Sunday, May 7, 2017

በማዕከላዊ ያለው የወጣት አወቀ አባተ የእጅ ጣቶች ተሰባብረዋል



(ብራና ሚዲያ) የለውጥ ሐዋሪያ በሆኑት በዐማራ ወጣቶች ላይ የሚደርሰው ቶርቸር እጅግ ጭቃኔ የበዛበትና ለሚሰማውም አስደንጋጭ ነው፤ በአቶ ማሙሸት አማረ በሚመራው መኢአድ የአዲስ አበባ ቀጠና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና በአገር አቀፍ የላዕላይ ምክር ቤት አባል በሆነው በወጣት አወቀ አባተ ከጳጉሜ 5 ቀን ጀምሮ በማዕከላዊ በደረሰበት ቶርቸር የአካል ጉዳተኛ መሆኑን አብረውት ታስረው በነበሩ ሰዎች በኩል የወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወጣት አወቀ አባተ በወይዘሪት ንግሥት ይርጋ የሽብርተኝነት የክስ መዝገብ ሥር ከተከሰሱት ወጣቶች መካከል አንዱ ሲሆን የተመሠረተበትን የፈጠራ ክስ እጣቶቹ በመሰበራቸው ምክንያት መርማሪዎቹ የተሰበሩ እጣቶቹን ይዘው እንደፈረሙበት ነው የተነገረው፡፡ በወጣት አወቀ አባተ ላይ እስካሁን ድረስ የትግሬዎች የቶርቸር ሰለባ ቢሆንም ከመስከረም 3-18 ቀን 2009 ዓ.ም. በየቀኑ የደረሰበት ስቃይ ለአካል ጉዳቱ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
ወጣት አወቀ በአሁኑ ሰዐት ከሁለቱም እጆቹ እጣቶች መሰባበር በተጨማሪ የጀርባው ሰርሰር (ስፓይናል ኮርድ) በብረት በደብደቡ ምክንያት በትክክል መራመድ አይችልም፤ የግራ ጆሮው መስማት ተስኖታል፡፡ ወጣት አወቀ ሽንት በሚሸናበት እና በሚጸዳዳበት ጊዜም ከፍተኛ መጠን ያለው ደም እንደሚፈሰው ነው የነገሩን፡፡ ወጣት አወቀ በአፋጣኝ ሕክምና ካላገኘ በሕይወት የመቆየት እድሉ አሳሳቢ እንደሆነ ነው መረጃውን የሰጡን ሰወች የነገሩን፡፡
ወጣት አወቀ በአዲስ አበባ አየር ጤና አካባቢ የራሱ ጣውላ ቤት የነበረው ቢሆንም እሱ በመታሰሩ ቤተሰቦቹም እንዳያስቀጥሉት ጫና በመኖሩ ምክንያት ድርጅቱ ተዘግቷል፡፡ ወጣት አወቀ ቀደም ባሉት ዘመናት ከሁሉም የዐማራ አካባቢዎች በተለይ ደግሞ የመኢአድ አባላት ከሁሉም አካባቢ በቃሊቲ፣ ሸዋ ሮቢትና ዝዋይ ሲታሰሩ ቤተሰቦቻቸውንና እስረኞችን በገንዘብና በቁሳቁስ በግንባር ቀደም ሲረዱ ከነበሩት መካከል አንዱ ነው፡፡ ሆኖም አሁን ላይ የወጣት አወቀ ቤተሰቦች በአሁኑ ሰዐት ችግር ላይ መሆናቸውን ጭምር ነው የትግል ጓዶቹ የነገሩን፡፡
ወጣት አወቀ አባተ አሁንም ድረስ በዐማራነቱ እየደረሰበት ያለው ስነ ልቦናዊ ጉዳት በአካል እየደረሰበት ካለው ሁሉ የሚልቅ ነው ብለውናል፡፡ መረጃውን የሰጡን ሰዎች በወጣት አወቀ ላይ የደረሰው ግፍ በጽሑፍ የማይገለጽ ብዙ ጉዳይ እንዳለውና የዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ሕይወቱን ለማትረፍ ጥሪ እንዲቀረብ ሁሉ ተናግረዋል፡፡

No comments:

Post a Comment