Sunday, May 7, 2017

የጃንሆይ እናት! – ዳዊት ከበደ ወየሳ – አትላንታ | ለተስፋዬ ገ/አብ ‘የጀሚላ እናት’ ምላሽ




ነገሩ ትንሽ ቆየ። እኔ ግን በሆነ አጋጣሚ በቅርቡ ነው ቃለ ምልልሱን የሰማሁት። ተስፋዬ ገብረአብ አዲስ ስላሳተመው – “የጀሚላ እናት” መጽሃፍ፤ ከጋዜጠኛ በፍቃዱ ሞረዳ ጋር አጭር ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር። በትክክል እንዳዳመጥነው ከሆነ፤ “የቀዳማዊ ኃይለስላሴ እናት ስም ጀሚላ ነው፤ አንድ ወገናቸው ስልጤ ጉራጌ ነው – በሌላ ወገን ኦሮሞ ናቸው።” ይለናል። በመቀጠልም፤ “የጀሚላ እናት በአቶ በዛብህ ተጠልፈው ነበር። አቶ በዛብህ ከምኒልክ ጋር በጦርነት ሞቱ። የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ወይም የጀሚላ እናት እልፍኝ ውስጥ፤ በአጼ ምኒልክ ተገደሉ።” የሚሉና ሌሎች ተዘርዝረው የማያልቁ የልብወለድ ነገሮች በመጽሃፉ ውስጥ ማካተቱን በቃለ ምልልሱ ላይ ሰማን።፡ወደ ኋላ በመመለስ ‘በወቅቱ ምላሽ የሰጠ ሰው ይኖር ይሆን?’ በማለት አንዳንድ ድረ ገጾችን ብመለከት፤ በዚህ የተዛባ ታሪክ ምክንያት… “ኢትዮጵያ ሆይ ታሪክ ነጋሪ አጣሽ?” የሚሉ የቁጭት አስተያየቶችን አነበብኩ።
“እንግዲህ ለተስፋዬ ገብረአብ የተዛባ የታሪክ መጽሃፍ እኛ ምላሽ ካልሰጠን፤ እውነት ተዛብታ ልትቀር አይደለምን?” በማለት ይህንን ሃቅ ለመጻፍ ተገደድን። 
እውነቱ በአጭሩ ይሄ ነው። “የቀዳማዊ ኃይለስላሴ እናት… ስማቸው ጀሚላ ሳይሆን የሺእመቤት ይባላል። እናታቸው የታወቁና የተከበሩት ወ/ሮ ወለተ-ጊዮርጊስ ይመሩ ናቸው። ዘራቸውም ከመንዝ እና ከተጉለት ነው። አቶ በዛብህ ከምኒልክ ጋር ጦርነት ያድርጉ እንጂ የተገደሉት ተማርከው እና በህግ ተከራክረው በችሎት ፊት ሞት ተፈርዶባቸው ነው።” ተስፋዬ ገብረአብ እንዳለው ሳይሆን… የቀዳማዊ ኃይለስላሴ እናትም ሆኑ የሳቸውም እናት በምኒልክ ሊገደሉ ቀርቶ፤ እስከሞታቸው መጨረሻ ድረስ ተከብረው የኖሩ፤ የወለዱና የከበዱ፤ በመጨረሻም ገዳም ገብተው… “እማሆይ” ተሰኝተው በጾምና በጸሎት ቀሪ እድሜያቸውን ያሳለፉሰው ናቸው። ይህን ደግሞ በጽሁፍ ብቻ ሳይሆን በመረጃ በየትኛውም መድረክ፤ መሞገት የሚያስችል በቂ ሰነድ አለን። ይህ ጽሁፍ የተዘጋጀውም ስለ“ጀሚላ እናት – የተሳሳተ ታሪክ።” የምላሽ ምላሽ ለመስጠት ሳይሆን፤ በዚህ አጋጣሚ ወደኋላ ተመልሰን ታሪካችንን እንድንቃኝ በማሰብ ነው፤ እንሆ ስለታሪካችን ክብር- ብዕራችንን አነሳን።

የጃንሆይ እናት!


ዳዊት ከበደ ወየሳ – አትላንታ

የሸዋው ንጉስ ሣህለስላሴ – ንጉስ ሣህለስላሴ – ከመጀመሪያ ሚስታቸው ኃይለመለኮትን፣ ተናኘወርቅ እና ራስ ዳርጌን ወለዱ። ከዚህ ቀጥሎ ያለው ታሪክ ከ’ነዚህ የንጉሥ ሣህለስላሴ ልጆች ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው።
አጼ ቴዎድሮስ ወደ ትግራይ ዘምተው፤ ደጃዝማች ውቤን ማርከው በየካቲት 1847 ንጉሠ ነገሥት ተብለው፤ አክሊል ከደፉ በኋላ…
“አንድ አድርጎ አጓዘው፣ የጎጃምን ሰው፤
ውቤን ጫማ አድርገህ፣ ሸዋን ክፈተው። “ተብሎ ተዘፈነ።
በአመቱ አጼ ቴዎድሮስ ወሎ ዘመቱና ጦርነት ሆነ። የወሎ ህዝብ ሃዘን ተቀምጦ እንዲህ ሲል አንጎራጎረ።

“አሁን ምን ያደርጋል፣ የሴት ወየው ባይ፤
ወሎ የመጣው ሞት፣ ሸዋ የለም ወይ?”  ተባለ።

እንደተባለም አልቀረ፤ የአጼ ቴዎድሮስ ጦር ወደ ሸዋ ዘመተ።
ቀጥሎም የሸዋን በር ለመክፈት፤ አጼ ቴዎድሮስ… ግሼን አልፈው፣ መንዝ፣ መንዝን አልፈው ጉርስላሴ ደረሱ። ከዚህ ተነስተው ወደ ደብረብርሃን ሲሻገሩ ግን… አቶ በዛብህ የአጼ ቴዎድሮስን ጦር በብርቱ ተዋጋ። እንደውም በዚሁ ግንባር አቶ በዛብህ ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር ፊት ለፊት ተጋጥሞ፤ በጦር ካሸማቀቃቸው በኋላ ሳይገድላቸው በመቅረቱ፤ በኋላ ላይ አጼ ቴዎድሮስም …ለአቶ በዛብህ ምህረት ያደረጉለት መሆኑን እናስነብባለን።

የሆነ ሆኖ… የሸዋው ንጉሥ (የምኒልክ አባት) ኃይለመለኮት ጦራቸውን ከአንኮበር ይዘው፤ ቶራ መስክ ላይ መሽገው ሳሉ፤ በወቅቱ በነበረው የወባ ወረሽኝ ምክንያት ኃይለመለኮት ጥቅምት 30፣ 1848 ላይ ጦርነት ሳያደርጉ ተሰማ። የምኒልክ አባት መሞት ሲሰማ፤ የንጉሥ ኃይለመለኮት እህት ወይዘሮ ተናኘወርቅ እና ወንድማቸው ራስ ዳርጌ እየተዋጉ አፈገፈጉ። እነአቶ በዛብህ እና እነ ደጃዝማች ገርማሜ… የከሰም በርሃን አቋርጠው በረከት ላይ የጦር ስብሰባ አደረጉ።
 
በዚህ መሃል ደግሞ… አጼ ቴዎድሮስ እንዲህ ሲሉ አዋጅ አስነገሩ፤ “ባለ አባት የሆንክ የአባትህን መሬት እሰጥሃለሁና አባትህን መርቅ፤ አባት የሌለህ (ርስት የሌለህ እንደማለት ነው) አባት የሌለህ… አባትህ እኔ ነኝ ነኝና ደጅ ጥናኝ።” አሉ።
ከአጼ ቴዎድሮስ አዋጅ በኋላ ህዝቡ ለሁለት ተከፈለ። ባላባቱ አጼ ቴዎድሮስን እጅ ለመንሳት ወደ ደብረ ብርሃን ሲሄድ፤ የሸዋ ጦር አዛዦችም ለሁለት ተከፍለው ተከራከሩ። የሟቹ ንጉሥ የኃይለመለኮት ልጅ የሆነው የ12 አመቱ ምኒልክ እጣ-ፈንታም በጦር አበጋዞቹ በነአቶበዛብህ እጅ ወደቀ። በመጨረሻዋ ሰአት ላይ… ምኒልክን ይዘው በረከት በርሃ ወረዱ።

እነደጃዝማች ገርማሜ “ምኒልክን ይዘን ወደ ኦሮሞ አገር እንሂድ። የቴዎድሮስ ጦር እዚያ ድረስ መጥቶ አይወጋንም” ሲሉ፤ አቶ በዛብህ እና ተከታዮቻቸው ግን፤ “የለም። ምኒልክን ለአጼ ቴዎድሮስ አስረክበን፤ እኛ በሰላም እጃችንን እንስጥ።” አሉ።
“ምኒልክን እንጠይቀው” ብለው ቢጠይቁ፤ አጼ ምኒልክ “ወደ ኦሮሞ አገር ውሰዱኝ።” አሉ። ክርክሩ እንደገና ቀጠለ።

“እሱ ገና ልጅ ነው! በራሱ መወሰን አይችልም!” የሚለው የአቶ በዛብህ ወገን እየጨመረ፤ “ይልቅስ በአዋጁ መሰረት እጃችንን ብንሰጥ…” የሚለው ሃሳብ እያየለ መጣ።

ከብዙ ክርክር በኋላ የነአቶ በዛብህ ሃሳብ አብላጫ ድምጽ በማግኘቱ፤ ምኒልክን ጨምሮ የሸዋ መኳንንትን ለአጼ ቴዎድሮስ አሳልፎ በመስጠቱ ላይ ተስማሙ። እንዳሉትም ሆነ።
ይሄን ግዜ የሸዋ ሰው እንዲህ የሚል ቅኔ በታሪክ ብራና ላይ ጻፈ።
“ቁርጡን አወቁና፣ አለመኖርህን፤
በረከት አገቡት፣ ጌታዬ ልጅህን።” (ጌታዬ ያሉት ኃይለመለኮትን ሲሆን፤ በረከትም ሁለት ትርጉም አለው። ‘አንድም በረከት ቦታውን ለመጥቀስ አስመስለው፤ ምኒልክ ልጅህን መታረቂያ በረከት አደረጉት’ በማለት ተቀኙ)

አቶ በዛብህ ብርቱ ተዋጊ የመሆናቸውን ያህል በጭካኔያቸውም ይታወቃሉ። ተቃዋሚዎቻቸውን ያለምንም ምህረት በመግደል የሚያህላቸው የለም። ከላይ እንደገለጽነው ግን… በደብረብርሃኑ ጦርነት ላይ ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር ፊት ለፊት ተያይተው፤ ንጉሡን  ሳይገድሏቸው ቀርተዋል።

በመጨረሻም አቶ በዛብህ አባድክር… ልጅ ምኒልክን ይዘው ለአጼ ቴዎድሮስ በማስረከባቸው ምስጋና ብቻ ሳይሆን ስልጣንም አገኙ። አጼ ቴዎድሮስም የደብረ ብርሃኑን ብርቱ ውጊያ አስታውሰው፤ የአቶ በዛብህንም ተዋጊነት አድንቀው፤ “በዛብህ እኔ እኮ…;  አንተን በዘውድ እንጂ፤ በጀግንነት አልበልጥህም።” ሲሉ አሞኳሿቸው። በመጨረሻ ንጉሥ ኃይለመለኮት ያስተዳድሩ የነበረውን የሸዋ ግዛት በአደራ ሰጥተዋቸው ስንብት ሆነ።

እነደጃዝማች ገርማሜን ጨምሮ የንጉሥ ሳህለስላሴ ልጅ፤ ራስ ዳርጌ ጭምር ከአቶ በዛብህ ጋር ከመሆን ይልቅ፤ ለአጼ ቴዎድሮስ እጃቸውን መስጠት መርጠው፤ እስከመጨረሻው የመቅደላ ሽሽት ድረስ የሸዋን ግዛት ተሰናበቱ። ወጋችንን በአጭር ለመቁረጥ ያህል… ልጅ ምኒልክ እና የሸዋ ባላባቶች በአጼ ቴዎድሮስ ዘንድ በክብር ተያዙ። የደጃዝማችነት ማዕረግም ተሰጣቸው። እድሜያቸው ለአቅመ አዳም ሲደርስ ደግሞ፤ አጼ ቴዎድሮስ አልጣሽ የተባለች ሴት ልጃቸውን ዳሩላቸው።  – 1853።

በዚሁ አመት በ1853 ደግሞ እንዲህ ሆነ። የኃይለመለኮት እናት ወ/ሮ በዛብሽ “የአባቴ አገር መራቤቴ ይሰጠኝ” ብለው አጼ ቴዎድሮስን ደጅ ይጠኑ ጀመር። የኃይለመኮት ሚስት ወ/ሮ ትደነቂያለሽ ደግሞ፤ “ከኃይለመለኮት በኋላ ባል አልፈልግም” ብለው፤ መርከብ ተሳፍረው እየሩሳሌም መንነው፤ መነኮሱ።

ይሄን የሰሙት አጼ ቴዎድሮስ…
“ታዩልኛላቹህ ይሄን ጉድ…
“የእናት ለማኝ፤
የሚስት መናኝ።” ማለታቸው ይነገራል።

የሴቶቹን ነገር ካነሳን ዘንዳ… በዚሁ ሌላ ሴት እናስተዋውቃቹህ። ወለተ-ጊዮርጊስ ይባላሉ። እጅግ የተዋቡ አይነ ግቡ ሴት ናቸው። (ዋናው ታሪክ እዚህ ላይ ይጀምራልና ልብ ይበሉ) ወ/ሮ ወለተ-ጊዮርጊስ… ለንጉሥ ኃይለመለኮት ታናሽ ወንድም፤ ለራስ ዳርጌ አንድ ልጅ ወልደውላቸዋል – ደስታ ይባላል። ራስ ዳርጌ በአጼ ቴዎድሮስ ተግዘው፤ እስር ላይ በነበሩበት ወቅት፤ ሸዋን እንደንጉሥ ሆነው ሲያስተዳድሩ የነበሩት አቶ በዛብህ ከኚህ ቆንጆ ሴት ማሞ የሚባል ሌላ ልጅ ወልደዋል።

ይህም ሆኖ ወ/ሮ ወለተ ጊዮርጊስ ልባቸው እና ፍቅራቸው፤ የመጀመሪያ ልጃቸውን ለወለዱላቸው ለራስ ዳርጌ ነበር። በመሆኑም በቴዎድሮስ እጅ የነበሩትን ባል እና ልጃቸውን ለመጠየቅ  ወደ ጎንደር ጉዞ ጀመሩ – 1853 ዓ.ም.።

ሸዋን አልፈው ወሎ ሲደርሱ ግን የሼኽ አሊ አይን… ወ/ሮ ወለተ-ጊዮርጊስ አረፈ። (ሼኽ አሊ አባጅፋር በወቅቱ የወረ-ኢሉ ባላባት ነበሩ) እናም ወለተጊዮርጊስን ጠልፈው… “ሚስቴ ነሽ” ብለው በግድ አኖሯቸው። በዚህ ወቅት… የሺ’መቤት አሊ ተጸነሰች።

ወ/ሮ ወለተጊዮርጊስ ይመሩ ያለውዴታቸው ከአቶ በዛብህ ማሞን፤ ከአሊ የሺ’መቤትን ወለዱ።

በዚህ መሃል ያለውን ታሪክ አልፈን ወደ መጨረሻው ግድም እንወስዳችኋለን።

በመጨረሻም… በነደጃዝማች ገርማሜ የሃሳብ ምህንድስና ንጉሥ ምኒልክ እና ሌሎች የሸዋ መኳንንት፤ ከአጼ ቴዎድሮስ እስር ቤት… ከመቅደላ ሸሽተው አመለጡ። የምኒልክ ከመቅደላ ማምለጥ ሲሰማ በሁሉም አቅጣጫ ውጥረት ተፈጠረ። ሸዋን ሲያስተዳድሩ የነበሩት  አቶ በዛብህ በጥፋታቸው መጠን ሊደርስባቸው የሚችለውን ቅጣት በማሰብ፤ ለወሎዋ ባላባት ለወ/ሮ ወርቂት… “እጁን አስረሽ” ላኪልኝ የሚል መእክት ላከባት።
አጼ ቴዎድሮስም በበኩላቸው የሸዋ እና የወሎ ሰዎችን ከእስር አስወጥተው እጅና እግራቸውን እየቆረጡ ከገደል ይጨምሯቸው ጀመር። ሞታቸውን ተሰልፈው ከሚጠብቁትም መሃል፤ አንደኛው የንጉሥ ኃይለመለኮት ታናሽ ወንድም፤ የምኒልክ አጎት… ራስ ዳርጌ አንደኛው ነበሩ። የመሞቻ ተራቸው ሲደርስ፤ ወደንጉሡ እንዲህ ብለው ጮኹ።

“ንጉሥ ሆይ! ለዚህ ነበር ምክራችን? ምክራችን እና ህልማችንን ገደል ሊጨመሩት ነው!?” ብለው አምርረው ተናገሩ፤ አጼ ቴዎድሮስ ቁጣቸውን ውጠው፤ ወትሮም ያከብሯቸው የነበሩትን፤ በአንድ ወቅት ከፈረስ ወድቀው ራሳቸውን በሳቱ ግዜ ጥይት ተኩሰው፣ ባሩድ ባፍንጫቸው አስሸትተው ከሞት ያዳኗቸውን ራስ ዳርጌን በሃዘን አደመጧቸው። ራስ ዳርጌም በሲቃ ንግግር “ይስሙኝ ጃንሆይ!” ማለታቸውን ቀጠሉ።

“የ’ንግሊዝ ጦር ወደ መቅደላ እያመራ ነው። በዚህ ጦርነት ብሞት፤ ‘የኢትዮጵያን ነገር አደራ’ ብለውኝ አልነበረምን? እኔ ዛሬ ከዚህ ገደል ገብቼ ብሞት አደራዎ ጭምር አብሮ አይሞትምን? ምነው ምክራችንን ዘነጉ ጃንሆይ?” ሲሏቸው፤ አጼ ቴዎድሮስ በሃዘን እልህ ተውጠው… ለመናገር ሲቃ ተናነቃቸው፤ አንደበታቸው መናገር ቢያቅተው በ’ጃቸው ምልክት ሰጥተው፤ “በቃ ተው!” አሉ። ራስ ዳርጌ እና ከሳቸው ኋላ የነበሩት የሸዋ ሰዎች በሙሉ በዚህ አይነት ህይወታቸው ተረፈ።

በሌላ በኩል ደግሞ… ወሎ ላይ ወ/ሮ ወርቂት እነምኒልክን ተቀበለቻቸው። እነምኒልክን ወደአጼ ቴዎድሮስ አሳልፋ እንዳትሰጥ፤ ልጇን አመዴ አሊን ገድለውባታል። ለአቶ በዛብህም እንዳታልፋቸው ደም ተቃብተዋል። በመጨረሻ መቶ ያህል አጃቢዎች ጨምራ፤ “የሸዋ ሰው አውራህ መጥቷልና ተቀበለው!” ብላ ምኒልክን መርቃ ወደ ሸዋ ሸኘች – ወ/ሮ ወርቂት።

የምኒልክን ወደ ሸዋ መምጣት የሰሙ አብሮ አደጎቻቸው… እነጎበና ዳጨ፤ ሌሎች የኦሮሞ ፈረሰኞችን አሰልፈው ምኒልክን ለመቀበል በደስታ ሲጋልቡ፤ አቶ በዛብህ ግን… ምኒልክን ለመውጋት ጦሩን ያሰናዳ ጀመር።

ነገሩ እየተካረረ መጥቶ ጦርነቱ እንደሚደረግ እውነት ሲሆን፤ እነምኒልክን መንገድ አግኝታ የተቀላቀለችው… ማሚት የተባለችው ሴት፤ ድምጿ እንዲያስተጋባ ከተራራው ጫፍ ላይ ሆና… ለአቶ በዛብህ ወታደሮች እንዲህ ብላ ገጠመችላቸው።
“ማነው ብላቹህ ነው፣ ጦራቹህ መሾሉ፤
ማነው ብላቹህ ነው፣ ካራቹህ መሳሉ፤
ማነው ብላቹህ ነው፣ ጋሻው መወልወሉ፤
የጌታቹህ ልጅ ነው፣ ኧረ በስማም በሉ።” አለች። *የገደል ማሚቶ የሚለው ቃል የመጣውም ይህችው ማሚት የተባለች ሴት ከተራራ ላይ ሆና፤ ድምጿን ከፍ አድርጋ ግጥሟን በዜማ ለእረኞች ስለምታቀብል ነው። (የሷ ታሪክ ብዙ ነው)

አቶ በዛብህ ምኒልክን ከመቀበል ይልቅ፤ ጦሩን ተማምኖ፤ የጌታውን ልጅ ምኒልክን አላስገባም ብሎ አስቸገረ። በዚህን ግዜ ማሚት ሌላም ግጥም አከለች።
“አንተም አደረከኝ፣ የመነኩሴ ፈራጅ፤
የሙት ልጅ ሲቀበል፣ እንዲህ ነው ወይ ወዳጅ።”  ተባለ። እረኞችም ገደል ላይ ሆነው የሰሙትን የማሚት ግጥም አስተጋቡ። የገደል ማሚቶ ግጥሞች ብዙ ናቸው።
“አገር ለምኒልክ፣ እያለ ቆይቶ፤
ሊወጋቸው ሄደ፣ የሰው ነገር ሰምቶ።” ተባለ።

ምኒልክ ወደ ሸዋ ሲገቡ፤ ወደ አባታቸው አገር አንኮበር አልሄዱም። ወደቢሾፍቱ ደቡብ አቅንተው፤ ከአዳው ኦሮሞ የቡታ ቤተሰቦች ዘንድ ሄደው አረፉ። እነጎበና ዳጨና የጦር አበጋዞቻቸው ሆነው፤ ምኒልክ እስከሚነግሱ ድረስ በታማኝነት አገለገሉ። አቶ በዛብህ ግን ለዚህ ታማኝነት ሳይበቁ ቀሩ።

እዚህ ድረስ ይህን ካልን፤ አሁንም ታሪኩን ትንሽ ወደፊት ገፋ አድርገን፤ የነአቶ በዛብህን መጨረሻ እንንገራቹህ። ምኒልክን ወደሸዋ አላስገባም በሚል ብዙ ተዋጉና በመጨረሻ፤ ተሸንፈው “ማሩኝ” ብለው ለምኒልክ እጃቸውን ሰጡ – 1857።

ብዙዎች አቶ በዛብህ እንዲገደል ቢፈልጉም፤ ምኒልክ ግን “በዛብህን የመሰለ ጀግና በሞት አልቀጣውም።” ብለው አንገራገሩ።
“እንዲህ ያለ ክፉና ጨካኝ ሰው ሊገደል ይገባል” ብለው ቢሞግቷቸው…
“አዎ ክፉና ጨካኝ ሰው ነው። ቢሆንም ክፉ ሰው ለክፉ ቀን ይሆናልና በሞት አትቅጡት።” ብለው መለሱ።

ህዝቡ ልጅ ምኒልክን በደስታ ቢቀበልም፤ በበዛብህ ላይ የሞት ፍርድ ስላልሰጡ ውስጥ ውስጡን ማኩረፉ አልቀረም።

እናም የአቶ በዛብህ ነገር ብዙ አወዛገበ። የአቶ በዛብህ የግል ሃብትና ንብረታቸው ሲወረስ፤ ፈረሶቻቸውን እነአባ ድክር፣ እነቡሬን ደጃዝማች ገርማሜ ወሰዷቸው። ደጃዝማች ገርማሜ ደግሞ በአጼ ቴዎድሮስ ትዕዛዝ አንድ እግራቸው ተቆርጦ ነበር። ይህን ያየችው ማሚት ወደ ገደል ሄዳ ድምጿን አስተጋባች።

“እነአባ ድክር፣ እነ ቡሬ ፈረስ እንዴት ይግረማቸው፤
ገርማሜ ባንድ እግሩ፣ ሲኮረኩራቸው።”  አለችና ሃሳቧን በነጻነት ገልጻ፤ የመጨረሻዋን መጀመሪያ በራሷ ላይ አወጀች።

ወደ አቶ በዛብህ ጉዳይ እንመለስ። መኳንንቱም “ይህ ሰው ይመርመርልን” የሚል አቤቱታ በማብዛታቸው፤ በምኒልክ ትዕዛዝ ቤቱ እንዲፈተሽ ሲደረግ፤ ምኒልክን መልሶ ለመጣል ከሌሎች ሰዎች ጋር የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ተገኙ። ሌላም ሌላም ነገር ተጨመረና የአቶ በዛብህ ታስረው፤ ጉዳዩ በህዝብ ችሎት ይታይ ጀመር።
አቶ በዛብህ አባ ድክር ጀግና ቢሆንም፤ ብዙ ጠላት ስላፈራ ሞቱን የሚመኝለት በዛ። በክርክሩ ወቅት አቶ በዛብህን የሚወቅሱ፤ ክፋት እና ጭካኔውን እያነሱ የሚያወግዙ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ከ’ነዚህም መሃል አቶ ሰራዊቱ የሚባለው ሰው አንዱ ነበር። አቶ ሰራዊቱ በአፉ ኃይለኛ ቢሆንም ጦር ሲመጣ ፈሪ ነው። እና አሁንም በክርክሩ ወቅት የበዛብህን ሃጢያት ዘርዝሮ ሲያበቃ፤ መሬቱን በጦር እየደቀደቀ “በዛብህ አንተ ያልሞትክ ማን ይሞታል? ትሞታታለህ።” እያለ ዛተበት።

በዚህ ወቅት አቶ በዛብህ ቀበል አድርገው፤ “ጦርነት የገጠምኳቸው የኦሮሞ፣ የአማራ የእስላም ጀግኖች መጥተው ይፍትርዱብኝ እንጂ፤ አንተማ የመግደያው ጦር ይመም አይመም ስለማታውቅ ልትፈርድብኝ አትችልም።” በማለት አቶ ሰራዊቱ ላይ አሳቁባቸው።

በመጨረሻ ግን አብላጫው ሰው የሞት ፍርዱ እንዲጸና ስለተስማማ፤ የዚያኑ ቀን የሞት ቅጣት ተወሰነበት። እናም የሚገድሉት ሰዎች ጠመንጃቸው ውስጥ ባሩድ ጠቅጥቀው (የድሮ ጥይት) በዛብህን ኢላማ አድርገው ተኩሱበት። እናም ከባሩዱ ብዛት የተነሳ፤ ልብሱ ጭምር በእሳት ተቃጥሎ ሞተ። በዚያን ወቅት…
“አንተም ጨካኝ ነበርክ፣ ጨካኝ አዘዘብህ፤
እንደ ድፎ ዳቦ፤ እሳት ነደደብህ።”  አለች አሉ፤ የገደል ማሚቶ።
“ኦሮሞ አርፈህ ተኛ፣ አውልቀህ ጀባህን፤
አማራውም ተንፍስ፣ አራግፍ ኮርቻህን፤
በ’ሳት አቃጠሉት፣ የሚያባንንህን።” ተባለ።

ከዚህ በኋላ የኛም ወግ ሊያበቃ ነው። እላይ እንደተገለጸው አቶ በዛብህ፤ ከወ/ሮ ወለተ ጊዮርጊስ ማሞ በዛብህን ወልዷል። ማሞ የደጃዝማችነት ማዕረግ አግኝቶ፣ አባ ቀትር ተሰኝቶ እነደጃዝማች ግርማን ወልዶ ከብዶ ኖረ። ማሞ በዛብህ… በእናቱ በወ/ሮ ወለተጊዮርጊስ በኩል የየሺ’መቤት ታላቅ ወንድም መሆኑ ነው።

ራስ ዳርጌ የንጉሥ ሳህለስላሴ ልጅ፤ የኃይለመለኮት ታናሽ ወንድም ናቸው። መቅደላ ላይ ከሞት ከተረፉ በኋላ፤ አጼ ቴዎድሮስ መሞታቸው ሲረጋገጥ መቅደላን ለቀው ወደ ሸዋ መጡ። ብዙዎች “ንጉሥነቱ የሚገባው ለራስ ዳርጌ ነው።” አሉ። ምኒልክም ከዙፋናቸው ተነስተው፤ አጎታቸውን… “ይህ የታላቅ ወንድምህ የንጉሥ ኃይለመለኮት ዙፋን ነው” አሉ።

ራስ ዳርጌ ሳህለስላሴ ግን፤ “እግዚአብሔር የመረጠው አንተን ነው፤ ንጉሥነትም ላንተ ይገባሃል።” አሉት።

ራስ ዳርጌ በዘመናቸው ሁሉ እንደተከበሩ ነው ያለፉት። ሌላው ቀርቶ ምኒልክ ወደ አድዋ ሲዘምቱ፤ “በህይወት ካልተመለስኩ ዙፋኑን ውረስ።” ብለዋቸው ነበር የሄዱት። ሆኖም የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ምኒልክ ከአድዋ ሲመለሱ፤ ዙፋናቸውን ብቻ ሳይሆን የአሁኑን ቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ጭምር በግንብ አሰርተው ጠበቋቸው።

በ’ርግጥም በራስ ዳርጌ ለአጼ ቴዎድሮስ ቃል እንደገቡላቸው፤ ከምኒልክ ጀርባ ሆነው ኢትዮጵያን አንድ ያደረጉ አስተዋይ ሰው ነበሩ። ትላልቆቹ ሰዎች በድንበርና በማይረባ ነገር ተጣልተው አገር የሚበጠብጥ ነገር ሲነሳ፤ ግራና ቀኙን ተቆጥተውና ሁሉን አስታርቀው አንድ አደረጉ። ሌላው ቀርቶ… በአጼ ቴዎድሮስ እስር ቤት በነበሩበት ወቅት ከበዛብህ የተወለደውን ማሞን እንደልጃቸው ተቀበሉት።  ከላይ እንደገለጽነው ሚስታቸው ወ/ሮ ወለተ-ጊዮርጊስ ይመሩ፤ ባላቸውን ለመጠየቅ ወደ ጎንደር ሲሄዱ፤ በወሎው ባላባት ተጠልፈው፤ የሺ’መቤት አሊን መውለዳቸውን እንዳትዘነጉ።

በታሪካችን መጨረሻ ላይ የምናወጋውም ስለየሺ’መቤት አሊ ይሆናል። የሺ’እመቤት ከወሎው የወረ ኢሉ ባላባት ነው የተወለደችው። በታሪኩ መጨረሻ ላይ… ወ/ሮ ወለተ ጊዮርጊስ ይመሩ…ወረኢሉ ላይ በግድ ሚስት ካደረጓቸው ከሼኽ አሊ አምልጠው ወደ ሸዋ ሲሄዱ፤ ሴት ልጃቸውን የሺ’መቤት አሊንም ይዘው ነበር። እናም ከባላቸው ከራስ ዳርጌ እና ከልጃቸው ደጃዝማች ደስታ ጋር ዳግም ሲገናኙ እንደገና ትልቅ ደስታ ሆነ። (በኋላ ላይ ሼኽ አሊ የሰው ሚስት ጠልፈው በመውሰድ ወንጀል ተከሰው ተፈርዶባቸዋል)

ራስ ዳርጌ እና ወ/ሮ ወለተ ጊዮርጊስ ከዚህ ሁሉ ግዜ በኋላ ሌሎች ልጆች ወለዱ። ለ’ነዚህ ልጆች ታላቅ እህት ሆና ያሳደገቻቸው የሺ’መቤት አሊ ናት። በዚህ መሃል የሺ’መቤት እንደ’ናቷ ቆንጆ ሆና አደገች። የወንዶችም አይን አረፈባት። ራስ ዳርጌ ከሌሎች ሴት ልጆቻቸው የበለጠ፤ ከሳቸው ላልተወለደችው የሺ’መቤት አሊ ክብር ሰጡ። ታላቅ እህታቸውን ልዕልት ተናኘወርቅን እንዲህ አሏት።

“ይቺን ቆንጆ ልጅ፤ ለልጅሽ ለመኮንን ልድርለት አስቤያለሁ።” ይሏቸዋል።

ከዚያ በኋላ የሆነውን ነገር በአጭሩ እንግለጽ። ከዚያ በኋላ የሆነው እንዲህ ነው። የልዕልት ተናኘወርቅ ወንድ ልጅ፤ ራስ መኮንን ሚስት ተገኘላቸው። የሺ’እመቤትም ለራስ መኮንን ተዳረች። ልጅም ወለዱ፤ ተፈሪ መኮንንም አሉት። ተፈሪ መኮንን በነገሱ ግዜ ስማቸው፤ ኃይለስላሴ ተሰኝንቶ፤ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በኢትዮጵያ እና በአፍሪቃ ገናና መሪ ሆኑ።

ይህ ያልተበረዘና ያልተከለሰው… የ’ኛና የ’ናንተ፤ ኢትዮጵያውያን ታሪክ ነው – ቸር ያሰንብተን።

አንዳንድ የታሪክ ምርቃት፡ አንዳንድ ግዜ ከዋናው ታሪክ ጋር አብረው ስለማይሄዱ የምንተዋቸው ነገሮች አሉ። ስለአቶ በዛብህ፣ ደጃዝማች ገርማሜ እና ራስ ዳርጌ ብዙ ማለት እየተቻለ፤ ከዋናው መስመር እንዳንወጣ በማለት የተውናቸው ነገሮች አሉ። እነዚህ የተውናቸውን ነገሮች ደግሞ፤ ከአንዳንድ ወዳጆቻችን ጋር መልሰን ስናወራ፤ “ይሄማ መጻፍ ነበረበት” ብለው ያስቆጩናል። ከዋናው ታሪክ ጋር አብረው ስለማይሄዱ ከተውናቸው ነገሮች አንደኛው፤ የደጃዝማች ገርማሜ ጉዳይ ነው። በኋላ ላይ የሸዋ እንደራሴ ነበሩ። ከመቶ ሃምሳ አመት በፊት ገና በወጣትነታቸው፤ ከሸዋ ተነስተው የአሁኗን አዳማ በግብርና ያቀኑ ሰው ናቸው። በ1880 ረሃብ በመጣ ግዜ፤ እህል ከጎተራ እያወጡ ለደሃው እየሰፈሩ ይሰጡ የነበሩ ናቸው። ብልህ እና ነገር አዋቂ በመሆናቸው በአጼ ቴዎድሮስ ዘንድ ታስረው ሳለ፤ “ሊያመልጡ ይችላሉ” በሚል አንድ እግራቸውን ንጉሡ አስቆርጠውባቸው ነበር – ሃምሌ 23፣ 1890 ሞተው ቀጨማ ቅዱስ ላሊበላ ተቀበሩ።  የሳቸውን ትተን የራስ ዳርጌን ነገር እንመርቅ።

ራስ ዳርጌ – በአጼ ቴዎድሮስ ዘንድ የተወደዱ ሰው ነበሩ። አጼው ራስ ዳርጌን አቆላምጠው በመጥራት “የዳሩ” ይሏቸው ነበር። አንድ ቀን ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር ፈረስ ጉግስ ሲጫወቱ፤ የቴዎድሮስ ፈረስ አነቀፈውና ንጉሡን ይዞ ወደቀ። በአካባቢው የነበሩ ሰዎች፤ አጼ ቴዎድሮስ የሞቱ መስሏቸው  በድንጋጤ ሲሸሹ፤ ራስ ዳርጌ ጠመንጃ ወደ መሬት ተኩሰው ባሩዱን በማራገብ፤ ራሳቸውን የሳቱት አጼ ቴዎድሮስን አንገታቸውን አቅንተው ውሃ ያጠጧቸዋል። በዚህ መሃል አጼ ቴዎድሮ ድንገት ነቅተው፤ “ዘራፍ መይሳው!” ብለው ይፎክሩና ቀና ብለው ሲያዩ፤ ራስ ዳርጌን ብቻ በማየታቸው ተደንቀው፤ “የዳሩ ነህ?” ካሉ በኋላ፤ “ድሮም የጨዋ ልጅ ከቁም ነገር ቦታ አይታጣም።” ብለው መርቀዋቸዋል።

የዚያኑ ቀን ማታ፤ ከንጉሡ ጋር እራት እንዲበሉ ቢጠሩ፤ ፈርተው እምቢ በማለታቸው… “አንተ እኮ የነፍሴ ጌታ ነህ። አንተ ያልበላህ ማን ሊበላ ነው?” ብለዋቸው ነበር። እንግዲህ በኋላ ላይ… እንዲህ የሚወዷቸውን ሰው ከገደል ሊጨምሩ ሲሉ፤ “ምነው ጃንሆይ ‘የኢትዮጵያን ነገር አደራ’ ብለውኝ አልነበረምን? እኔ ዛሬ ከዚህ ገደል ገብቼ ብሞት አደራዎ ጭምር አብሮ አይሞትምን?” ቢሏቸው ግዜ፤ አጼ ቴዎድሮስ መናገር እኪያቅታቸው ድረስ ከልብ ማዘናቸውን ከላይ ገልጸናል።
መመረቃችን ካልቀረ ይችንም እንመርቅ። ራስ ዳርጌ ከመቅደላ አምልጠው ሳይሆን፤ ተለቀው ወደ ሸዋ ሲመጡ፤ ንጉሥ ምኒልክ ከዙፋናቸው ተነስተው፤ “አልጋው ለሣህለስላሴ ልጅ ለርስዎ ነው የሚገባው።” ቢሏቸው፤ ራስ ዳርጌ ግን፤ “እውነት ነው። አልጋው የአባቴ ነው። ነገር ግን አባታችን የሰጡት፤ ላንተ አባት ለኃይለመለኮት ነው። አንተ እያለህ የአባትህን ዙፋን አልወርስም” ብለው፤ ለትውልድ የሚቆይ ቁምነገር ሰሩ። የዚህ ታሪክ ባለቤት የሆነችው የሺመቤት አሊ፤ የ’ንጀራ ልጃቸው ብትሆንም፤ ለትልቅ ማዕረግ አበቋት። የዘር ግንድ እና የደረሰባቸውን በደል ሳይቆጥሩ ለእህታቸው ልጅ ለራስ መኮንን ዳሯት። ቀዳማዊ ኃይለስላሴም ተወለዱ። ከአርሲ ጦርነት በኋላም በአርሲ ተሹመው የኦሮሞን ህዝብ በፍቅር ስላስተዳደሩ፤ የተጣላውን ስላስታረቁ… ህዝቡ በስማቸው ትምህርት ቤት አቋቋመላቸው። በኦሮሚያ በተለይም በአርሲ “የነፍጠኛ ቅሪት” ተብሎ ብዙ ቅርስ ሲጠፋ፤ የድንጋይም ጡት በሃውልት መልክ ሲመረቅ፤ የራስ ዳርጌ ትምህርት ቤት ግን በደርግም በኦህዲድም ስሙን ሳይቀይር ዛሬም ድረስ መቆየቱ፤ የራስ ዳርጌን ተወዳጅነት የሚያመለክት ነው።
ነገርን ነገር ያነሳዋልና ወደ ደብረሊባኖስ መሻገሪያ የሆነውን ድልድይ ያሰሩት እሳቸው ነበሩ። ሌላው በስማቸው ያለ ቅርስ መሆኑ ነው። መጋቢት 15፣ 1892 ዓ.ም. ሞተው ደብረ ሊባኖስ ሲቀበሩ፤ እድሜያቸው በስልሳዎቹ መጨረሻ ላይ ነበር። ብዙ ያልተዘመረላቸውን… የራስ ዳርጌን ጉዳይ ወደኋላ መለስ ብለን ስናይ… በ’ርግጥም ገደል ገብተው ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያም እድል አብሯቸው ገደል ይገባ ነበር ያስብላል… ለግዜው ላይ ቢበቃንስ? በሌላ ታሪክ ለመገናኘት ያብቃን።

2 comments:

  1. Thank you for your knowledge of history. Please keep writing when they come up with made-up stories. These made-up stories have destroyed our country. May the Lord bless Ethiopia and bring us peace and unity.

    ReplyDelete
  2. Don't know what to say but thanks for educating us with your rich knowledge and complement too. Haters always are on Ethiopia's neck and its history with their pathetic lies but they will remain ashamed and belittled. Ethiopia shall always shine !

    ReplyDelete