Saturday, May 6, 2017

ከ‹አንበሳው› ምድር የተገኘው አንበሳ ልጅ አሰፋ ጫቦ በክብር አረፈ

    


የጀግና ዕረፍቱም ያስተምራል
ከ‹አንበሳው› ምድር የተገኘው አንበሳ በክብር አረፈ//
ዛሬ እኩሌ ቀን ላይ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ኢትጵያዊያን ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት … ሳይከፋፍላቸው ተሰባስበው በዛሬው 76ኛ የድል በዓል ዕለት አንድ ‹ጋሞ› በክብር አሳርፈዋል፡፡ አጋጣሚውን/ግጥምጥሙን የጀግናው ዕረፍት በዚህ በዓል ዕለት እንዲሆን ፈጣሪ የፈቀደው ጀግንነቱን ሊመሰክርለት ነው ብሎ ‹ማሰብ› ይቻላል፡፡

‹ጋሞ› ማለት በአማርኛ ‹አንበሳ› ነው፡፡ ዛሬ በክብር የሸኘነው የኢትዮጵያ ‹ብርቅ› (ኖረና ሞተ የሚባል ሁሉ አያገኘውምና) ልጅ አሰፋ ጫቦ ደግሞ ‹‹ጋሞነቱና ኢትዮጵያዊነቱ ያልተጋጩበት›› የጋሞ በረከት ጋሞ ነው፤ አንበሳ ነው፡፡ ጋሞው እንኳን ቆሞ ‹‹ በድኑና የሙት መንፈሱ›› ህወኃት/ ኢህአዴግን የሚያርበደብድ ጀግና ነው ( ቀብሩ ከተገኘበት የጋሞ ምድር እንዲፈጸምና ሥጋው ከተፈጠረበት የጋሞ አፈር እንዲቀላቀል የቀረበውን ኃሳብ ህወኃት/ኢህአዴግ አልቀበልም ብሎ አዲስ አበባ እንዲቀበር መደረጉን አስከሬኑ አገር ቤት እንዲያርፍ ከተቋቋመው ኮሚቴ አባላት የተገኘው መረጃ ያመለክታል) ፡፡ ጠንካራ እምነቱ፣ የኢትዮጵያ ፍቅሩና ኢትዮጵያዊ መንፈሱ እርሱ ባይለውም እኔ የምላቸው ‹ጠላቶቹን› የሚያርበደብድና እንቅልፍ የሚነሳ ፣ ወዳጆቹንና በኢትዮጵያዊነታቸው ጥያቄ ለሌለባቸው ሁሉ የጽናት ሥንቅ ፣ የማንነትና ኢትዮጵያዊነት ጥምረት በረከት ነው፡፡ ጋሼ አሰፋ በህይወት ዘመኑ በጻፋቸው ሲመግበን የኖረውን ዛሬም ‹አስከሬኑን› ከበን ባደመጥነው የህይወት ታሪኩ ( ወዳጁ አቶ ዘገዬ ሞላ ከተለመደው የህይወት ታሪክ አቀራረብ በተለየ መንገድ በቤተሰቦቹ የተዘጋጀውን መልዕክት ሳግ እየተናነቀው በትረካ መልክ ያስደመጠን ) ‹ እውነትም ይህ ‹ጀግና › በዕረፍቱም ስለ ሰብዐዊነት/የሰው ልጅ እና ኢትዮጵያዊነት ይተርካል፣ ሁላችንም ሄደን ፣ሄደን በአዳምና ሄዋን ልጆች አንድ ስለመሆናችን፣ ልዩነቱ ከዚያ ወዲህ/በኋላ የመጣ መሆኑን ያስተምራል፤› አስብሎናል፡፡ ጋሼ አሴ ካንተ ብዙ ተምረናል፤ ባንተ ገና ብዙ እንማራለንና ‹ ብታልፍም › በመንፈስህ . በአስተምሮህና በተሞክሮህ በተውካቸው በረከቶች ሁሌም አብረሄን ትኖራለህ፣ በጽናትህ ታሪክህን አጽንተሃልና ፤ በዚህ እንጽናናለን ፡፡
የአንዱ አሰፋ ‹ቃል/ሃሳብ› አገዛዞችን (ደርግ፣ ህወኃት) ከባታሊዮን ጦር በላይ እንደሚያስፈራ ከእናቱ እቅፍ ከተለየ/ከወረደ በኋላ በምድር ካሳለፈው ዕድሜ ግማሹን (35 + ዓመት – በደርግ እስር ቤትና ህወኃት አሳዶት በስደት) ከሚወዳት አገሩ ተነጥሎ እንዲኖር መሆኑ የሚያረጋግጠው ይህንኑ ነው፡፡ ህወኃት/ ኢህአዴግ ሆይ ለአገራቸውና ወገናቸው ይጠቅማል የሚሉት ካንተ የተለዩ ባለኃሳብ ‹ ጀግኖቻችንን › አሰቃይተህ ( እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ ፣ በቀለ ገርባ ፣ መረራ ጉድና፣ አበበበ ቀስቶ፣ . . .) አሳደህ፣ አሰድደህ ፣አስከሬናቸውን ለማወራረጃነት (ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ጄ/ል ዋቆ ጉቱ፣. . .) ማስረከቡን፤ ሥጋቸውንም ማሰደድ ( የመኢሶኑ ሙሌ፣ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ተስፋዬ ለማ . . .) ትተህ ከነሃሳባቸው በአገራቸው ምድር ፣በህዝባቸው መሃል በነጻነት እንዲኖሩ ስለማድረግ ፣እንደልደታ ንፍሮ የተበተኑትን ወደ አገራቸውና ህዝባቸው እንዲመለሱ ማሰብ ይጠቅምሃልና አስብበት፡፡ ይቅርና ለነጻነትና ክብራቸው የሚታገሉ፣ አገሬን ሲሉ ሥጋቸው በሰው አገር / በስደት የቀረ ኢትዮጵያዊያን ነጻነታችንና ክብራችን ሲመለስ፣ የአገራችን ባለቤት ስንሆን ለአገራቸው መሬት ይበቃሉና፣ ይህም ሩቅ ባለመሆኑ በዚህም እንጽናናለን፡፡
‹‹ ጋሞ ሃይቀና፣›› አንበሳ አይሞትም እንዲሉ ሆኖ ጋሼ አሴም አብሮን ይኖራል፣ ባመነውና በኢትዮጵያዊነቱ ጸንቶ፣ ለአገሬ ይበጃል ብሎ ያመነውን ማንንም ሣይፈራ፣ሳይሰስትና በሆዱ ሳያስቀር በግንባርና፣አደባባይ ተናግሮና ጽፎ፣ በወደደውና በፈቀደው መንገድ ኖሮ፣ ጥላቻንና ጠባብነት ተዋግቶ፣ መቻቻልና አንድነትን ሲያስተምር ደክሞት ‹‹ አረፈ›› እንጂ አልሞተም፤ ጀግና አይሞትምና ፡፡ በጋሼ አሰፋ ትዕዛዝ መሰረት ( ካገለገለበት የጨንቻ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ግቢ ባለማረፉ ብንቆጭም ) በጋሞ ባህልና ወግ መሰረት ‹ጨፍረን› ፣ባደገበት የቤተክህነት ህግ መሰረት በዝማሬና ውዳሴ <አሳረፍነው> እንጂ አልቀበርነውምና ከእርሱ የተገኘው በረከት አብሮን ይዘልቃል፡፡
እንግዲህ ጋሼ አሰፋ የሁላችን ነውና ከልጆቹና መንድምና ቤተሰቦቹ በቀር ማናችን ማንን ‹ታሳ› እንደምንል አላውቅም፡፡ ‹ታሳ› ማለት ከጋሞኛ ወደ አማርኛ ሲመለስ ‹እኔን/በእኔ-የእኔ – ይሁን › ማለት ነው፡፡
ከጋሼ አሰፋ ቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ያገኘኋቸውን በረከቶች በተከታታይ ይዤ እቀርባለሁ፡፡
እስከዚያው በቸር ያገናኘን፡፡ 27/08/09.

No comments:

Post a Comment