Sunday, May 28, 2017

አሁንስ ሊመጣ ላለው ዝግጁ ነን?።


    




ለለውጥ እንደቆመ ወይ ምኞተኛ በመሆን ሳይሆን እራሱን ካገዛዙ በኩል አድርጎም ይህን ቢያደርጉ ያ፤ ይህ ቢሆን ደግሞ ያ እያሉ መጣዊውን ያገራችንን ሁኔታና የገዥዎቻችንን መጣዊ እጣ ፋንታ በሁሉም አቅጣጫ ለማየት ቢሞከርም የዚህ ስርአት እድሜ አጭር መሆኑ ግልፅ ብሎ የሚታይ እየሆነ ነው። በፊትም ህዝብ ተቆጥቶ አደባባዬች ላይ መውጫው ጊዜ ላይ መደረሱን ቀድመው ያዩም ሲወተውቱም የነበሩ ነበሩ።
እንደሚገሉ፤ እንደሚያስሩን፤ ከኛም አልፎ ቤተሰባችን ላይ ሊደርስ የሚችለውን መቼ አጣናው። መገዛትንና ተቆራፍዶ መኖርን ምርጫ አድርገን ልንወስደው  አንችልም። ምንም አይነት መሰዋትነት ቢያስከፍለን ልንታገለው ወስነናል።  በሚሉ የወጣቶች ድምፅ ሞገድ ሲሞላ ማየት ለቻለ ሊመጣ ያለውን ህዝባዊ ቁጣ አይቀሬነት አመላካች ነበር።  ጥረቱ  የምር ተደርጎ አልተወሰደም እንጂ ቄሮዎች አውራ የሆኑ ድርጅቶችን ቀርበው “እኛ ልናፈነዳው ዝግጁታችንን ጨርሰናል። ተባብረን ብናደርገው የተሻለ ነው በሚል  ህዝባዊ እንቢታው ከመነሳቱ ከአመታት በፊት  ሞክረዋል”።
አሁንም ጨፍጫፊ አንባገነኖችና፤ ዘራፊዎች ስልጣን ላይ አሉ። ዘጠና ሚሊዬን በጭራሽ ደስተኛ ያልሆነና ተበዳይ ህዝብ ደግሞ በሌላ ጎን አፍጦ አለ። የሰባዊ መብት፤ የፍትህ፤ የጤና፤ የምግብ፤ የመጠጥ ውሀ፤ የትራንሰፖርት፤ የስራ አጥነት፤ የኑሮ ውድነት፤….. የቀውሱ ብዘት ተዘርዝሮ አያልቅም። መሀል ዋና ከተማው አዲስ አበባ ውስጥ ታይፎይድና ታይፈስ አንዴ ያልታመመ ሰው ፈልጎ ማግኘት አይቻልም። ምን አለባት በለስልጣናቱን ጨምሮ። ተስቦዎች ከመራቆትና ከረሀብ ገር ቀጥተኛ ቁርኝት አላቸው። የቆሼው እልቂት አይነት አንድ ጠዋት ስንነሳ በሺዎች ባልታወቀ ተላላፊ በሽታ  አለቁ የሚል ዜና ቢሰማ  በአገራችን ሁኔታ  የማይጠበቅ አይደለም።  ዜጋውን ካገሩ ማሳደዱን በርትተውበታል።   የአፍሪካ አገሮች አስር ቤቶች በወገኖቻችን ተጣበዋል። በአረብ አገራት በሴት እቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለው መከራውም ጎዞውም ቀጥሏል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ከባድ ችጋር እንደ አምናውና  እንደካቻምናው ዘንድሮንም ተሻግሮ ለከርሞው የማያልፈን መሆኑን ሊደብቁት የሚቻላቸው አልሆነም። ዜጋው ይህንን ሁሉ ያውቃል። መንግሰት ዶላር እንደቸገረው፤ የአገዛዙን መዳከምና መከፋፈልም እየሰማ ነው። በህዋዋት ውስጥ ያለው መከፋፈል ብቻ ሳይሆን አጋር ከሚሏቸው ድርጅቶች ጋር ያለው ግንኙነት ወደተሻለ አይደለም ወደነበረበት መመለሱ እራሱ በሰማያዊ ታምር ካልሆነ ከዚህ በሗላ የሚቻል አይደለም።
ውጪዎቹም ለኛ በመጨነቅም ብቻ ባይሆን በጣም ብዙ ህዝብ ስለሆንን የኢትዬጵያ ሁኔታ በጊዜ መላ ካልተባለበት ቀውሱም ሆነ ጦሱ ትልቅ፤ መመለሻውም አስቸጋሪ እንደሆነ ያውቃሉ። በዚህ ምክንያት እየበረታ የመጣባቸውን ውጫዊ ጫናም  እየሰማ ነው። ይህ እየጨመረም ሂያጅ ነው። በተጨማሪም አገዛዙን አጣብቂኝ ውስጥ የሚከቱ አካባባያዊና አለምአቀፋያዊ  የሁኔታዎችን መቀያየርንም ይሰማል።
አገዛዙ ላፉም ቢሆን ዲሞክርያሲያዊ፤ ሰብአዊ፤ ባለ ነፃ ሜዲያ የመሆኑን ነገር ከተወው  ቆይቷል። ለገበሬው፤ ለብሔር ብሔረሰቦች፤ ክልል፤ ኢህአዲግ እራሱ ህዘብ እያየው ታሪክ  እየሆነ ነው። “ወደመጣችሁበት” ትንቢት ሆነ መሰል ህዋዋቶች ብቻቸውን ቆመዋል። ይሄም  ሂደት እየጨመረ ሄያጅ ነው። ስለተናጋና ተጓታች ስለሆነ ለይስሙላም ቢሆን የነበሩ ነገር ግን የማይኖሩና የማይደረጉ ተመሳሳይነት ያላቸው ነገሮች እየጨመሩ  መሄዳችው አይቀርም። ይህን ሁሉ ደማምሮ ሲያይየ የሚደርስበት ድምዳሜ ያገዛዙን ፍፃሜና ለነፃነቱ የተፈጠረውን ምልካም አጋጣሚም ነው።
ወታደር ከካንብ ወጥቶ ከህዝብ ጋር መኖር ጀምሯል። በህገመንግሰት ሳይሆን ባስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየተሞከረ ነው። በየቤቱ የገባውን የሟቾቹን የታሳሪዎችን ብዛት፤ ለተናጋሪው የከበደውን ግፍና ነውር፤ ህዘብን ህዝብ ላይ ማስነሳትና የጅ አዙር ፍጅት ሁሉ ተስፋ መቁረጥና ለመግዛት አቅም ማጣት ያመጣው መሆኑን ህዘብ አያጣውም። እንደህዝብ ለመንግሰት ተሀድሶ የሚባል ነገር የለም፡፤ እርጅና ነው። ሞት ነው። እንግዲህ ጥልቅን ሳይጨምር ቢያየውም ማለት ነው። ከተቃዋሚዎች ጋር የተባለውን ህዝብ ጉዳይ የሰጠው አልሆነም። የጠረቤዛውን መፍትሄ ከመጥላት አይደለም። ወይ ሊሆን የሚችልበት የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እድል ኖሮ አልታየው ብሎም አይደለም። ህዝብም ሆነ ህዋዋቶችም እራሳቸው ተቀናቃኞችም ቢሆን በዚህም ሆነ አስገዳጅ  በሆነው መንገድ መጨረሻው ለባለስልጣናቱ ተመሳሳይ መሆኑን አሳምረው ስለሚያውቁ ነው። ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ጫወታ ብቻ ነው።
“አገዛዙን ያስጠላነው እኛ ነን። ማስታረቅም እንችላለን”። ያው አመል የሆነ አጉል ህዝብ ላይ መታበይ ነው። ይህን የሚሉት በታምር ሆነ እንበልና “አገዛዙ ስልጣኑን በሰላም ሊሰጣቸው  ቢሆን እንኳ” ይህን እንደመፍትሄ ህዝብ እንዲገዛው የማድረግ ተቀባይነቱ የላቸውም። ይህንን እነሱም አያጡትም። በተረፈ ተቃዋሚዎች ካገዛዙ ጋር ለጠረቤዛ ዙሪያ መፍትሄ መቀመጣቸው ለነሱ አጉል ልፋትና የባከነ ጊዜ ከመሆኑ ውጪ ህዝብን ከትግሉ ከማዘናጋት አኳያ የሚቀርበው ምክንያት ብዙም አያሳምንም። በመሳተፋቸው የሚያስገኙትም። ቢያገኙም የሚጠቅማቸው። ይህም ሆኖ ደግሞ የሚያጡት  ታላቅ የሆነ ነገር ያለበት ጉዳይ አይደለም። ሰላማዊው መፍትሄ እዚህ ደረጃ ለመደረሱ የዝሆኑን ድርሻ አሁንም ገዥዎቻችን ናቸው የሚወስዱት። ዋናው አሳሳቢ የሆነው ይህንን የሚያህል አገራዊ ቁምነገር በይበልጥ አገር ውስጥ ለለውጥ የቆሙ ክፍሎች እንደ ሁለተኛ አማራጭ እንኳ አገዛዙን ባላካተተ ሊዘጋጁበት አይደለም መታሰቡ እራሱ ትክክል አይደለም የሚል ክርክር ላይ መሆናቸው ነው።  ይህ አላስፈላጊ የስልጣን ፍክክርን ማስከተሉ ስለማይቀር መንገራገጭ ውስጥ ሊከተን  የሚችልበት እድል  አለው። የመከራው ዘመን መቋጨት ሲቻልም እያረዘመው ነው።
በዋናነት ህዘብ ካገዛዙ ጋር ተፈታትኗል።  ህዝብ  ሀያል መሆኑ ሁሌም ቢሆን  የታወቀ ነው። ሕዝባዊ ሀይሉ  ይገለፅ ዘንድ ምክንያት አለው ወይ?። ጉልበተኛነት ይሰማዋል ወይ? ምሬቱ ምን ደረጃ ደረሷል። ስለሚወስደው እርምጃ እውቀቱ አለው ወይ?  አጋጣሚዎች ተመቻችተዋል ወይ? በመሳሰሉት የሚወሰን ነው የሚሆነው። ጠቅላላ ያገራችን ነባራዊ ሁኔታ የህዘብ ሃያልነት እንደገና ለመገለጥ የተደላደለ ሁኔታ መኖሩን  ነው የሚያሳየው። ሀይሉን በምን መንገድ ፍልሚያው ላይ እንደሚያውለው በቂ እውቀትና ተሞክሮ ያዳበረገበት ሁናቴም ነው ያለው። በሚሊዮኖች ድርሻ በሚያደርጉበት ከተማን ጭር ማድረግ፤ሲያሻው አደባባዬችን መሙላት አልያም መገበያየትን ማቆምና መንገዶችን መዝጋት እንደሚችል ያውቃል። ይህ እያደገና እየሰፋ አገራዊ መልክ እየያዘ መሄዱ አይቀርም። እርቆ ሄዶ ዜጋው በመሳርያ እራሱን ወደመከላከል የዞረበት ሁኔታም ነው ያለው። ተፅኖ ፈጣሪና ወሳኝነት ያላቸው ጠንካራ የተቃውሞ ድምች ከማይጠበቁ  አካባቢዎች መምጣትታቸውና  እየበዛ መሄዱ ሌላው መጣዊው ሁኔታ ላይ አስረጅ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።
ጠቅለል ባለ ሁኔታ የአገራችን ሁኔታ ይህን ከመሰለና ጉዞው ወዴት እንደሆነ በከፊል እንኳ ለተስማማ በቀጣይ ሊመጣ ያለውን ለማየት አይቸገርም። መልስ የሚያሻው ታላቅ አገራዊ ቁምነገር አሁንስ ለለውጥ ዝግጁዎች ነን ወይ?። የሚለው ነው። በእርግጥ ለለውጥ ቆመናል ላልን  ክፍሎች ብዙ መልስ የሚሹ ተያያዝ ጥያቄዎች ተድርድረው እየጠበቁ ነው። የተባበረ አቅምን ስለመፍጠር፤ ሽግግር፤ ጉዟችንን፤ ታምቀው ታምቀው የቆዩ የተለያዩ የመሀበረሰብ ክፍሎች የነሷቸው ጥያቄዎች ሊካድና የተለመደ ሰበብ ሊሰራለት በማይቻል አደባባይ ላይ ፈንድቷል። ጥያቄዎቹ አገዛዙ እንዲመልሳቸው ታስበው አይደለም መራር መሰዋንት እየተከፈለባቸው ያለው። ግልፅ መሆን ያለበት አበባየሆሽ መጨፈርያ እንጂ  አገራዊ መፍትሄ አይሆንም። ይሄ ያው የተለመደ ጎታታነት ነው። እነዚህ ሁሉ በሚመለከታቸው በጋራ ተሰርተው ቢያንስ ሁሉ ማለፊያ ነው ሊሉው የሚችለው መፍትሄን ይሻል። እነዚህን የቤት ስራዎቻች እየሰራን ነው ወይ?። እየተሰራበት ነው ከተባለ ስራው  ከነበርንበት ምን ያህል ፈቅ ብሏል?። ሌላው ቢቀር ዜጋው ለመብቱ እያደረገ ባለው ተጋድሎ አጋዥ መሆን ባይቻል  አሁን እንኳ አፍራሽና አዳካሚ ከሆነ ሚና ውስጥ መገባት የለበትማ።
ለውጥን አምርሮ ፈልጎ -ለውጥን ምርር ባለ ሁናቴ ፈርቶ ደግሞ አይሆንም። አንዱን መምረጥ የግድ ነው። ዛሬ በገፍ  እየተቀሉም ዜጎች አደባባይ ወጥተው መብታቸውን መጠየቃቸው እንጂ ዛሬ የተፈጠረ አገራዊ ችግር አንድም የለም። አዲስ የሆነ የህዘብ ጥያቄም የለም። መብታቸው ሊሆን ይችላል የሚሰኝ አንድም ጥያቄም የለበትም። እንደውም ከመብትም በላይ ነው። ይህን የሚሉት ስለህልውና ሲያወሩ የዜጋውን ህልውና ከአገር ህልውና እንዴት ለይተውት እንደሆነ  በጭራሽ አይገባም። እነንትናን ሊያስደነግጥ ይችላልና መሬታቸውን እየተቀሙ ለማኝ ሲደረጉ ዝም ይበሉ?። ያላባራ ፍጅት ሲፈፀምባቸው ወይ አንድ ህዘብ ቋንቋው የእስርቤት ቋንቋ እስኪሆን ሲጋዝ ሳይታገሉ ይለቁ ነው ወይ?።
መፍትሄ ፍለጋው ላይ ድንኳን አልበቃ ብሎ የሀዘን ቀን ከሶስት ወደ አንድ ቀን እስኪቀየር ኤድስ ህዘብን ሲያረግፈው አንድና አንድ መፍትሄ “አንድ ወንድ ካንድ ሴት መታቀብ” መሆኑን ሲወተውቱ የነበሩ ነበሩ። የዚህ አይነት መፍትሄ ያምራል። በአድማጭ በቀላሉ ተቀባይነትም አለው።  ሊተገበር የሚችል እንደውም በእርግጥ መፍትሄ ነው ውይ ቢባል በጭራሽ።  ኢትዮጵያ ትቅደም- ኢትዬጵያን ያስቀደመ ነው፤ አስቀድማላው….. ጎራና ግርግዳ መስራት መፍትሄ አይሆንም። ሲጀመር በጭራሽ አዲስ አይደለም። ወደሗላም ቢኬድ የነበሩን አገዛዞች በሙሉ  ይሄው ነው ምክንያታቸው። ሁሉም የለየላቸው ጨካኞችና ጨፍጫፊ አንባገነኖች ግን ነበሩ። የአለም መጨረሻ ሗላ ቀርና ደሀ የሆነው እንደ አንድ አገር ህዘብ ምንም አንሶን ወይ ተረግመን አይደለም። መፍትሄው የማይሰራ ወይ እኩይ ለሆነ አላማ ሲገፋ ስለነበር ነው። ታዲያ ዛሬ እንኳ መፍትሄ ፍለጋው ላይ  ሰው ቅድሚያ የማይደረገው ለምንድን ነው?።

...
እንደ አንድ የመሀበረሰብ አካል መቶ የማይሞላ ጋዜጠኛ ወይ አስተማሪ ጥያቄ የመጠየቅ መብት አለው። የአንድ አገር ዜጎች እንደ ጋንባላ ወይ እንደ አፋር ግን ጥያቄ መጠየቅ፤ የተለየ ፍላጎት ሊኖራቸው አይችልም። የኦሮሞ ህዝብ የመብት ጥያቄ አንስቷል። ስለዚህ አርማጌዲዬን ሊሆን ነው።  ከዚህ አይነቱ እሳቦት መውጣት አለብን።  አገር የጭቃ ቤት አይደለም። ዜጎች መብታቸውን ስለጠየቁ የሚፈርስ። ህዘብን ማሸማቀቁና ማሰጠኑም ለከት አጥቷል። ልጓም ሊበጅለት ይገባል። ጥቂት፤ ኦነጎች፤ ዘረኞች፤ ጎጠኞች፤ ጠባቦች፤ ግንጣዬች… አሁን ደግሞ በአሜሪካ ተቀምጠው ይህ ሁሉ  እራስን መሸንገያና ሌላውን ህዝብ ማወናበጃ  ብቻ ነው። ህዘብ ለመብቱ የታገለው ፍፁም ጨዋነት ባለበት በሆነበት ነው ይህ ሁሉ ውርጂብኝ። አገዛዙ ፍጅት ከሚፈፅምበት አመክንዬ ጋር በሚያሳዝን ሁናቴ ብዙው ውርጂብኝ ተመሳሳይነት አለው።
በአሉ ግርማ ይህን አይነቱ ሁኔታ በፈጠረበት ስሜት ይመስለኛል
“ እስቲ ላንጎራጉር – ከአድማስ ባሻገር፤ ያለ ሰው ቢወዱት ምን ያደርጋል አገር”። ያለው።  በምንመ ምክንያት ይፃፈው ሰሞኑን የሚሰማኝን ስሜተ በትክክል ገልፆልኛል። ልጨምር ብል የምጨምረው  “ፍቅሩና መተባበሩ ቀርቶ- መጨካከኑ ቢቀር ምን አለ”። የሚለውን ብቻ ነው
ሊሰራበረት የሚገባው ፖለቲካው ግን ብቻ አይደለም። ትግሉም ነው። ብዙ ድክመቶች ብዙ ያልተሟሉ እንከኖች  አሉት። የመታገያ እቅዱ በወረቀት ላይ መቀመጥ አለበት። የለውጥ ሀይልን ስለማደራጀት፤ የገንዘብ አቅምን ስለመገንባት፤ መረጃ አሰባሰብ፤ አያያዝና አጠቃቀማችን። መሳርያ በጁ ያለወን ጨምሮ ከዚህ የበሰበሰ ስርአት ጋር የተነካኩ ዙጎቻችንን በለውጡ ሊኖራቸው ስለሚገባ ድርሻ ። አገር ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የተመቸ አይደለም እነዚህን ስራዎች ወደወጪ አውጥቶ  መስራት ስለሚቻልበት ሁኔታ። በዋናነት የስርአቱን ፍፃሜ ለማድረግ ኢኮኖሚውን ወይስ መሳርያ በጁ ያለውን?። የምርጫ ካርድ ቀዳዶ መጣል ወይስ የተገኘችውን ቀዳዳ ሁሉ ትግሉን ሊያግዝ በሚችል መንገድ መጠቀም?፤ የረጅም ጊዜ የሚቀጥል ህዝባዊ እንቢተኛነት ወይስ በጣም ፈጣን የሆነ በሳምንት ውስጥ ማጠናቀቅ በሚያስችል ደረጃ ማቀድና መዘጋጀት? …… ብዙ ብዙ።
ብሔራዊ ጭቆና ይብቃ!።

No comments:

Post a Comment