Sunday, May 7, 2017

በሚሊዬን የሚቆጠሩ የሶማሊያ ህጻናት ሞት አፋፍ ላይ መሆናቸውን ተመድ ገለጸ





በሶማሊያ በሚሊዬን የሚቆጠሩ ህጻናት አደገኛ የምግብ እጥረት ላይ እንደሚገኙ ተነገረ፡፡ በቁጥር 1.4 ሚሊዬን የሚሆኑት እነዚሁ ህጻናት፣ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የማያገኙ ከሆነ፣ ህይወታቸው ሊቀጭ እንደሚችልም ስጋት አሳድሯል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት አድን ድርጅት የሆነው ዩኒሴፍ፣ 1.4 ሚሊዬን የሚሆኑት ህጻናት፣ እጅግ በከፋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል፡፡
ድርጅቱ እንደገለጸው ከሆነ፣ ካለፈው የፈረንጆቹ ዓመት መጠናቀቂያ ወዲህ ባሉ ጊዜያት ያለው የተጎጂ ህጻናት ቁጥር በእጅጉ ያሻቀበ ሲሆን፣ ጭማሪውም በ50 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ከነዚህ ህጻናት ቁጥር ውስጥ እጅግ በባሰ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት ደግሞ 275 ሺህ ህጻናት ሲሆኑ፣ ህጻናቱ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ካላገኙ ህይወታቸው እንደሚያልፍ ድርጅቱ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ከድርቁ በተጨማሪም ሌላ ስጋት የሆነው ጉዳይ የኮሌራ በሽታ ሲሆን፣ በዚሁ በሽታም የሰዎች ህይወት ያልፋል ተብሎ ተሰግቷል፡፡
ሶማሊያ ለገጠማት ሀገራዊ ቀውስ መቋቋሚያ የሚሆን ገንዘብ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡ ድርጅቱ እንዳለው ከሆነ፣ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቋቋም ቢያንስ 720 ሚሊዬን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ የተገኘው ገንዘብ ግን 415 ሚሊዬን ዶላር ብቻ መሆኑን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ማለትም በ2011/12 በሶማሊያ በደረሰው የድርቅ አደጋ፣ ከ260 ሺህ በላይ ሰዎች ማለቃቸው ይታወቃል፡፡

No comments:

Post a Comment