የጉዳያችን ማስታወሻ
ዶ/ር ማርጋሬት ቻን ተሰናባቹ የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለዓለም ጤና ድርጅት ከፍተኛ የስራ ኃላፊነት ከቀሩት ሶስት ግለሰቦች ውስጥ አንዱ እጩ መሆናቸው እና የመጨረሻ ድምፅ የመስጠቱ ስነ-ስርዓት ማክሰኞ ግንቦት 15፣2009 ዓም ድምፅ እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል። ዛሬ ሰኞ ማለዳ በስዊዘርላንድ ዋና ከተማ ጄኔቭ በተሰናባቿ የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ማርጋሬት ቻን (Dr Margaret Chan) ለቀጣይ ሰባት ቀናት በሚቆየው የድርጅቱ 70ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት ተሰብሳቢዎቹ ኢ-ፍትሃዊ እኩልነት በተቻለ መጠን እንዲቀንስ አበክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል። “ፍትሃዊ እኩልነት ላይ ትኩረት መደረግ አለበት ስል ደግሞ” አሉ ወይዘሮዋ ዶክተር ቀጠሉና ” የዓለም ጤና ድርጅት የስነ ምግባር መመርያ መርህ ´የዓለም ጤና ድርጅት ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ፀንቶ ይቆማል´ የሚለውን አንቀፅ በማስታወስ ነው ” አሉ። ከእዚህ ጋርም አያይዘው ድርጅቱ ለምርምር ትኩረት እይዲያደርግ እና ከመንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር የሚደረገው ግንኙነት መጠናከር እንዳለበት ይህም የሲቪሉን ማኅበረሰብ ለማዳመጥ እንደሚረዳ እና የሲቪሉ ማኅበረሰብ መንግስትን እና እንደ ሲጋራ፣የምግብ እና አልኮል ፋብሪካዎች ሕብረተሰቡን የሚጎዳ ተግባራት ሲሰሩ አደብ የሚያስይዛቸው መሆኑን ጠቁመዋል።ከእዚሁ ጋር ተያይዞም የድርጅቱ ተሰናባች ዳይሬክተር ንግግር እንደጀመሩ ከአዳራሹ የጋዜጠኞች መቀመጫ ሰገነት ላይ ዶ/ር ቴዎድሮስን የሚቃወም ድምፅ ከአክቲቪስት ዘላለም ተሰማ ተሰምቷል።ዘላለም ከ190 በላይ የሀገር ተወካዮች ፊት ባሰማው ድምፅ ” ቴዎድሮስ ለፕሬዝዳንትነት አይሆንም! አፍሪካ ደግማ ታስብበት!” የሚል ድምፅ በእንግሊዝኛ አሰምቷል።የአክትቪስቱ ተቃውሞ በደቂቃዎች ውስጥ በዓለም ዙርያ በማኅበራዊ ሚድያ ተሰራጭቷል።
በድርጅቱ የዛሬ ውሎ ማብቂያ ላይ ማክሰኞ እለት የድርጅቱ ፕሬዝዳንትን ለመወሰን ምርጫ እንደሚደረግ እና ምርጫው ላይ አንድ ሀገር አንድ ሰው ብቻ እንዲወክል በድርጅቱ ህንፃ ሌላኛው ክፍል ላይ ነገ እንዲገናኙ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
በሰሞኑ የዶ/ር ቴዎድሮስ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት መወዳደር በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ዓቢይ የፖለቲካ መከራከሪያ ሆኖ ቀርቧል።መመረጥ አለባቸው ብለው የሚከራከሩት መሰረት የሚያደርጉት የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ስለነበሩ በድርጅት ፍቅር የተጠመዱ፣ ሁለተኛዎቹ ከድርጅት ፍቅር በላይ የትግራይ ብሄርተኝነት አይሎባቸው ” የእኛ አካባቢ ነው” ከሚል ብቻ የሚደግፉ እና ሶስተኛዎቹ ሌላ ቦታውን ከሚይዘው ኢትዮጵያዊ ሰው ቢሆንበት ይሻላል የሚሉ ናቸው።
በተቃዋሚዎች በኩል ደግሞ ደጋግሞ የሚነገረው ዶ/ር ቴዎድሮስን የምንቃወመው ትግራይ ስለሆነ እና ስላልሆነ አይደለም የምትለው አረፍተ ነገር ቀዳሚ ስትሆን፣ ከእዚህ በተለየ ግን ዶ/ር ቴዎድሮስ የአንድ አካባቢ ፍላጎት እና ነፃነት አስከብራለሁ የሚለው ሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው አብረው በወሰኗቸው ውሳኔዎች የበርካታ ግድያዎች፣እስሮች እና ሰቆቃዎች ተባባሪ ናቸው።በሌላ በኩል በዐማራ ክልል በተሰጠ የወሊድ መቆጣጠርያ እንክብል እና ክትባት ሳቢያ ከሁለት ሚልዮን በላይ ዜጎች እንዳይወለዱ አስደርገዋል።በሌላ በኩል በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፉ ግሎባል ፈንድ ውስጥ የገንዘብ ቅሌት ውስጥ እጃቸው አለበት የሚሉ እና በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው የኮሌራ በሽታ እንዲደበቅ አድርገዋል የሚሉ ይገኙባቸዋል።በተለይ የኮሌራ በሽታ መደበቅ ጉዳይ ላይ የኒው ዮርክ ታይምስ እና ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጦችም ባለፈው ሳምንት በሰፊው የፃፉበት ጉዳይ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ሌላው ሊተኮርበት የሚገባው ጉዳይ ዶ/ር ቴዎድሮስ ዓለም ዓቀፋዊ አስተሳሰብ የሚያላብሳቸው ምን ጉዳይ አለ? ብለን ብንጠይቅ ያለፈ ታሪካቸው በአንድ ክልል ነፃነት ቆምያለሁ የሚለው ስሙንም እስካሁኗ ሰዓት ድረስ የትግራይ ነፃ አውጪ ብሎ የሚጠራው ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንደነበሩ እና በእዚሁ መስመር ብቻ የውጭ ጉዳይነቱንም ሆነ የጤና ሚኒስትርነቱን ቦታ ይዘው እንደነበር የሚታወቅ ነው።ስለሆነም አንድ ሰው ብሔራዊ ሳይሆን በአንድ ክልል ነፃነት በቆመ ድርጅት አስተሳሰብ ታንፆ እንዴት ዓለም ዓቀፋዊ አስተሳሰብ ሊዳብር ይችላል? ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ ሁሉን እኩል አድርጎ የማየት ክህሎት እንጂ የትግራይ ነፃ አውጪ ነኝ በሚል ድርጅት ግንብ ውስጥ መታጠር አይረዳም።ስለሆነም ዶ/ር ቴዎድሮስ ዓለም አቀፋዊ አስተሳሰብ ለማዳበር ከአንድ በዘር ላይ ከተመሰረተ ድርጅት አስተሳሰብ እራሳቸውን ማላቀቅ አስፈላጊ ነው።
በመጨረሻም ዶ/ር ቴዎድሮስ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተርነት ቢመረጡ ለሕወሐት ይዞ የሚመጣው እራሱን የቻለ አደጋ አለው።ብዙዎች የስርዓቱ ደጋፊዎች ሕወሓት አንዱ ባለሥልጣኑ ለከፍተኛ የዓለም ድርጅት መሪነት መመረጣቸው የስነ – ልቦና እርካታ እንደሚያገኙ የሚያስቡ አሉ።ሆኖም ግን ውጤቱ የተቃራኒው ነው የሚሆነው።የዶ/ር ቴዎድሮስ መመረጥ ሕወሓት ማን ነው? ምን ያህል ሕዝብ በድርጅቱ ውሳኔ ተገድሏል? ድርጅቱ ለአንድ ጎሳ የቆመ መሆኑን እራሱ ከስሙ ጀምሮ እንደሚተርክ፣ እና የመሳሰሉት ሁሉ ለዓለም የበለጠ ግልጥ ይሆናል። ይሄውም ዶር ቴዎድሮስ ከተመረጡም በኃላ የኢትዮጵያውያን ተቃውሞ እንደማይቆም ግልጥ ነው።
አንድ የዓለም አቀፍ ድርጅት ፕሬዝዳንት በተንቀሳቀሰ ቁጥር ተቃውሞ የሚገጥመው ከሆነ ዓለም አቀፍ ሚድያዎችን ትኩረት በእጅጉ ይስባል።ተቃውሞ ማድረግ ደግሞ አንድ ግለሰም ምንም ያህል ዲፕሎማሲያዊ ከለላ ቢኖረውም የማንም ሰው መብት ነው። ይህ ማለት ኮንጎ ውስጥ ያለ ገጠር መንደር ውስጥ ያለች እናት ሕወሓት ማን ነው ? ትላለች ማለት ነው።ብራዚል ውስጥ ያሉ ወጣቶች ተቃውሞው እና ዶ/ር ቴዎድሮስ የመጡበትን ድርጅት ሕወሓት በአፍሪካ አደገኛ የሰብዓዊ መብት የጣሰ ድርጅት መሆኑ የበለጠ የታወቀ ይሆናል።የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር በእየሄዱበት ተቃውሞ የሚገጥማቸው ብቸኛ ሰው ይሆናሉ ማለት ነው።በመሆኑም ሕወሓት በዶ/ር ቴዎድሮስ መመረጥ የበለጠ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የተጋለጠ ይሆናል።ይህ ሁኔታም ዶ/ር ቴዎድሮስ ከተመረጡ የስራ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ስራቸውን ለመልቀቅ ሊያስገድዳቸው ይችላል።አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ያሰበው እና ሰው ያሰበው መለያየቱ እና እግዚአብሔር የበለጠ ሊሰራ ሲፈልግ እንዴት እንደሚሄድ የሚታይበት አንዱ አጋጣሚ ነው። ሕወሓት በዓለም ዙርያ የሰራቸው እኩይ ተግባራት ሁሉ እንዲጋለጥ የእግዚአብሔር መንገድ ይህ ሊሆን ይችላል።ለእዚህ አንድ አባባል አለ።አንድ ብርጭቆ ከሁለተኛ ፎቅ ላይ ቢወድቅ አይጎዳ ይሆናል ከአስረኛ ፎቅ ላይ ከወደቀ ግን ስብርባሪውም አይገኝም።ሕወሓት በዓለም ላይ የበለጠ እንዲጋለጥ ዶ/ር ቴዎድሮስ አስረኛ ፎቅ ላይ መውጣት አለባቸው ይሆናል።ከአስረኛ ፎቅ ላይ የወጣ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበረ ሰው የሕወሓትን በዘር ላይ የተመሰረተ አደረጃጀት፣የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት መቀራመት እና በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮያውያን መገደል እና ሰቆቃ ለዓለም የበለጠ በዶ/ር ቴዎድሮስ ላይ በሚደረጉ ቀጣይ ተቃውሞዎች እንዲጋለጥ የተወሰነው ከላይ እንደሆነ ማን ያውቃል? ” ማን ያውቃል የመስከረም ወር እና የመስቀል ወፍ ቀጠሮ እንዳላቸው” ነው ያሉት ደራሲ እና ገጣሚ መንግስቱ ለማ።
ጉዳያችን GUDAYACHN
No comments:
Post a Comment