Thursday, May 18, 2017

ተስፋዬ ገ/አብ “የሚዲያ ያለህ” እያለ ነው!



ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
  • ለተስፋዬ ዕድል መስጠት ሬዲዮ RTLM መሆን ነው
የኢትዮጵያ ስም ሲጠራ፣ ከፍ ከፍ ሲል “የዘር ወባው” የሚነሳበት ተስፋዬ ገ/አብ አሜሪካ ገብቶ የሚያናግረው ሚዲያ በማጣቱ “በሚዲያ ረሃብ” እየተሰቃየ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ በክፉም ይሁን በመልካም ከሚዲያ መገለል የማይወደው ተስፋዬ “ሻዕቢያን የሚያጋልጥ መጽሐፍ ጽፌአለሁና አናግሩኝ” እያለ በዳያስፖራ ያሉትን ሚዲያ እየለመነ፣ በራቸውን እያንኳኳ መሆኑ ተነግሯል – በተለይ የተንቀሳቃሽ ምስልና (TV and YouTube) የሬዲዮን፡፡ ዛጎል እንደዘገበው ከሆነ እስካሁን ዕድሉን የሰጠው የለም፡፡
ተስፋዬ ከዚህ በፊት እየጻፈ የሚያወጣቸው መጣጥፎች እንደዱሮው ተነባቢነት ካጡ ሰነባብተዋል፡፡ የኦሮሞም ጽንፈኞችም እንደፈለጉ ሲጠቀሙበትና እሱም በተራው ሲጠቀምባቸው ቆይቶ አሁን ከእርሱ “የተሻሉ” አግኝተው ትተውታል፡፡ በርካታ እርሱን የሚተኩ በዘረኝነት የተከተቡ የኦሮሞ ጽንፈኞች (ያውም እንደ ተስፋዬ “ሰልባጅ” ሳይሆኑ ኦሪጂናል ዘረኞች ስለተገኙ)፤ ሚዲያውንም እስከሚበቃቸው ስለተቆጣጠሩትና እርሱ የሚመጻደቅበትን ኦሮሚኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያደረጉ በመሆናቸው ተስፋዬ “አሮጌ ስልቻ” ሆኗል፡፡ ከዚህም አልፎ ከአማርኛ ጋር ጨምረው ተስፋዬ ሲናገርም ሆነ ሲነገር የሚነስረውን እንግሊዝኛ አቀላጥፈው የሚያንበለብሉ በመሆናቸው ባሁኑ ጊዜ የተስፋዬ ዋጋ የተመጠጠ ሸንኮራ ወይም ፊልተሩ የቀረ የተጨሰ ሲጋራ ሆኗል፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ግን ዘመን ተገልብጦ አሁን የሚዲያ ባለቤት ሲሆኑ “ዝምታቸውን” አስጩኾ “የጡት ጉማጅ” ሃውልት ባለቤት ያደረጋቸውን “ወዳጅ” መዘንጋታቸው ነው፡፡
ተስፋዬ ግን ሞራል የሌለው በመሆኑ የትም ቢጠራ፣ የትም ተናገር ቢባል፣ … ያደርገዋል፡፡ ዓላማው የውይይት አጀንዳ መሆን ነው፡፡ በተለይ ሰሞኑን በድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያዊነት አዲስ ቀለም አበጅቶ የአበባው ሕብረቀለማዊነት መታየት ስለጀመረ ይህንን ማፍረስ የተስፋዬ ተቀዳሚ ዓላማ እንደሚሆን የበፊት ታሪኩን መመልከት ብቻ በቂ ይሆናል፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለተስፋዬ ዕድል ሰጥቶ ቃለምልልስ የሚያደርግለትን ሚዲያ የሩዋንዳውን ፍጅት እንዲቀጣጠል ካደረገው ሬዲዮ RTLM (Radio Télévision Libre des Mille Collines) ለይቶ እንደማያይ ግልጽ በሆነ ቋንቋ ለማስቀመጥ ይወዳል፡፡
በሩዋንዳ በተካሄደው የዘር ማጥፋት (ጄኖሳይ) በዋንኛነት ከሚጠቀሱት መካከል የሚዲያውን ኃይል በመጠቀም RTLM (Radio Télévision Libre des Mille Collines) በተሰኘው የሬዲዮ ማሰራጫ አማካኝነት የተነዛው የዘር ጥላቻ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህንን ተግባር ሲፈጽሙና ሁቱዎች በቱትሲዎች ላይ እንዲነሱ ያደረገውና ቱትሲዎችን “በረሮ” (“cockroaches”)  እያለ በመጥራት “እንዲገደሉ” በሬዲዮው አማካኝነት “ትዕዛዝ” ሲሰጥ የነበረው ፌሊሲዬን ካቡጋ (Félicien Kabuga) ዋነኛ ተጠቃሽ ነው፡፡ የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በሩዋንዳ ዘር ማጥፋት ዙሪያ ባደረገው ጥናት ካቡጋ እና የሬዲዮ ጣቢያው ልፈፋ ለ51ሺህ ሰዎች መገደል ቀጥተኛ ተጠያቂ አድርጓል፡፡ ይህም በአጠቃላይ ከተጨፈጨፉት ሰዎች ውስጥ 10በመቶ መሆኑን ጥናቱ ጠቁሟል፡፡
ተስፋዬ ማለት ካቡጋ ነው! መጽሐፎቹና መጣጥፎቹም RTLM ሬዲዮ ናቸው፡፡ ተስፋዬ በሚዲያ ረሃብ ጠውልጎ መሞት አለበት፡፡ ይልቅ የጻፋቸው መጽሐፎችና ያወጣቸው መጣጥፎች ለዜጎች መጨራረስ ምክንያት እንደሆኑ የራሱን ማስረጃዎች በመጥቀስ ለፍርድ የሚቀርብበት ሁኔታ ቢመቻች ነው ለአገርና ሕዝብ የሚበጀው፡፡ አሜሪካ ለዚህ ዓይነት ሕጋዊ አሠራር የተመቻቸች አገር ናት፤ በቅንጅት መንቀሳቀስ ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ምናልባትም ወደ አሜሪካ መምጣቱ ሳያውቀው በአንገቱ ላይ ገመዱን እያጠበቀ እንዳይሆን! የመናገር ነጻነት ማለት ከተጠያቂነት ነጻ መሆን ማለት አይደለም!
ዛጎል ያወጣው ዜና እንዲህ ይነበባል፡፡
ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ – ተስፋዬም ተነሳ
ተስፋዬ ሲያትል ግብቶ የሚዲያ ረሃብተኛ ሆነ!!
የጋዜጠኛ ማስታወሻ የሚለውንና “የግል የሚለውን ማስታወሻ” ገጣጥሞ ለንባብ ካበቃ በኋላ ዲያስፖራው አንግሶት ነበር። በፓልቶክ፣ በሬዲዮ፣ በ“ቲቪ/ዩቲብ” … በተለያዩ ሚዲያ አክተር ሆኖ ሙገሳ ጠግቧል። “የቡርቃ ዝምታ” በሚለው የፍጅት አቀጣጣይ መጽሃፉ ጥርስ የነከሱበት ከጅምሩ ቢቃወሙትም የሚሰማቸው አልነበረም። በኢትዮጵያኖች ሚዲያ፣ ኢትዮጵያ ላይ መርዝ እየረጨ ሲጨበጭብለት ያበዱ፣ የተቃጥሉና የተሟገቱ ብዙ ብለው እንደነበርና የሃሳብ መለያየት እስከሚከሰት ድረስ ግጭት ተነስቶም ነበር።
በደጋፊዎቹና ከልብ በሚጠሉት መካከል ያለውን ፍትጊያ “ኦሮሞን” በመንተራስና ግንቦት ሰባትን በ“መደገፍ” ያለፈው ተስፋዬ ገብረአብ (ገብረ እባብ አንዳንዶች እንደሚጠሩት)፣ በስደት ከሚኖርበት ኔዘርላንድስ የወጣበት መረጃ ሊስተባበል በማይችል መልኩ ከሚዲያና እንዳሻው ከሚዘንጥበት ማህበራዊ ገጾች ገፍትሮ እንደወረወረው በጊዜው ብዙ ተብሎበታል። የአሁኑ አመጣጡ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ሲነሳ መሆኑ አነጋግሪ ሆኗል።
በተለይም ከኤርትራው መሪ ኢሳያስ አፈወርቅ ጋር የሚያደርጋቸውን የጽሁፍ ምልልሶች ኮፒ በማደረግ የኔዘርላንዱ ነዋሪ ይፋ ካደረገው በኋላ፣ ካለፈው የቡርቃ ዝምታ መጽሃፉ ጋር ተያይዞ ሊከሰስ እንደሚገባው የሚጠይቁ ተነስተውበት ነበር። እነዚህን ሰዎች ጠቅሶ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ “ተስፋዬ ማለት ካቡጋ ነው፤ የቡርቃ ዝምታ ደግሞ የካቡጋ ሬዲዮ RTLM ነው” ብሏል። አያይዞም ያነጋገራቸውን ጠቅሶ “ሆላንዳዊው” ተስፋዬ እንደ ካቡጋ “ወደ አባት አገር” በመሄድ ከመሸሸጉ በፊት ውጤታማ ሥራ መሰራት ያለበት አሁን ነው ይላሉ” ሲል ዘግቦ “አክትቪስት ነን” ለሚሉት ሁሉ ህዝብን ለፍጅት በማነሳሳት ወንጀል እንዲከሰስ አሳስቦ ነበር። እንደተባለው ይሁን በሌላ ምክንያት ተስፋዬ አገሩ ገብቶ የኢንተርኔት ሱቅ በመክፈት ሲሰራ እንደነበር ከዚያው አካባቢ የመጡና የሚያውቁት ይናገራሉ። ተስፋዬ አስመራ እያለም ከሕገወጥ የሰው ዝውውር (human trafficking) ጋር በተያያዘ ታስሮ እንደነበርም ስለጉዳዩ የሚያውቁ አመልክተዋል።
ተስፋዬ በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ ሲያትል ይገኛል። እዚያም ብዙ እንደሚቆይ ከመናገሩ ውጪ ከሻዕቢያ ጋር ስለመለያየቱ ያለው ነገር የለም። ይልቁኑም አሁን እያሳተመ ያለው ታሪክ የሻቢያን “ምስጢር” የሚያጋልጥ እንደሆነ መናገሩን ዜናውን ያቀበሉን ጠቁመዋል። ጥሩ የመጻፍና የመፈጠር ችሎታ ያለውን ተስፋዬን ኮሎኔል ከማል ገልቹ “የተወለድኩባትንና ያደኩባትን አርሲን ከኔ በላይ የሚያውቅ ሆኗል” ሲሉ አስተያየት እንደሰጡበት አይዘነጋም። ተስፋዬ አሁን እያሳተመ ያለው መጽሃፍ እንዲተዋወቅለት የኢትዮጵያኖችን ሚዲያና ለመጠቀም ቢፈልግም እንደፈለገው ሊሳካለት እንዳልቻለ በዚሁ ጉዳይ ያወያያቸው ለዛጎል አመልክተዋል።
ኢሳትን ለማስታወቂያነት ቢመርጥም እንዳልተሳካለት የጠቆሙት ምንጮች፣ ኢሳት ተስፋዬን ቃለ ምልልስ አድርጎ የመጽሃፉን ማስታወቂያ ከሰራ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደሚነሳበት ገሃድ በመሆኑ ሊሳካለት እንደማይችል ተናገረዋል። ሌሎች የሚዲያ ተቋማትንም ለማነጋገር የሞከረ ሲሆን አንዳንዶቹ ጥያቄውን አንቀበልም ባይሉም እንደወትሮው እጃቸውን እንዳልዘረጉለት ነው የተሰማው።
በሌላም በኩል ኦነግን ሻቢያ እንዳፈራረሰው ሁሉንም አብጠርጥሮ የተናገረውን ሰናይን ለማስተባበብል ሆን ተብሎ የተዘጋጀና የሻዕቢያን እውቅና ያገኘ መጽሃፍ እንደሆነ ግምት ያላቸውም አሉ። ተስፋዬ ሻዕቢያን ሙሉ በሙሉ የሚያጋልጥ መጽሃፍ ለንባብ ካበቃ፣ የኤርትራን ምድር እንደማይረግጥ ግልጽ በመሆኑ “እመለሳለሁ” ማለቱ በመጽሃፉ ላይ ከወዲሁ ጥርጣሬን ፈጥሯል። ተስፋዬን በወጉ የሚረዱት እንዳሉት “አሁን ወቅቱ ኢትዮጵያዊነት የተነቃቃበት በመሆኑ ሃሳብ ለማስቀየርና ሌላ አጀንዳ ለማስቀመጥ ነው” ባይ ናቸው። በዚሁ መነሻ የሚዲያ ረሃቡን ማጠናከርና ፊት መንሳት አስፈላጊ እንደሆነ ያሰምሩበታል።

No comments:

Post a Comment