Wednesday, May 10, 2017

አዋርድ ወይስ ዐዋርድ?




 ነጋ ተኣ

  በማንኛውም የሙያ ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት ላሳየ ሰው ውጤቱ  በከፍተኛ ባለሙያዎች ታይቶና ተገምግሞ  ለላቀ ማዕረግና ሽልማት ይታጫል:: በዚህ ዓይነት መሠረት ከፍተኛ ውጤት ባሳዩ ድንቅ ሙያተኞች በዕጩነት ቀርበው እንዲወዳደሩ ይደረጋል::   ከዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከልም የላቀ ነጥብ ያመጣውን ለመለየት አያሌ መስፈርቶች ይቀመጣሉ:: መስፈርቶቹን በሚገባ ያሙዋላ ሰው ለተሸላሚነት ብቁ ሆኖ ይቀርባል:: ይኼ በአጭሩና በቀላሉ የአንድን የሽልማት ሂደት ሊጠቁም ይችላል:: ምክንያቱም ለብቻው ተወዳድሮ  አሸናፊ መሆን ስለማይቻል የግድ ውድድርና ተወዳዳሪ ሊኖር ይገባል::  ሌላው በማንኛውም ዘርፍ ውጤት ያመጡትን ሙያተኞች ለመሸለም  ስለሚቁዋቁዋም ድርጅት ነው::  በየትኛውም አገር በማንኛውም ዘርፍ  በሙያ: በችሎታ:  በዕውቀትና በምርምር ረገድ  ለማህበረሰባቸውና ለአገራቸው የሚጠቅም ነገር ያበረከቱ  ውድ ሰዎችን ለማበረታታት: ለማጠናከር: ለማመስገን: ዕውቅና ለመስጠት: አድናቆት ለመቸር:  ምስጋና ለማቅረብ  ሲባል ሽልማት የሚያዘጋጁ ድርጅቶች  ሁኔታ ግምት ውስጥ የሚገባ ወሳኝ ነገር ነው:: ምክንያቱም ያለውን ውጤት አምኖና ተቀብሎ ዋጋ መስጠት ለተተኪው ትውልድ ሞዴል  እንደማዘጋጀት ነውና::  ስለሆነም እንዲህ ዓይነቱን ታላቅ ክብር የሚያስገኘውን   ቅርስ የሚገነባ ድርጅትን  ማንነት በግልጽ ማወቅ የማይታለፍ ጉዳይ ነው::  ታማኝነትን: ፍትሐዊነትን: ሚዛናዊነትን  እና ብቃትን እንደመመዘኛ የሚጠይቅ ተግባር ስለሆነ  በቀላሉ የሚታይ አይደለም::   በአጭሩ እና በቀላሉ ለመግለጽ ያህል ነውጂ በዛሬ በዚህ ዘመን   ስለ ሽልማት: ስለ ሸላሚውና  ስለተሸላሚው   ሁኔታዎች በጥልቅ ለማስረዳት መሞከሩ  አስተዛዛቢ ነው::   እያንዳንዱ ሰው  ግዙፍ ላብራሪ በእጁና በኪሱ ይዞ ስለሚዞር  ስለዚሁ ነገር ለመረዳት  አድካሚ ስለማይሆን ጠቆም አድርጎ ማለፉ አንባቢን ማክበር ይሆናል::  

ወደ ዋናው አርእስቴ ልምጣ::  “አዋርድ ወይስ ዐዋርድ” ማለት ምን ማለት ነው? ይባል ይሆናል:: ግርርታም የሚፈጥር ነው:: ቃሉ    የሚያወዛግብም ሊሆን ይችላል::  ነገር ግን ቀላል ነው::
ዛሬ ቴዎድሮስ ካሳሁን የዘመናችን አወዛጋቢ ድምጻዊ ሆኖ ተገኝቶአል::  ልክ እንደ 1950ዎቹ: 1960ዎቹ እና ከዚያም ወዲህ  የድምጻዊያን ንጉሥ ተብሎ የሚጠራውና እራሳቸው ታላላቅ ድምጻዊያን  እንደነማህሙድ አህመድ: እንደነ ታምራት ሞላ: እንደነ ዓለምአየሁ እሸቴ:  እንደነምኒልክ ወስናቸው: እንደነ መልካሙ ተበጀ: እንደነ አያሌው መስፍን: እንደነ ብዙነሽ እና ሂሩት በቀለ”:  እንደነ አስቴር አወቀ  ሁሉ የመሰከሩለት ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ  በዘፈናቸው ዘፈኖቹ እልህ አስጨራሽ ፈተናዎች እንደገጠሙት ይታወቃል::
ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ   በየቀኑ እንደ ፍየል ወጠጤ የሚታሰር ነበረ:: የመድረክ ዝግጅቶች ሲኖሩትም  ከእስር ቤት እየተወሰደ እንደሚዘፍን  የነበሩ እማኞች አጫውተውኛል:: በየጊዜው የተለያዩ የማበሳጫ ስልቶች ይቀርቡለት ነበረ::   ለዚህም  አእምሮውን ስቶ  አማኑኤል ሆስፒታል ገብቶ ብረት አልጋ ላይ  እጅና እግሩ ታስሮ   እያለ የክቡር ዘበኛ አዛዥ ጄነራል መንግስቱ ንዋይ  ሂደው እንደጎበኙት  የሚታወስ ነው::  ይሄ ብቻም አይደለም::   ደብረ ሊባኖስ ገዳምም እንዲገባ ተደሮጎአል::  በጥቅሉ ድምጻዊ ጥላሁን ገሠሠ ሰባት ጊዜ ሞትን ድል የመታ ድምጻዊ ነበረ::  በምሥራቁ   ክፍለ አገራችን በወራሪው ሶማሊያ መንግስት የተከፈተብንን ጦርነት  ለመመከት  በሙያቸው ከዘመቱት አርቲስቶች መካከል ጥላሁን ገሠሠ አብይ ድምጻዊ ነበረ::  በሰሜኑ ክፍለ አገራችንም ከወንበዴዎቹ ገንጣይና አስገንጣይ ጋራ በሚደረገው ፍልሚያ  መካከልም ነበረ::  እስከ ሞት ደጃፍ የሚያደርስ መስዋእትነትንም ከፍሎአል::  ለመጥቀስ ያህል ስለሆነ ዝርዝር ውስጥ አልገባም::  እንዲህ ስል አገራዊ ተልእኮ ይዘው ከተሰማሩት አርቲስቶቻችን መካከል ለአብነት ያህል ጥላሁን ገሠሠን  ብቻ ጠራሁ እንጂ  የላቀ ድርሻ ያበረከቱ አርቲስቶች ብዙዎች እንደነበሩ ግምት ውስጥ ይጨመርልኝ::
በኢትዮጵያችን ውስጥ እውነትን የሚናገር: እውነትን የሚዘፍን: እውነትን የሚጽፍ: እውነትን የሚቀኝ:  እውነትን የሚፈርድ:  ለእውነት የሚቆም: ለእውነት የሚታገል ሰው ሁልጊዜ ፈተና አለበት:: ታላቁ ባለቅኔ ሎሪየት ጸጋዬ ገብረመድኅን  ደልቶት አላለፈም::  ደራሲ በዓሉ ግርማ  የዕድሜውን ያህል በህይወት መኖር አልቻለም::  አቤ ጎበኘውም  የእሳት እራት ከመሆን አላመለጠም::  በላይ ዘለቀም  የአርበኝነቱን ዋጋ መርካቶ ቃኘው  ሻለቃ ሆቴል ጀርባ  ዛሬ ፖሊስ ጣቢያ ያለበት ቦታ  ላይ በስቅላት ተገደለ::  ኮሎኔል አብዲሳ አጋም በጡረታ ዘመኑ አባጂግሳ የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶት ወደ ኦጋዴን በረሃ እንዲዘምት ከተደረገ  በሁዋላ  የማታ ዕድሜው  በአሳዛኝ ሁኔታ እንዲቁዋጭ  ተደርጎአል::  በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ዘርዝሬ ስለማልዘልቀው እዚሁ  ላይ ይብቃኝና ወደ ቴዲ አፍሮ ልመለስ::   ቴዲ አፍሮ የዘመኑ አነጋጋሪ ድምጻዊ ነው::  ቴዎድሮስ የሚዘፍነው ወቅቱን ነው:: ዘመኑን ነው:: የሚያቀነቅነው ድልና ገድልን ነው የሚያሞግሰው:: በቴዲ ድምጽ ውስጥ  አሸናፊዎችና ባለታሪኮች ከፍ ያለ ቦታ አላቸው::   ዓጤ ምኒሊክ: ዓጤ ኃይለሥላሴ:   ሩዋጭ ኃይሌ ገብረሥላሴ: ሩዋጭ ቀነኒሳ በቀለ:  ወዘተ  የመሳሰሉት  የቴዲ አፍሮ ድምጽ በአንክሮ ሲያቀነቅናቸው ተሰምቶአል:: ቴዲ የአድማጩን የጋለ ስሜት የመረዳት ክህሎት አለው::  ዛሬን መግጠም ይችልበታል:: ዛሬን መዝፈን ያቅበታል::  ይህ ደግሞ ራሱን የቻለ  ፈተና አለው:: ይህንን ፈተና ያለመፍራቱ  ደፋር ድምጻዊ አድርጎታል::  ስንቱ አንገቱን  እንደ ካሮት መሬት ውስጥ ቀብሮ መኖርን በሚመርጥበት ዘመን  አንገትን ቀና አድርጎ ድምጽን ከፍ አድርጎ በአደባባይ መዝፈን ራሱን የቻለ ጀግንነት ነው:: ቴዲ በዚህ ይደነቃል:: ይሁን እንጂ ደጋፊዎቹ ግምት የለሽ እየሆኑበት ሲያሳጡት እየተስተዋለ ነው:: አንዳንድ ሀያሲዎች  ኅጸጹን ሲያወጡበት: ግድፈቱን ሲጠቁሙበት:  በቴዲ አፍሮ ሳይሆን በአድናቂዎቹ  አማካይነት የማያባራ ውግዣ ያዘነሙ ሰዎችን ሰምተናል::   በቴዲ አፍሮ አድናቂዎችና በቴዲ አፍሮ ነቃፊዎች መካከል ያለውን  ጉዳይ  ራሱን በቻለ  አጀንዳ እንገናኛለን:: ስለዚህ አሁንም ወደ ተነሳሁበት ርእሰ- ጉዳይ ልመለስ::
በዶክተር ፍስሀ እሸቱ አማካይነት እየተመሠረተ ያለው አንድ ኢትዮጵያ ንቅናቄ  ቴዲ አፍሮን እሸልማለሁ ብሎ ትኩስ አጀንዳ ቀርጾ  እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ሚድያ ላይ እየሰማን ነን:: እያነበብንም ጭምር:: ይሁን እንጂ  በሸላሚና በተሸላሚ መካከል አለመግባባቶች ተነስተዋል::   ክርክርም በሚመስሉ ቃላቶችም ተወራውረዋል::     ስለዚሁ ጉዳይ የተሰማኝን ስሜት ላጋራችሁ ተመኘሁና በድፍረት ይህንን ጽሁፍ ለማቅረብ ዳዳሁ::  ስህተት ከሆነ በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃለሁ::በሸላሚና በተሸላሚ መካከል ለምን ስምምነት  ጠፋ ብዬ ራሴን ስጠይቅ ቀድሞውኑ ሥራው በስምምነት መቼ ተጀመረና የሚል መልስ እኔው ራሴ ለራሴ መልስ ሰጠሁ:: ቀጥሎም  የሸላሚው ማንነት: የሸላሚው መሠረታዊ ዓላማ እና ግብ ጥያቄ የሚያስነሳ  ስለሆነ የግድ ምላሽ የሚያስፈልጉ ናቸው::  እንደዚሁም የሽልማቱ  ሂደትም ራሱን የቻለ አነጋጋሪ ጉዳይ ነው:: ይህንን አስመልክቶ ዶክተር ፍሰሀ እሸቱ  በኤስ ቢኤስ ራዲዮ ላይ  ያቀረቡት መከራከሪያ ሃሳብ  ያደጉ አገሮችን  ተሞክሮ በማየት ነው የጀመርነው ስለዚህ ነውር የለበትም ባይ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ:: ስለዚህ የግሌን ሃሳብ መስጠት እፈልጋለሁ::  ዶክተር ፍስሀ እሸቱ መሠረታዊ ስህተት ሠርተው የሠሩትንም ስህተት  ላለመቀበል  አጀንዳቸውን አንጠራርተው  ካደጉ አገሮች ጋራ በማነጻጸር  ሊያስተባብሉ ብቻ ሳይሆን ሊያስተምሩም ሞክረዋል::  ተጨማሪ መሠረታዊ ስህተት  እየሠሩ መሆናቸውንም ታዝቤያለሁ::
ይኸውም አንደኛ ድርጅታቸው ገና በምስረታ ላይ የሚገኝየባህል ድርጅት  ነው::  የዶክተር ፍስሀ የባህል ድርጅት  በማንኛውም የሙያ ዘርፍ ወይም በተለይ የሙያ መስክ የላቀ ውጤት የሚያመጡ  ሙያተኞችን  እሸልማለሁና ሸላሚ ድርጅት ነኝ ብሎ ቢል  በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ የሚታወቅ ነገር የለም:: በዚህ ረገድ ራሱን ለኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ  ለተለያዩ ሙያተኞች አላስተዋወቀም::  ሌላው ትልቁ ስህተት  ስለሽልማት  መሠረታዊ ሕግጋቶችን የጣሰ አካሄድ መሄዱ ነው::  እርሱም  የሽልማቱ   ሂደትን በተሸላሚው ስም ሰየመውና አረፈው:: ይህ ማለት አንድ ሽልማት የሚዘጋጀው በራሱ መንገድ አለው:: ሂደት አለው:: ባህርያቶችና መስፈርቶች ይኖሩታል::  ተወዳዳሪ የሌለበት ገለልተኛና ነጻ የሆነ  ሙያውን የሚገመግም የዳኝነት ሚና የሚጫወት ኮሚቴ  የያልተፈጠረለት ሌሎች ዕጩ ተወዳዳሪዎች ያልተጋበዙበትና ያልተሳተፉበት  ወዘተረፈ ብዙ ብዙ ነገሮች የተጉዋደሉበት  ሂደት መከተሉ  ዶክተሩን ከነድርጅታቸው የሚያስገመግማቸው ሆኖ አግኝቻለሁ::   ምክንያቱም በደመ-ነፍስ ተነሳስቶ: በስሜት ተነሽጦ:  አንድ ነገር ለመስራት ማሰብ ሚዛናዊነትን ያሳጣል:: ፍትሃዊነትን ያጉዋድላል::  በማህበረሰቡ ዘንድም  የሚያመጣውን አዎንታዊና አሉታዊ እንድምታ  ቀድሞ አርቆ አለማየትን ያመላክታል:: በዚያ ላይ ቴዲ አፍሮን የመሰለ አነጋጋሪና አወዛጋቢ  ድምጻዊን የሚያክል ስም ለሽልማት መጠሪያ ወስዶ እንደገና ራሱኑ ለመሸለም  አስቀድሞ አሳውቆ   ለሽልማቱ የሚውል የገንዘብ ምንጭ በራሱ በተሸላሚው ስም መዋጮ ለመሰብሰብ ወስኖ  መነሳት ደረቅ ስህተት ነው::
በብዙ ነገሮች የተጉዋደለ  አካሄድ መሄድ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን ያስከትላል:: በሕብረተሰቡም ዘንድ አመኔታን ያሳጣል:: ምክንያቱም በይዘቱ: በቅርጹ: በባህርዩ በመንፈሱና በሁለንተናዊ ፍጥረቱ የተዛባ አመለካከት ይዞ ገና ለገና ሕዝብ ወደደ ብሎ  አጋጣሚውን ለመጠቀም መንደርደር ተገቢ አይሆንም:: ለዚህም ይመስላል ደምጻዊው  የቅሬታ መነሻ ያቀረበው::  ቅሬታው በባለሙያ ቢታይ እወነተኛ ቅሬታ ነው:: ማንም ሽልማትን አይጠላም:: ነገር ግን ማንም ሰው መሸለምን ይፈልጋል ብሎ  በማሰብና በመገመት በስሙ የፈለጉትን ማድረግ ተገቢነት የለውም::
አንድ ተዋቂ ሰው  የሕዝብ ንብረት ነው ተብሎ አለግባብ ካለ ባለቤቱ ፈቃድ  ወይም በቃልም ሆነ በጽሑፍ ሳያሳውቁና አሽታውንና እንቢታውን ሳያገኙ  ሚድያ ላይ በስሙ  መጠቀም መጀመር  ጥያቄ ያስከትላል:: ለአርቲስቱም ሞራል እና ያለበትን ደረጃ ግምት ውስጥ አለማስገባት ነው::  ተዋቂም ሆነ ሽልማት ሕግ አለው:: መንገድ አለው:: ሂደት አለው:: ሙያም ይጠይቃል:: ዝም ብሎ አይሆንም::  በዚህ ረገድ እኔ የቴዲ አፍሮ አቁዋም ደጋፊ: የፍሰሀ እሸቱ እና ድርጅቱ ነቃፊ ነኝ::      በመጨረሻም ዶክተር ፍሰሀ እሸቱ ቴዲ አፍሮን  ይቅርታ መጠየቅ አለበት::  ሃሳቡንም ማሰተካከል ወይም መተው አለበት:: በስሙ የሰበሰበውን ሳንቲም  ለባለቤቱቹ መመለስ ይኖርበታል::  ቴዲ የገንዘብ ችግር የለበትም:: አለብኝ ካለም ገንዘብ ሸልሙኝ ብሎ  የሚመጣ አርቲስት አይደለም:: ኩሩና ጨዋ ልጅ እንዲያውም ለብዙ በጎ አድራጊ ድርጅቶች በመቶ ሺህ ብር እርዳታ የሚሰጥ ሰብዓዊ ስሜት የሚያጠቃው ኢትዮጵያዊ ነው::  ዶክተር ፍሰሃ እሸቱ እና ድርጅታቸው በድፍረት ከገቡበት  ስሁት  በፍጥነት መውጣት አለባቸው:: አለበለዚያ እርሳቸውና ድርጅታቸው እንዳሰቡት ሳይሆን አርቲስቱን በነጻ ለድርጅታቸው ማስተዋወቂያ እየተጠቀሙበት ነው ያስብላል::  የጀማሪ ድርጅታቸውን ስም በመዋጮ ገንዘብና በሽልማት ስም  ለማስታወቂያ እየተገለገሉበት ነው ማለት ይቻላል:: ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የያዙትን አገራዊ አጀንዳ  ከእጅ የወደቀ እንቁላል ያደርግባቸዋል::  ሌላው  ቴዲ አፍሮ ያለፈውን ጨቁዋኝ ሥርዓት ስለሚያወድስ ቅሬታ ተሰምቶናል በሚሉት ኢትዮጵያዊንን በኩል ያለው ቅራኔ እጅጉን እንዲሰፋ እና የቴዲ አፍሮ ተቃዋሚዎችን እልህ ውስጥ እንደማስገባት ነውጂ ቅሬታዎችን አስወግዶ እንደማቀራረብ አይደለም::  ይህ ደግሞ እራሱን የሽልማት ሳይንስን የሚጻረር ነው::  ሁለት ወገኖችን በሚያወዛግብ አጀንዳን ለሽልማት ማብቃት ክፋት ነው:: ወይም ሆን ተብሎ የታቀደ ሤራ  ሆኖ ይቆጠራል::    ዶክተር ፍሰሀ እንደሚታረሙና ይቅርታ እንደሚጠይቁ ተስፋ አደርጋለሁ:: ቴዲ አፍሮም  በያዘው ጥሩ አቁዋም ጸንቶ ክብሩን እንደሚጠብቅና አድናቂዎቹን እንደማያሳፍር እምነት አለኝ:: አንድ ኢትዮጵያ ንቅናቄ  እና ዶክተር ፍሰሀ እሸቱ   ተገቢ እርምት ወስደው በተገቢ መንገድ ካልተራመዱ:  ለቴዲ አፍሮ “አዋርድ ሳይሆን ዐዋርድ”  ብለው እንደሚሠሩ ይቆጠራል::

No comments:

Post a Comment