Tuesday, May 2, 2017

አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ከሳኡዲ የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ተመለከተ

   


አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ከሳኡዲ የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ተመለከተ

የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ወረቀት አልባ ስደተኞችን ከሀገሩ ለማስወጣት ይፋ ያደረገውን የሶስት ወራት የምህረት አዋጅ ተከትሎ ወደ ሀገራቸው ይገባሉ ተብለው የተጠበቁ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ መቀነሱ ታወቀ፡፡ በሳኡዲ አረቢያ ወደ መቶ ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ያለ ወረቀት እንደሚኖሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን የምህረት አዋጁን ተጠቅመው ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸው ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
‹‹ሀገር ቤት ሔደን ምን እንሳራለን፡፡›› የሚሉት ስደተኞቹ፣ ‹‹የሶስት ወራቱ የምህረት አዋጅ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ በወረቀት አልባ ስደተኞች ላይ የሚጣለውን ማንኛውንም ቅጣት ተቀብለን ሳኡዲ መኖር እንፈልጋለን፡፡›› ብለዋል፡፡ አስተያየቷን ለቢቢኤን የገለጸች በሳኡዲ የምትኖር አንዲት ወረቀት አልባ ኢትዮጵያዊት፣ እሷን ጨምሮ አብዛኛው ህገ ወጥ ስደተኛ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ፍላጎት እንደሌለው ተናግራለች፡፡ ‹‹በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ ካለው አጠቃለይ ሁኔታ አንጻር ወደ ሀገር ቤት መመለስ የማይታሰብ ነው፡፡›› ያለችው ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገችው ይህች ስደተኛ፣ ወደ ሀገር ቤት እየተመለሱ ያሉት ኢትዮጵያውያን ቁጥርም፣ ኢዚህ ካለው ወረቀት አልባ ስደተኛ ቁጥር አንጻር እጅግ አናሳ መሆኑንም ገልጻለች፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በሳኡዲ የሚኖሩ ወረቀት አልባ ስደተኞች እና ወደ ሀገራቸው እየገቡ ያሉ ስደተኞች ቁጥር ከጠበቀው በታች እንደሆነበት ገልጾ፣ በቀሩት የምህረት አዋጅ ቀናት ውስጥ ዜጎቹ ተጠቃለው ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ተደጋጋሚ ጥሪ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ የምህረት አዋጁ ከተጠናቀቀ በኋላ ለሚደርስባችሁ አደጋ ኃላፊነቱን ማን ሊወስድላችሁ ይችላል የሚል ጥያቄ ከቢቢኤን የቀረበላት ስደተኛዋ ‹‹ማንም፡፡›› ስትል በሲቃ ድምጽ መልሳለች፡፡ ከዚህ ቀደም በሳኡዲ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ በሀገሪቱ ፖሊሶች እና በአንዳንድ ጎረምሶች የደረሰውን ግፍ ያስታወሰችው ስደተኛዋ፣ በወቅቱ እዚያው ሳዑዲ እንደነበረች በመግለጽ፣ ከምህረት አዋጁ መጠናቀቅ በኋላ ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም ተመኝታለች፡፡ የሳአዲ አረቢያ መንግስት ይፋ ያደረገው የምህረት አዋጅ ሊጠናቀቅ ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል፡፡

No comments:

Post a Comment