Thursday, May 4, 2017

የእኛ ሰንድቅ ዓላማ ከፍ ሲል` የእነሱ ዝቅ አለ !

   
የእኛ ሰንድቅ ዓላማ ከፍ ሲል` የእነሱ ዝቅ አለ !! ይድነቃቸው ከበደ
“ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣የወራሪው የፋሽስት የጣሊያን ባንዲራ አውርደው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ሰቀሉ ! ”
“እንኳን ሰማይ ላይ ባንዲራሽን አይቶ
ኢትዮጵያ ሲባል ማን ዝም ይላል ሰምቶ
በቀስተ ዳመናሽ ሰማይ መቀነቱን ባንዲራሽን ታጥቆ
አርማሽ የታተመ እንኳን ባለም መዳፍ በአርያም ታውቆ”

ብላቴናው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ !የጀግኖች አርበኞቻችን የመታሰቢያ ክብር በአል ለ76ኛ ጊዜ ሊከበር የተወሰኑ ቀናት ሲቀሩ፣አምስተኛ የሙዚቃ አልበሙን “ኢትዮጵያ” የተሰኝ  ምርጥ ሥራውን ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን አቅረቦልናል፡፡ለዚህም ምስጋና ይገባዋል ! ይህ በታሪክ የራሱን አሻራ አስቀምጦ የሚቀረው ድንቅ ሥራው ፣በተለይ በተራ ቁጥር አንድ ላይ የተቀመጠው “ኢትዮጵያ” የተሰኘው የጥበብ ውጤት፤ የብዙ ነገር መገለጫ የሆነ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ከፍ አድርጎ ያሳየ ነው፡፡ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ጀግኖች አባቶቻችን እና እናቶቻችን በከፈሉት ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍ ብሎ የተውለበለበው ብላቴናው ቴዲ አፍሮ በዜማው ያወደሳት የእናት ሃገር መለያ ባንዲራችንን ነው፡፡
—-
ኢጣሊያ በዓድዋ ላይ የደረሰበትን ታሪካዊ ሽንፈት ለመበቀል ከ40 ዓመት ቆይታ በኋላ፣ ከኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር የማይነጣጠለው የኢትዮጵያ ባንዲራ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ ዓላማችንን ዝቅ አድርጎ፣ድንበር ተሻግሮ በፋሺስታዊ መንግሥታት ድጋፍ አማካይነት ሚያዝያ 1928 ዓ.ም የጣልያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ፣ አዲስ አበባ ገብቶ በታላቁ ቤተ- መንግሥት የጣሊያንን ባንዲራ የሰቀለበት ቀን ነው ፡፡ከዚህ ቀን ጀምሮ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ለአምስት ዓመት ያደረጉት ተጋድሎ የትየለሌ ነው፡፡ ከአድዋው ዘመቻ (ከ40 ዓመት) በፊት ብዙም ያልተሻለ የጦር ትጥቅ የነበራት ኢትዮጵያ፣ የወራሪው የፋሽስት የጣሊያን ጦር በፅናት ተዋጋች ፡፡
—-
“ኢትዮጵያ ሀገሬ
ኢትዮጵያ ሀገሬ
ባንቺ አይደል ወይ ክብሬ
ባልፍም ኖሬ ስለናት ምድሬ
እሷናት ክብሬ አረ እኔስ ሃገሬ”

አሁን ላይ ድምጻዊ ቴዲ! “ኢትዮጵያ” በሚለው ዜማ የተቀኘላት የእናት ሃገር ክብር ያኔም የሆነው ይሄ ነው ፡፡ ጀግኖች አርበኞቻችን ብንሞት ለሃገር፣ ለሃገር መሞት ደግሞ ክብር ነው፡፡ በማለት በሀገር ፍቅርና በብሔራዊ ስሜት ቆፈጠን ብለው፣ኢትዮጵያውያን ጀግኖች እምቢ ለነፃነቴ፣አረ እኔስ ለሃገሬ በማለት የሽምቅ ውጊያ ጀመሩ፡፡ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች በጣሊያን ወታደሮች ላይ ጥቃትቸውን ቀን ከለሊት በፅናት በመቆም አፋፋሙ፡፡ ወራሪዊ የጣሊያን ጦር ክፉኛ ተሸነፉ፡፡በየቦታው ኢትዮጵያዊያን አርበኞች ድል የመሆናቸው ዜና ናኘ፡፡ የጠላት ጦር አዲስ አበባን ለቀው ፈረጠጡ፡፡በዚህ ታሪካዊ የድል ቀን ! በጄኔራል ካኒንግሂም እና በጄሪራል ኘላት የሚመራው የእንግሊዝ ጦር ለኢትዮጵያዊያን አርበኞች ያደረጉት ድጋፍ በታሪክ የሚወሳ ነው፡፡
—-
በሕዝቡና በአርበኞች ተጋድሎ የኢትዮጵያ የድልን ቀን ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ተበሰረ፡፡ ንጉሰ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ! ሚያዝያ 1928 ዓ.ም የጣልያኑ ጦር አዛዥ ጄኔራል ባዶሊዩ የሰቀለውን፣የወራሪው የፋሽስት የጣሊያን ሃገር ሰንደቅ ዓላማ አውርደው፣ በከፍተኛ አጀብ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በታላቁ ቤተ-መንግሥት ሰቀሉ፡፡በዚህን ጊዜ የእኛ የኢትዮጵያዊያን ባንዲራ፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንድቅ ዓላማችን ክፍ ሲል የእነሱ ዝቅ አለ ! ለዚህ ታላቅ ድል ላበቁን ጀግኖች አርበኞቻችን ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላላም ትኑር !!!

(ይድነቃቸው ከበደ)

No comments:

Post a Comment