የተሰማራው ሙሰኛው የህወሃት አገዛዝ ለገጽታ ግንባታ ሲል በተለያዩ ክልሎች አስጀምሮአቸው የነበሩት የልማት መሠረቶች በአብዛኛው ገና ከጅምር ላይ እንዳሉ የተቋረጡ አለያም ግማሽ መንገድ ተገፍቶ የቆሙ መሆናቸው ታውቋል።

ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ሳያደርግ የአገርና የመንግሥት ገንዘብ አለአግባብ እንዲባክን ምክንያት እየሆኑ ነው በማለት ህብረተሰቡ ማማረሩን ወደ ተለያዩ ክልሎች ለሥራ የተላኩ ልማታዊ ጋዜጠኞ መዘገባቸውን ከአገዛዙ ሥር ከሚተዳደሩ ሚዲያዎች ዘገባ ለማወቅ ተችሎአል።
በቅርቡ ወደ ኢሉ አባቡር ተልኮ የነበረው የልማታዊ ጋዜጠኞች ቡድን በቡኖ በደሌ ወረዳ ውስጥ የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት ከ9 አመት በፊት ተጀምሮ የነበረው ፕሮጀክት እስከዛሬ ድረስ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን የተዘረጉ የኤሌክትሪክ ገመድ መሸከሚያ ሚሶሶዎችና በየቦታው የቆሙ ትራንስፎርመሮች መወዳደቅ መጀመራቸውን መመልከታቸው ዘግበዋል።
ስለዚህ ፕሮጀክት ለጋዜጠኛው ቡድን አስተያየታቸውን የሰጡ የበደሌ መብራት ሃይል ሃላፊ ፕሮጄክቱን የተረገበው ድርጅት ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተከፈለውና ርክክብ ሳይፈጽም እንደተሰወረ ተናግረዋል።
ሃላፊው ስለዚህ ችግር በወቅቱ ለበላዮቻቸው ሪፖርት አድርገው እስከ ዛሬ ምንም አይነት እርምጃ እንዳልተወሰደም አረጋግጠዋል።
ገንዘቡ ከተበላ ቦኋላ ባክኖ ከቀረው ከዚህ የፕሮጄክት ሥራ በተጨማሪ በዚያው ዞን የመጠጥ ውሃ ለማዳረስ፤ ኪሊኒኮችና ጤና ጣቢያዎችን ለመገንባት እንዲሁም ወረዳዎችን የሚያገናኙ የመኪና መንገዶች ለመሥራት በሚሉ ሰበቦች ብዙ ሚሊዮን የአገር ሃብት በከንቱ ባክኖ ቀርቶአል።
በጣም የሚያሳዝነው በነዚህ አብዛኛው ቦታዎች ላይ ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ቦታው ለልማት ይፈለጋል እየተባለ ከተፈናቅሉ ቦኋላ ልማት የተባለው ነገር በተግባር ሳይታይ በርካታ አመታት እየተቆጠሩ ነው።
በአብዛኛው በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ለልማት ተብለው የሚጀመሩ ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠላቸው ቦኋላ
የውሃ ሽታ ሆነው የሚቀሩ አለያም ደግሞ የተወሰነ አሸዋና ድንጋይ በቦታው ከተጣለና ቁፋሮ ከተካሄደ ቦኋላ እዛው ላይ የሚቀሩ ናቸው።
በደቡብ ክልልም ተመሳሳይ ችግሮች እየተስተዋሉ እንደሆነ በርካታ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የህወሃት ንብረት የሆኑ ሚዲያዎች አልፎ አልፎ እነዚህን እውነታዎች ይፋ በማድረግ ችግሩን በበታች ሃላፊዎች ላይ ለማላከክና ሥርዓቱን ከተጠያቂነት ነጻ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ እየተስተዋለ ነው።
የመንግሥትን ልማታዊነትን ለመስበክና በመላው አገሪቱ እየተስፋፋ ነው የሚሉትን የዕድገትና የብልጽግና ዜና ብቻ በማሰራጨት ህብረተሰቡን ለማዘናጋት ወይም ለማደንዘዝ የተቋቋሙ የህወሃት ሚዲያዎች ህዝባችን እየተማረረባቸው ያለውን እነዚህን ችግሮች በመዘገብ ሥራ ላይ እየተጠመዱ ያሉት መንግሥት ችግሮቹን እንዳወቀና መፍተሄ ለመስጠት እንደሚንቀሳቀስ ባዶ ተስፋ በመስጠት ተቃውሞ እንዳይነሳ ጊዜ ለመግዛት እንደሆነ ሚዲያዎቹን የሚከታተሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ።
በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ከተጀመሩ አመታት ያስቆጠሩና በእንጥልጥል የቀሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፕሮጄክቶች እያሉ ህወሃት ህዝቡን በተስፋ ለመደለል ሲል አሁንም በጠቅላይ ሚንስትሩ ሃይለማሪያም ደሳለኝ አማካይነት የተላያዩ መሰረተ ድንጋዮችን በበርካታ ቦታዎች ማስቀመጥ መቀጠሉ በርካታ ሰዎችን እያነጋገረ ነው።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሚያዚያ 14 ቀን ከጎንደር ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው የጤዳ ከተማ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ መሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በስፍራው ተገኝቶ እንደነበር የገለጹ ምንጮቻችን የአካባቢውን ህብረተሰብ ለማስደሰት በዕለቱ 35 በሬዎች ታርዶ እንደነበርና በስርዓቱ ላይ ቂም የቋጠረው የከተማው ህዝብ ግን ወደ ግብዣው ቦታ ባለመሄድ ድግሳቸውን እንዳሰናከለባቸው አስረድተዋል።
አሁን በጠዳ ከተማ ለጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ የመሠረተ ድንጋይ በተቀመጠበት ቦታ ላይ ቀደም ሲል ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ከአመታት በፊት ቦታው ለልማት ይፈለጋል በሚል ሰበብ ያለምንም ካሳ እንዲፈናቀሉና መሬቱም ያለምንም ጥቅም ለአመታት ከተቀመጠ ቦኋላ ህብረተሰቡ ውስጥ የተፈጠረውን ቅሬታ ለማስታገስ ነው ይህ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠው የሚሉ አሉ።
ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሰሞኑን አደዋ ውስጥ ለፓን አፊሪካ ዩኒቬርሲቲ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ሲያስቀምጥ ባደረገው ንግግር በአደዋ ያስቀመጠው መሠረተ ድንጋይ ከዚህ ቀደም በሌሎች ቦታዎች ተቀምጠው እንደቀሩት መሠረተ ድንጋይ ብቻ ሆኖ እንደማይቀር ቃል በመግባት በሌሎች ቦታዎች የሚደረገው ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ እንደሆነ ማረጋገጫ ሰጥቶአል።

No comments:

Post a Comment