Sunday, May 7, 2017

ቴዲ አፍሮ እጠነቀቃለሁ ብሎ የሰራው ሥህተት! ድጋሜ ታርሞ ይውጣ! – ሰርጸ ደስታ



ቴዲ አፍሮ ምናአልባትም አገር ወዳድነቱ ነው የሚል ግምት አለኝ ኦሮሞ ነን በሚሉት ዘንድ አልተወደደም፡፡ ይህን ስል የኦሮሞ ሕዝብን በመወከል ሳይሆን ከሌላው በላይ ኦሮሞ ነን ብለው ሌሎችን በንግግራቸውና በአመለካከታቸው በማሸማቅቅ ገዝፈው ዛሬ ያለ እኛ ፍቃድ አንድም ቃል መተንፈስ አትችሉም በሚሉት በኦሮሞ ፈርስት ቡድን ማለቴ ነው፡፡ ቴዲ በአንድ ወቅት ሚኒሊክ አገርን ለመገንባት ያደረጓቸውን ጦርነቶች እንደ ቅዱስ ጦርነት ነው የምቆጥረው ብሏል ተብሎ በእነዚህ ከኦሮሞ ሕዝብ በላይ ኦሮሞ ነን በሚሉ በዋናነት በአርሲ እስላማዊ አክራሪዎች የሚመራው ቡድን አባላት ዘመቻ በቴዲ ላይ እንዲከፈት ምክነያት ቢሆንም እንዚህ ቡድኖች ድሮውንም ጠብ ያለሽ በዳቦ ብለው ነገር ሲጠብቁበት እንደነበር ይሰማኛል፡፡ ጥቁር ሰው የተባለውን ዘፈኑንም በእጅጉ ያለእኛ ፍቃድ እንዴት ሊያወጣው ቻለ በሚል ተገዳድረውታል፡፡ አሁንም ኢትዮጵያ የሚለው ነጠላ ሲለቀቅ በዚሁ የኦሮሞን ሕዝብ ሁሉ ከእኔ ፈቃድና ቃል ውጪ እንድም ሰው ስም መጥራት አይችልም በሚሉ የአርሲው ጽንፈኛ የሚመራው ቡድን አባላት ሕዝብን አንድ የሚያደርግ ዘፈን ጠብቀን ነበር ሆኖም አሁን ስናየው ልጁ የድሮውን ሥርዓት ከመናፈቅ ያለፈ ምንም ሊለወጥ አይልቻለም እና ተስፋ ቆርጠናል ያሉም አሉ፡፡ ነገሩን አሳንሼው እንጂማ ገና እልበሙ ይወጣል ሲባል የግድያ ዛቻም የዛቱ ነበሩ፡፡  በአጠቃላይ ቴዲም ሆነ ሌሎች ብዙዎች ስለ ኦሮሞ የመናገር መብታቸው የተገደበ በመሆኑ ድንገት አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት እንኳን የኦሮሞን ሕዝብ ለማወደስም ሆነ ለመውቀስ በሙሉ ልብ ሊሆን አልቻለም፡፡ ሰሞኑን ቴዲ ስለመይሳው ካሳ የዘፈነው ዘፈኑ የዚህ አንዱ ማሳያ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የዘፈኑ ቅንብርና ክሊፕሱንም በጣም ወድጄዋለሁ፡፡ ያው እንደ አንድ ዜጋም እንዲህ ያለ ዜማ ስሰማ ትንሽ ትንሽም ስለዚህች ዛሬ ደሀ ስለሆነች በፊት የት እና የእነማን አገር እንደነበረች የማቃት አገር በመሆኗ ላግደው የማልችለው ስሜት ይፈትነኛል፡፡ ምን አልባትም ያለቦታው ገብቼ ራሴ የፈለፈልኩት ሚሰጢር ይሁን ወይም ሳልፈልገው መጥቶ የገባኝ ስለኢትዮጵያ የሚያሳሰብ እንዲህ ያለ ታሪክ ነክ የሆነ ዘፈን ረጋ ማዳመጥም ይከብደኛል፡፡ ቴዲስ እንዲህ አንዳንዴ ይተነፍሰዋል፡፡ አሁንም ወሰደኝ ወደተነሳሁበት ልመልሳችሁ፡፡
ቴዲን በዚህ ዘፈን የብዙዎችን አማሮች ትግሬዎች ሌሎች ሕዝብንም ስሜት በብዙም በጥቂቱም የነካው ይመስላል፡፡ በተለይ የመቅደላውን ቴዲ ወዳጆች፡፡ ምን ያህሉ መቅደላን እንደሚያውቅ ባላውቅም፡፡ በዚህ ዘፈን ታዲያ ቴዲ አፍሮ ጎጃምና ጎንደር እያለ መጥቶ ኦሮሞና ተጉለት ሲል በስሜቴ ላይ በረዶ ነው የከለሰበት፡፡ እርግጥ ነው  ወለጋና ሐረር፣ ባሌና ቦረና፣ ኢሉ አባ  ቦራ፣ አርሲና ጂማ ብሎ ቢከሽነው የኦሮሞ ፈርስት እራት መሆኑ ነው፡፡  ምን አልባትም ሆን ብሎ ኦሮሞን ለመከፋፈል እንዲህ ያለ ዘፈን ዘፈነ ብለው ቀውጢ ሊያደርጉትም ይችላሉ፡፡  በአሁን ጊዜ ስለኦሮሞ ሕዝብ የተናገረ ሁሉ የሚገጠመው ይሄው ነውና፡፡ የሆነውም ቢሆን ግን ቴዲ አፍሮ በዚህ ዘፈን ኦሮሞን የገለጸበት ሥንኝ ከስህተትም ስህተት ነው እላለሁ፡፡ ኦሮሞ የሚል ቃል ባይናገር የተሻለ ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ስህተቶች በቴዲ አደለም የተጀመሩት፡፡ ከዚህ በፊትም ሌሎች እንዲሁ ዘፍነዋል፡፡ በእርግጥም በኦሮምኛ ዘፋኞችም የሚዘፈነው እንዲሁ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ኦሮሞ ከአሉ በኋላ ዘርዘር ቢያደርጉትም፡፡ ለመሆኑ ቴዴ አማራ የተባለውን ሕዝብ ጎጃም፣ ጎንደር፣ ተጉለት እያለ ሲዘረዝር ኦሮሞ ብሎ ማለፍን እንዴት ስህተት እንደሆነ አላስተዋለም; ቴዴ እዚህ ላይ ተሳስተሀል፡፡ ሌላውንም እንዲሁ ነው ያልኩት ማለት አይቻልም፡፡ ለምሳሌ አፋር፣ ሱማሌ ትልልቅ ሕዝብም ቢሆኑ በአንድ ቢገለጹ የሕዝቡ ማሕበራዊ እሴቶች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ጎራጌም እንደዛው፡፡ ኦሮሞ ግን ፍጹም እንደዚህ አደለም፡፡
ብዙ ጊዜ ይህን ጉዳይ አንስቼዋለሁ፡፡ የአሮሞ ሕዝብ በፍጹም የተለያዬ ማህበራዊ እሴቶች ያሉት ሕዝብ ነው፡፡ ሲጀምር ሕዝቡ ከታሪካዊ አመጣጡ ጋር በተያያዘ ከሁሉም ሕዝብ ይልቅ ብዝሀነት ያለው ነው፡፡ ቦረና ከወለጋ ከቋንቋ በቀር በምንም አይገናኝም፡፡ ሐረር ከኢሉ አባቦራ ጋርም ባሌ ከሸዋ፡፡ ይህ ሕዝብ ዛሬ ላይ ሆን ተብሎ በአንድ እንዲታጨቅ በመደረጉ ሁሉም እየተነሳ በአንዲት ኦሮሞ በምትል ቃል ያስረዋል፡፡ በጅምላ ይነግዱበታል፡፡ ዛሬ ላይ አርሲዎች የሚዘውሩት የኦሮሞ ፈርስት ቡድን ኦሮሞ በሚል ሁሉንም በጅምላ ከእኔ ሌላ አንድም ውክልና ሊኖር አይገባም ብለውት እየተንቀሳቀሱ ያሉት እንዲህ ባለው የጅምላ ማጨቅ ምክነያት ነው፡፡ ከጅምሩም በዚህ መልኩ እንዲሆን ታስቦበት 25 ሙሉ ማንነቱን ለማጥፋት የተዘመተበት ነበር፡፡ እንደእውነቱ ከኦሮሞ ሕዝብ በተሻለ በአማራው ሕዝብ ያለው ብዝሐነት ያንሳል፡፡ አማራ የተባለው ሕዝብ ሌላው ቀርቶ ሸዋን እንኳን ብናይ ተጉለት፣ ቡልጋ፣ መርሀቤቴ፣ ይፋት፣ መንዝ እያለ ይዘረዘራል፡፡ ጎንደሬንም እንይ ወልቃይት፣ ጸገዴ፣ ቋራ፣ ጋይነት፣ እስቴ፣ ፎገራ እያለ ይተነተናል፡፡ሸዋ አሮሞ ሰላሌ፣ አቢቹ፣ ሜታ፣ በቾ፣ ይላል ራሱን፡፡ ወለጋስ ሀረቶ፣ ሻምቡ፣ ኦኖ ይለዋል እራሱን፣ ጂማስ፣ ባሌስ፣ ሀረርስ፣ ኢሉ አባቦራስ፣ ቦረናና ጉጂስ; ይህና ከዚህ በላይ የሆነ ሕዝብ ነው በአንዲት ኦሮሞ በምትል ቃል ዛሬ ሁሉም ባቤት እየሆነበት የሚነግድበት፡፡ ሲጀምር ኦሮምኛ ተናጋሪ ሁሉ ከመዳወላቡ የመነጨ ነው ብሎው ሲዘፍኑልን የነበሩት ኦነጋውያን የታሪክ ስህተት መስራታቸው ሳያንሳቸው ሕዝቡን በኦሮሞነት ሥም በባርነት እንዲኖር ሌሎች ሕዝቦችም በኦሮሞ ሕዝብ ምክነያት በተገዥነት እንዲኖሩ ነው ያደረጉት፡፡ ዛሬ የአሮሞ ሕዝብ በኦሞነት ሥም ባይመክን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመታደግ ሸዋ ይበቃ ነበር፡፡ ይህን የምለው ሰሞኑን ስለሸዋ ራሱን የቻለ ክልል መመስረትን አስቤ አደለም፡፡ ስለእሱ እመጣበታለሁ፡፡ ይልቁንም ኦሮሞ ሁሉ በቀላሉ በሚዘውሩት እጅ በኦሮሞነት ሥም እየተዘወረ መሆኑ የሌሎችንም ትግል እያመከነው ስለሆነ ነው፡፡ ከኦሮሞነት ወጣ ባለ በመሠረታዊ ባሕላዊና፣ ማህበረሰባዊ ግንኙነት ላይ የተመሰረት ሕብረት ቢኖር የሸዋ አሮሞ ትግል ቢጀምር መጀመሪያ የሚቀጣጠለው ቅርቡ ወደ ሆነ ሸዋ አማራና ጉራጌ እንዲሁም ጎጃም ወልጋ አርሲ እያለ ነበር የሚቀጥለው፡፡ ዛሬ የምናየው ግን ከዚህ በተለየ መንፈስ ነው፡፡
አዲስ አበባ ማስተር ፕላን ገበሬዎችን አፈናቀለ ሲባል የባሌ ኦሮሞ ከጉራጌውን ከሰሜን ሸዋው አማራ ቅርብ አደለም፡፡ ኦሮሞ በሚል ዘረኝነት ሕዝብን ፋይዳ የሌለው አመጽን ከአገር አገር ከመዝፈን በአንዲት የጎንደር ከተማ ኢትየጵያዊ የሕዝብ ትዕይነት ወያኔ ምን ያህል እንደተሸበረች እናውቃለን፡፡ ሁሌም እለዋለሁ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ተከትሎ የመጣው አመጽ ለሌሎች ሕዝቦች መነሳሳት አስተዋጾ ቢኖራም መሠረታዊ አላማው በፍጹም ዘረኝነትን ያነገበ ሥህትት ነበር፡፡ ለአዲስ አበባ ገበሬዎች መፈናቀልና ፍትህ ማጣት ተቀዳሚ ጠያቂው ራሱ የአዲስ አበባ ሕዝብ መሆን በተገባው፡፡ ይህ ሊሆን ይችል ነበር ወይ ከተባለ አይሆንም ዛሬ ላይ ሁሉም ፍትህን ማሰብ አልቻለም፣ ታውሯል፡፡ ባሌ ያለ ኦሮሞ አዲስ አበባ ስለተፈናቀሉ ገበሬዎች ያመጸው ከፍትህ አንጻር ነው ወይ ከተባለ መልሱ አይደለም ነው፡፡ በኦሮሞነት ከመጣ ዘረኝነትና ሌላውን ከመጥላት እንጂ፡፡ አሊያማ ከአዲስ አበባ በላይም ደሀውን ገበሬ እያፈናቀለ ለባለጊዜዎች እየሸጠ ያለው በሥሙ የሚነግደው የአሮሞ ቡድን አደለ እንዴ፡፡ ጉዳዩ ከክልሉም ጋር አደለም፡፡ ያው ነው እዛው አዲስ አበባ ሥር ብዙ ገበሬዎች መሬታቸው ተቀምቶ ለሌላ የተሰጠባቸው በኦሮሚያ ክልል በተባለው ነው፡፡ ቡራዩ ሰበታ፣ ሌሎች ሁሉም መሬቱ የሚፈልጉት መሬቱን ለመሸጥ እንጂ ለሕዝቡ በፍትሐዊነት ለመስጠት አደለም፡፡ ገበሬው ከመገፋት አልዳነም፡፡ እንደውም ባይብስ፡፡ እንነጋገር ከተባለ የቡራዩ ከተማ አስተዳዳሪዎች ያላስለቀሱት ነዋሪ አለ; ሌሎቹስ፡፡ በእርግጠኝነት አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ነዋሪዎች ከኦሮምያ ወጥታችሁ አዲስ አበባ ሥር ተጠቃለሉ ቢባሉ በአንድ ሌሊት እንዲፈጸምላቻ በተቻኮሉ ነበር፡፡ በኦሮሞ ሥም እየደረሰባቸው ያለውን በደል እናውቀዋለን፡፡ ሲጀምር ሕዝቡን ማን ጠይቆት;   ማንስ ስለሕዝቡ ችግርና ስለገበሬ መፈናቀል ጉዳዩ ሆኖ፡፡ ጉዳያቸው ከመሬት መቀራመት ጋር ነው እንጂ፡፡ ለመሆኑ ኦሮሚያ የተባለው ክልል አንድ ይሄ የሚለው ከተማ አልምቷል;  እነጂማ እድሜ ልካቸውን እየታረሱ ሕዝቡ አሁን ላይ በበጋ አቧራውን በክርምት ጭቃውን ስለልመደው የጅማ ከተማ ሥራ መቼ ነው የሚያልቀው ሲባሉ ከማለቁ በፊት ምፅዐት ይመጣል በሚል ተስፋ ቆረጠው ተቀምጠዋል፡፡ ድሬዳዋ በማዕከላዊ ሥር ነች፡፡ እሷም ሞታ ሞታ ነው ግን አሁንም ብዙ አላገገመችም፡፡ አዳማ ቢባል ለአዲስ አበባ ቅርብ መሆኗና ብዙ ባለሀብት ነዋይ ስለሚያፈስባት ነው፡፡ አምቦ በመሀሏ መንገድ አቋርጧት ሲያልፍ ከተማ እንደመሆኗ በመንታ መንገድ መቋረጥ ሲገባት ሰው ጠፍቶ  ከሜዳ በገባው የመንገድ ሥፋት ሕዝቡም ተሸከርካሪውም ያችንው ጠባብ መንገድ ይጋፋል፡፡ ደግነቱ የአምቦ ሕዝብ በትራፊክ ሥርዓቱ የሰለጠነ ባይሆን እንዴት የከፋ አደጋ ባስተናገደች ነበር፡፡ ሲሆንማ አደለም አምቦ እነ ሆለታም በመንታ መንገድ መቋረጥ ነበረባቸው፡፡ የሰሜን ሸዋዋ ደብረብርሀን እኮ ተቋራጩን አስፈረሳ ነው እንደገና በመንታ መንገድ ጥራቱን በጠበቀ ሁኔታ እንዲሰራ ያስገደደችው፡፡ ኦሮሚያ በሚባለው ክልል በኦሮሞነት እንጂ በአካባቢው አስተዳደር ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቢያስብም ሕዝቡን በኦሮሞነት አምክነውት ከቁብም አይቆጥሩትም፡፡ ትንሽ ዳረጎት ከአገኙ እንደምናየው የሚኖርበትንም ቤቱንና ንብረቱን አስፈርሰው ለሌላ ይሸጡለታል፡፡
ብቻ እየሆነ ያለው በኦሮሞነት ሥም በጅምላ ሕዝብ እየተነገደበት ነው፡፡ አሊያማ የአርሲው ጀዋር እውን ስለ ሸዌው የጎበና ዘር ይገደዋል; ዛሬ ከአዲስ አበባ ጋር ሲገናኝ መሬቱ የኦሮሞነ ነው እያሉ የሚደነፉት እነ ኦሮሞ ፈርስት እኮ የመሬቱ ባለቤት የሆነውን ሸዌን የጎበና ዘር እያሉ ዛሬም ድረስ ከጎራ ለይተው የሚያሸማቅቁት ነው፡፡ ለነገሩ ሸዌው አይሸማቀቅም እንጂ በራሱ ታሪክ የሚያፍር አደለምና የጊዜ ጉዳይ ቢፈታተነውም፡፡ ኦሮሚያ ውስጥ እኮ አመት ሙሉ አመጽ ሲደረግ ብዙም ወያኔን ብዙም ትኩረት እንድተሰጠው አላደረጋትም፡፡ አምቦና ጊንጪ፣ ጀልዱን ሌላው ሸዋ ሲነሳ አስበረገጋት እንጂ፡፡ እውነታው ይሄ ነው፡፡
ቴዲ አፍሮ ግዙፉን ሕዝብ ጠላቶቹ ወገቡን አስረውበት በሚያሰቃዩት ሥም ኦሮሞ በምትባል እንዲት ቃል ሲያልፈው ቴዲ አንትም ነው ያለኩት፡፡ አሁንም ይሄ ዘፈን ተስተካክሎ ቢወጣ እመርጣለሁ፡፡ ድሮ እነ ሰለሞን ደነቀና አብተው ከበደ የተባሉ ዘፋኞች የተውልን ትውስታ ነው ዛሬ ያለን እንጂ ልንረሳቸው እኮ ቀርበናል፡፡ እነ አሊ ቢራም እኮ ኋላ ላይ ሁሉንም ኦሮሞ በሚል አጨቁት እንጂ ብዝሐነቱን የሚያሳዩ ዜማዎቹ ናቸው ዛሬም ድረስ የሕዝብን ቀልብ የሚስቡት፡፡ ማልቱ አዳ ኑባሴ የተዘፈነው  ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ነበር ኋላ በኦሮሞነት ታጠረና እዛም ለዛውን አጣ እንጂ፡፡ ቴዲ ይሄንን ዘፈኑን በልዩ ነጠላ ዜማ መልሶ እንዲያዜመው በትህትና እየጠየቅሁ ሀሳብና ግጥም እንድታዋጡ ሌሎችን እጋብዛለሁ፡፡ ዜማው ተመችቶኛል፡፡ ሲሆን ኦሮምኛ ሌላም የተቀላቀለበት ልዩ ነገላ ዜማ ቢሰራለት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲስ አበባን ያቀፈ ልዩ የሸዋ ክልሉ ሐሳብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ ሕገ መንግስት የተባለው የመለስና የሌንጮ ድርሰት ከጅምሩ አላማው አገርን ከማፍረስና ሕዝብን ከማቃረን ጋር ስለሆነ እርሱት፡፡ በየትኛውም ጤነኛ አእምሮ አዲስ አበባ ከኦሮምያ ጋር ጥቅም ትጋራ ብሎ አደለም በሕገመንግስት በጥያቄ መልክ እንኳን ሊነሳ የሚችል ጉዳይ አደልም፡፡ አዲስ አበባ ክልል ከሆነች በውስጧ ያሉ የተፈጥሮም ይሁን ሌላ ሀብት የአዲስ አበባ መስተዳድር እንጂ የኦሮሚያ ሊሆን የሚችልበት ምንም አይነት አመክንዮአዊ ሀሳብ አደለም፡፡ ክልል ከሖነ ክልል ነው፡፡ አዲስ አበባ በሬት ተከራይታ የተመሰረተች ከተማ አደለችም፡፡ የራሷ ሕዝብና አስተዳደር ያላት ናት፡፡ አዲስ አበባንና  ሌሎችንም ሁሉ ከነጋዴውቹ ህወሐትና ኦህዴዶች እጅ አላቆ ልዩ አስተዳደር መመስረት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሸዋ የተባለው ክልል ሀሳብ ጥሩ መፍትሄ ነው፡፡ ያኔ ሁሉም ነገር ባለቤቱን ያገኛል፡፡ እየተፈናቀለ ያለውም የሸዋ ሕዝብ የሆነው ደሀ እንጂ አርሲ አደለም፡፡ አዲስ አበባም ለመስፋፋትም ሆነ ልማቷን በተሳካ ሁኔታ ለመምራት ሸዋ ታስፈልጋታለች፡፡ የሸዋ ይህን ይፈልጋል፡፡ 26 ዓመት ዋና ሰለባ የሆነው የሸዋ ሕዝብ ነው፡፡ ጉራጌው ከንግዱ፣ አማራውና ኦሮሞው ቀድሞ ገዥዎች በሚል፡፡ ኦሮሞውን በጎበና ዳጬ አማራውን በሚኒሊክ ሥም ብዙ ደርሶበታል፡፡ አዎ እንኳን ሸዋ ኢትዮጵያም የጎበናና የሚኒሊክ ነች! እነሱ አንድ ያደረጓት አገር ነች ዛሬ ባንዳዎችና ቅጥረኞች እያፈረሷት ያሉት፡፡ ሸዋ ክልል ሲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድ ይሆናል፡፡ ሸዋ በመልካምድሯም በሕዝብ አሰፋፈሯም  ሁሉንም ነችና፡፡ ይህ ሀሳብ ይጠንክር፡፡ ቴዲም ዘፈንህን አሻሽል፡፡ እኛ ወያኔ በአወጣችልን ሥም መጠራት አንፈልግም፡፡ ሲጀምር አማራና ኦሮሞ ምናምን ተብለን መጠራት የማንፈልግም ያልሆንም ሚሊዮኖች ነን፡፡ የሚሰማው ግን የዘረኞቹ ሆኖ እንጂ፡፡ ይሄ 9 ያለበት የመለስና የሌንጮ ድርሰት አስጠንቁለው ነው መሰለኝ፡፡ አንቀጽ 39  ምንድን ነበር የሚለው;  የአዲስ አበባ ከኦሮሚያ ጋር የኪራይ ውሉ አንቀፅ 49 መሆኑ  ነው;

አመሰግናለሁ

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ! አሜን

ሰርጸ ደስታ

No comments:

Post a Comment