Wednesday, May 3, 2017

ጀርመን በኢትዮጵያ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ጠየቀች


(ቢቢኤን ዜና) በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ጀርመን ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ አቀረበች፡፡ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲግማር ጋብርኤል፣ ትላንትና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ከሌሎች የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተጨማሪም፣ በመንግስት ላይ ቅሬታ ያላቸው ወገኖች፣ ጥያቄአቸው በተገቢው መንገድ መፈታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሳና ከሁሉም በላይ ፖለቲካዊ ለውጥ ለማድረግ የገባውን ቃል እንዲተገብር ጠቅላይ ሚንስትሩን በድጋሚ አጥብቀን ጠይቀናል፡፡›› ያሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲግማር ጋብርኤል፣ በመንግስት በኩል በደል ደርሶብናል ብለው የሚያምኑ አካላትም፣ ቅራኔያቸው በአግባቡ ይፈታ ዘንድ ለመንግስት ጥያቄ ማቅረባቸውን ውጭ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል፡፡ የውጭ ኢንቨስትመን ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የሚችለው በሀገሪቱ የተረጋጋ ሁኔታ ሲኖር መሆኑን ያስረገጡት የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በአሁን ሰዓት በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ ግን ምቹ አለመሆኑን ለመንግስት ባለስልጣናት ገልጸውላቸዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከመንግስት ባለስልጣናት በተጨማሪም ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር የተወያዩ ሲሆን፣ ውይይታቸውም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ እና በመሰል ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ነበር፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት እንዳለበት አጥብቀው ለመንግስት ባለስልጣናት መግለጻቸውን የተናገሩት ሲግማር ጋብርኤል፣ በሀገሪቱ አስታራቂ የሆነ ፖለቲካዊ ድባብ እንዲፈጠርም ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ይፋ ተደርጎ ለስድስት ወራት ከቆየ በኋላ፣ በድጋሚ በመጋቢት ወር ለአራት ወራት እንዲራዘም በተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተነሳ በርካታ ንጹኃን ዜጎች መገደላቸው ይታወቃል፡፡ የታሰሩም በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment