Monday, May 8, 2017

የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታና የባንዳዎች ዕዳ!



በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
ረዥሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ከነፍጥ፤ ከሞፈርና ከመስቀል ጋር ተዛማጅነቱ ፍፁም ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ይመስላል አባ ዳኘው (ዳግማዊ አጤ ምኒልክ) የአድዋ ጦርነት  ዘመቻ ዝግጅት ላይ “… ሀገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖት የሚለዉጥ ጠላት…” መጥቷልና ከርስትህና ከሚስትህ ሳትነቀል የሚል ይዘት ያለው አዋጅ በወቅቱ እንዲነገር ያደረጉት፡፡  በጊዜ ሂደት ሀገሪቱ ከታሪኳ መድረክ “መስቀል”ን ገለል ብታደርግም ነፍጥና ሞፈር (ርስት) የአገሪቱ ህያው አምሳያ የታሪክ አካል ሆነዉ ቀጥለዋል፡፡ ወራሪ ኃይል በመጣ ቁጥርም እነዚህ የአገሬው ማታገያ አብይ አጀንዳዎች ሆነው ሲነሱ ኖረዋል፡፡
የነጮቹ ቅርጫ የሆነችው አፍሪካ በቅኝ ግዛት ክፉ ዕጣ ውልቅልቋ ሲወጣ፤ ኢትዮጵያ አድዋ ላይ በጀግኖች አባቶቻችን ተጋድሎ ሉአላዊነቷን ማስከበር ችላ ነበር፡፡ ፋሺስት ጣሊያንም ሽንፈቷን በእልህና በቁጭት ለመቀበል አርባ ዓመት መጠበቅ ነበረባት፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ በቀድሞ ድሏ እየተኩራራች ይህ ነው የሚባል አቅም ሳትገነባ አራት አስርታት ዓመት ተሻገረች፡፡ ያውም እንደ “ሰገሌ”፤ “አንቼም” ባሉ ትልልቅ የርስ በርስ ጦርነቶችና በሥልጣን ሽኩችዎች እየታመሰች ዘመን ተሻጋሪ ጠላቷን ጣሊያንን ዘንግታ፡፡
የፋሺስት መሪ ሙሶሊኒ ኢትዮጵያን ለመውረር የወሰነበትን ወቅት ይህ ነው ብሎ በሙሉ መተማመኝ መናገር ቢያዳግትም ከ1924 በኋላ እንደሆነ ብዙዎቹ የታሪክ ፀሐፊዎች ይስማማሉ፡፡ ሙሶሊኒ በአውሮፓ መድረክ ይከተል የነበረው የመስፋፋት ፖሊስ ከከሸፈበት በኋላ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ ማዞር ግድ ሳይሆንበት እንዳልቀረ የታሪክ ፀሐፍቱ ይስማማሉ፡፡ በህዳር 26/1927 ዓ.ም የተከሰተው የወልወል ግጭት ባንድ መልኩ ኢትዮጵያ ካጎራባች ቅኝ ግዛቶች ጋር ያሏት በቅጡ ያልተከለሉ ድንበሮች ውጤት ነው፡፡ (በይበልጥ ፓንክረስትንና ባህሩ ዘውዴን ያጤኗል)
ከወልወል ግጭት በኋላ መስከረም 22/1928 ዓ.ም የጣሊያን ጦር የመረብ ወንዝን ተሻግሮ በሦስት መስመር በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ከፍተ፡፡ የጥቃቱ አንዱ ዓላማ ከአርባ ዓመት በፊት የሃፍረት ማቅ የተከናነበበት አድዋ ነበረች፡፡ ሁለቱ ሌሎች የጥቃቱ ዓላማዎች “እንጢቾ” እና “አዲግራት” ነበሩ (በይበልጥ ዘውዴ ረታን፣ ባህሩ ዘውዴንና ፓርክረስትን ያጤኗል)
በወቅቱ የምስራቅ ትግራይ ገዥ የነበሩት ደጀዛማች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳ በግንባር ቀደምነት ለፋሽስት ጣሊያን ጦር ከነ ሰራዊታቸው አደሩ (ባንዳ ሆኑ)፡፡ የኢትዮጵያ የሰሜን ጦር በሦስት ረድፍ የተሰለፈ ነበር፡፡ በስተምዕራብ በራስ እምሩ ኃይለሥላሴ የሚመራው የጎጃምና የበጌምድር ጦር በስተምስራቅ፣ በጦር ሚኒስትሩ በራስ ሙሉጌታ ይገዙ የሚመራው የንጉስ ነገስቱ ጦር፤ በመሀል ደግሞ በራስ ሥዩም መንገሻና በራስ ካሳ ኃይሉ የሚመራ ጦር ነበር፡፡ በዚህ የኃይል አሰላላፍ ለጊዜውም ቢሆን የኢትዮጵያ ጦር ሽንፈትን መቀበል ዕጣዉ ሆነ፡፡
በተለምዶ የማይጨው ጦርነት የሚባለው የ1928ቱ ጦርነት በሽንፈት ለመደምደሙ የፋሽስት ጣሊያን የኃይል አሰላለፍና ወታደራዊ አቅም ከኢትዮጵያ የተሻለ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን በሰሜን ኢትዮጵያ የነበሩ የትግራይ መሳፍንቶች ከነጦር ሠራዊታቸው ለፋሽስቱ ጣሊያን በማዳራቸው እንደሆነ ብዙ የተባለለት ጉዳይ ነው፡፡
በሰሜኑ ግንባር የመጨረሻ ጦርነት የሆነው የማይጨው ጦርነት መጋቢት 24/1928 በሽንፈት ከተደመደመ በኋላ የፋሽስቱ ጦር አዲስ አበባ ለመግባት አርባ ቀናት ያህል እንኳን አልወስደበትም ንጉሠ ነገሥቱ ሚያዚያ 24/1928 ዓ.ም አገር ጥለዉ ሲሰደዱ ጣሊያን ሚያዚያ 27/ 1928 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ገባ፡፡
ጣሊያኖች የምስራቅ ትግራይን ገዥ ደጃች ኃይለሥላሴን በገንዘብ በገዙበት አኳኋን አንዳንድ ባላባቶችን ከየጁና ከአዘቦ አካባቢ ለማባበል ሞክረዋል፡፡ ይልቁንም እነዚህ ጥቂት ባላባቶች ከጦር ሚኒስትሩ ከራስ ሙሉጌታ ጋር በነበራቸው ቅራኔ ምክንያት አንዳንዶቹ ለፈሽስቱ ጦር ማበር ያዙ፡፡ የቅራኔው ምክንያት “ራስ ሙሉጌታ ቆቦንና አዘቦን አቃጠሉ፤ ሕዝቡን ዘረፉት” በሚል ነበር እንደ የታሪክ መጻሐፍት ይገልፃሉ፡፡ ራስ ሙሉጌታ የራያን፤ የየጁንና የአዘቦን ተወላጅ በውጊው ግንባር ከመሰለፍና ከሞት አንዱን እንዲይዙ ምርጫ ሰጥተዋቸው ነበር ባላባቶቹ ግን ለጣሊያን ማዳርን ምርጫቸው አደረጉ፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያ ትግራዋይ ባላባቶች ለጣሊያን ማደርና መተባባር ለፋሽስቶች በፍጥነት ወደ አዲስ አበባ መገስገስና ለአምስት ዓመት ቆይታቸው እገዛ አድርጎላቸዋል፡፡ በወቅቱ  ትግራዋይ ባንዶች በርከት ያሉ ነበር በሚል እንጅ ለባዕድ አገዛዝ ያደሩ ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢ ተወላጆችም ይገኙ ነበር፡፡ በአንፃሩ ከትግራይ እንደ ራስ መስፍን ረዳ ያለ ጠንካራ አርበኛ እንደነበር መዘንጋት የተገባ አይደለም፡፡ ጎጃም ላይ ዝነኛዉ አርበኛ በላይ ዘለቀና መሰሎቹ በየአዉደ ዉጊያዉ እንዳልተሰለፉ ራስ ኃይሉ ተክለሃይማኖት በተቃራኒዉ ተሰልፈው እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ወቅት ለባዕድ አገዛዝ አድረው (ባንዳ ሆነው) ከጣሊያን መንግስት ደመወዝ ተቀባዮች የነበሩ መሳፍንቶችና መኳንንቶች ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ስምደመወዝ
ራስ ኃይሉ40,874
ራስ ስዩም22,900
ራስ ጉግሳ25,000
ራስ ጌታቸው7,000
የአውሳሉ መሀመድ አንፋሪ15,000
ሱልጣን አብዱላሂ አባጅፋር8,000
ሱልጣን አባጆቢር አብዱላ8,000
ደጃዝማች ሆሳዕና ጆቴ15,000
ደጃዝማች ዮሓንስ ጆቴ15,000
ሼክ ኤል ሆጄሌ25,000
ደጃዝማች ታየ1000
ራስ እምሩ1000
ደጃዝማች አያሌው ብሩ16000
ምንጭ፡- Alberto  sbacchi (57) (መስፍን ወ.ማሪያም፤ አዳፍኔ ገጽ 152)
ፋሺስት ጣሊያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር የነበራቸው ግንኙነት ጥሩ ሊሆን ስላልቻለ ፓትሪያርኩ አቡነ ቄርሎስ ወደ ሀገራችው ወደ ግብጽ ተመለሱ፡፡ ፋሺስቶች ክርስቲያኑንና እስላሙን ለማጋጨት በነበራችው ፍላጎት የእስልምና ጠባቂና አስፋፊ ነን ማለት ያዙ፡፡ በዚህ ሁኔታ ጥቂት ሰዎችን ብቻ ሲያታልሉ፤ አብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያዊ በተንኮላቸው መረብ ውስጥ አልገባላቸውም፡፡ ይልቁንም የሃይማኖት አባቶች በጣሊያን ላይ የነበራቸው አቋም እየጠናከረና እየመረረ   ሄደ፡፡ እንደ ብጹዑ አቡነ ጴጥሮስ ያሉት ታላላቅ የሃይማኖት መሪዎች እንደ ደጀዝማች ዑመረ ሰመተር ያሉ ጀግኖች ሰማዕትነትን የተቀበሉት በአምስት ዓመቱ የጨለማ ዘመን ነበር፡፡
ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ውስጥ በቆዩባቸው አምስት ዓመታት የፍዳና የጭንቅ ዘመናት ለፓስታሹታ ለማክሮኒ ለፉርኖና ለመሳሰለው ዕለታዊ ጥቅም የወገኖቻቸውንና አርበኞቻችን እንቅስቃሴ እየተከታተሉ የሚጠቁሙና የሚያሳስሩ የሚያስገድሉ ባንዶች ነበሩ፡፡ ከአንዳንድ ከሶላቶዎች ጋር የወሲብ ግንኙነት የፈጠሩ ሴቶች፤ ባሎቻቸውን ሳይቀር አጋልጠው ለመከራ የዳረጉ፤ የቀበሩትን የጦር መሣሪያ እያስቆፈሩ ለጠላት የሰጡ፤ የትዳር ጓደኞቻቸውን ያሳሰሩ ነበሩ፡፡ ጎረቤቶቻቸውን፣ አበልጆቻቸውን ወዘተ በማስያዝ ሽልማት፣ ጉርሻና ደርጎ ሲቀበሉ የነበሩ አልታጡም፡፡ የራስ ካሣ ሦስት ልጆችና የ80 ዓመቱ አዛውንት ደጃች ባልቻ መስዋዕት የሆኑት፤ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት እንደችቦ የነደዱት በዚህ መልክ ነበር፡፡
ግራዚያኒ በወቅቱ በነበሩት ፊውዳል መኳንንትና መሳፍንት ለመቀጠቀም የፈለገው አገሪቱ ውስጥ በእነሱ ተጽዕኖና ርዳታ በደንብ ሰርጎ ለመግባት እንዲመቸው ነበር፡፡ በዚህ መካከል እንዳንዳቹ መሳፍንትና መኳንንት ባንዳዎች በአፄ  ኃይለ ሥላሴ ዘመን ያጡትን ስልጣንና ገናናነት ፋሽሲቱ የጣሊያን መንግስት እንደሚሰጣቸው ገምተው ነበር፡፡ ቀዳሚ ተስፈኞችም የትግራይ መሳፍንቶች ደጃች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳና ራስ ሥዮም መንገሻ ቀደም ከነበራቸዉ ማዕረግ ይበልጥ ከፍ የማለትና የንግሥናውን ቦታ የመቆናጠጥ ምኞት ነበራቸው፡፡ የጎጃሙ ራስ ኃይሉ ተክለሃማኖትም አይረሴው ባንዳ ነበሩ፡፡
በአንጻሩ የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በማይጨው፣ በሽሬ፤ በተምቤን… ጦርነት ላይ የዋሉትን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አርበኞችን እንኳን ብንተው ጣሊያኖች ከማይጨው ጦርነት በኋላ ወደ መሐል አገር እንደተንቀሳቀሱ “ዱር ቤቴ” ብለው ህዝባዊ ሠራዊት እያስከተሉ የሸፈቱ በርካታ ወገኖች ነበሩ፡፡ ከትግራይ ብቸኛው ፊታውራሪ መስፍን ረዳ፤ ከበጌምድርና አካባቢው ራስ ውብነህ ተሰማና ቢትውደድ አዳነ፤ ከጎጃም ቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ፣ በላይ ዘለቀና ራስ ኃይሉ በለው፤ከሸዋ ራስ አበበ አረጋይ፣ መስፍን ስለሺ ፀሐይ ዕንቁሥላሴ፤ የበሼ ቤተሰቦች ደጃች ተሾመና አበበ  ሽንቁጥ፤ ከደቡብና ምዕራብ እነራስ ደስታ ደምጠው፣ ገረሱ ዱኪ፣ መኮንን ደመሰው፤ ከወሎ እነ ኃይሉ ከበደ፣ ወሰን ኃይሉ፣ ከሐረርጌ እነ ደጃች ዑመረ ሰመተር …. ወዘተ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸዉ ጀግና አርበኞችን እያስተባበሩ ጠላትን እንደ ንፍፊት ወጥረውት ቆዩ፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ውድ ልጆች የካቲት 12/1929 ዓ.ም በማርሻል ግራዚኒያ ላይ የቦምብ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የፋሽስቱ ጭካኔ እየበረታ በመሄዱ የአርበኝነት ተጋድሎም እየተቀጣጠለ  እስከ ድል ጫፍ  ድረስ ቀጠለ፡፡
በአምስት ዓመቱ የአርበኝነት ተጋድሎ ወቅት የ“ጥቁር አንበሳ” አርበኞች ኅብረት የበረታ ትግል የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በየጊዜው የተነሱባት የውጪ ወራሪ ኃይሎች በህዝብ የተባበረ ክንድ ድባቅ መምታት ችላላች፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታ ከድል በኋላ በነበሩ ጊዜያት በቅጡ የታሰበና የተከበረ ነበረ/ነው ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡
በተለይም አፄ ኃይለ ሥላሴ ከስደት ከተመለሱ በኋላ በዘረጉት የአስተዳደር መዋቅር ግንባር ቀደም አርበኞችን በማግለል ብሎም በማሰርና በመቅጣት በወረራ ጊዜ ለባዕድ አገዛዝ ታዛዥ የነበሩ ባዶችን ወደ ስልጣን ከፍታ ሲስቡ ታይቷል፡፡ በ1937 ዓ.ም  በላይ ዘለቀን በስቅላት፤ በ1953 ራስ አበበ አረጋይን በመረሸን የግንባር ቀደሞችን አርበኞች አሻራ ከአስተዳደራዊ መዋቅራችው እየጠፉ የተጓዙት አፄ ኃይለ ሥላሴ የማታ ማታ መጨረሻቸው አላማረም፡፡
በርግጥ ኢትዮጵያ በአመዘኙ ታሪኳ ለደሙላትና ለቆሰሉላት ውለታ ስትመልስ አትታይም፡፡ ይልቁንስ ለባዕድ አገዛዝ ታማኝ የነበሩ ባንዶችን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁነት የኢትዮጵያ ታሪክ አንዱ ገጽታ  ነው፡፡ የአፄ ኃይሌ ሥላሴ የድህረ ነፃነት የሥልጣን ጉዞ የባንድነትን ከፍታ ይበልጥ ያሳያል፡፡ ባንድነት የኢትዮጵያ ህልውና የሚፈታተን ሀገራዊ በሽታ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
በርግጥ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም እንደሚሉት በየጦር ሜዳው ላይ ያለቀባሪ የቀሩት፣ ጅብና አሞራ የበላቸው የኢትዮጵያ ጀግኖች ድምጽ ተራሮችን እያርበደበደ ወንዞችዋን እያስጋለበ “ብድር መልሱ! ዕዳ ክፈሉ!” እያለ ያስተጋባል፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ጅግኖች ለኢትዮጵያ አፈር ማዳበሪያ ሆነው በመሞታቸው ሲመግቡን ቆይተዋል፤ በሕይወታቸው ክብርና ኩራት በመሞታቸውም ሕይወት የለገሱንን የአባቶቻችንንና የአናቶቻችንን ድምጽ ማድመጥና ከመንፈሳቸው ጋር መታረቅ አለብን!!
በየዓመቱ ሚያዝያ 27 የሚከበረው የድል ቀን በኢትዮጵያ የቀን መቁጣሪያ (ካሌንደር) ላይ ሥራ ተዘግቶ እንዲከበር ቢደረግም ትውልዱ የቀደሙ እናትና አባቶቹን የተጋድሎ ታሪክ እንዲያወቅ የሚያስችል የበዓል አከባበር አይታይም፡፡ ዕለቱም እንደአንድ ተራ የረፍት ቀን ያልፋል፡፡ በአንጻሩ አንዳች አገራዊ ፋይዳ የሌላቸው የህወሃት፣ የብአዴን፣ የኦህዴድ፣ … የምሥረታ ቀን እየተባለ በብዙ ሚሊዮን ገንዘብ የሚወጣባቸው ለወራት በዕቅድ ተይዘው የሚደገሱ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ ይደረጋል፡፡
አዲስ አበባ አራት ኪሎ አደባባይ ላይ በሚገኘው የድል ኃውልት ላይ የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥና በዕለታዊ የዜና ሽፋን የሚታለፈው ይሄው የድል በዓል፤ ትውልዱ የበዓሉን ፋይዳ በቅጡ እንዳይረዳው አድርጎታል፡፡ የፋሽስት ጣሊያን የአምስት ዓመቱ የወረራ  ዘመን በተነሳ ቁጥር የዛሬ ቁንጮ ገዥዎች (የሕወሓት አመራሮች) እንደዘዉጌ ብሄርተኝነታቸው የሚያፍሩበት እንጂ የሚኮሩበት ታሪክ እምብዛም ነው፡፡ ታሪክን በዜግነት ማዕቀፍ ሳይሆን በዘውጋዊ ማንነት ሽንሽኖ ማየት የሚቀላቸው የሕወሓት ሰዎች የኢትዮጵያዊያን የድል ቀን የሆነውን ሚያዝያ 27 በየዓመቱ በደበዘዘ መልኩ እንዲከበር ማድረግ መርጠዋል፡፡
የትግራይ መሳፍንቶች የእነ ደጃች ኃይለ ሥላሴ ጉግሳና ራስ ሥዩም መንገሻ መቼም የማይረሳ የባንዳነት ታሪክ ዕዳ ሆኖባቸው በዓሉን እንደ አንድ ተራ ዕለት ማለፍ ምርጫቸው ሆኗል፡፡ በእኛ በኩል እንደዜጋ የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታ በቅጡ እንዳልተዘከረ ይሰማናል፡፡ የአምስት ዓመቱ የወረራ ዘመን በኢትዮጵያዊያን ላይ ያደረሰው የፖሊቲካ፤ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጽዕኖዎች በሚገባ እንዳልተዳሰሰም እናምናለን፡፡
የኢትዮጵያ አርበኞች የተጋድሎ ሚና የታሪክ ትምህርት (ሥርዓተ ትምህርት) አንዱ ክፍል እንዲሆን ማደረግ፤ አርበኞችን የሚዘክር ብሔራዊ ቤተመጻሕፍት ማቋቋም፣ የአርበኞች ማህበርን ከፖለቲካ ፍላጎት በፀዳ መልኩ ማጠናከር ወዘተ ተግባራትን በአገር አቀፍ ደረጃ በማከናወን ተተኪ ትውልድ መፍጠር ይቻላል፡፡ አገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት ኃላፊነት የሚሰማው መንግስት ሊኖር ይገባል፡፡ ይሁንና “መንግስት”ነቱን የዘነጋ የቋሚ  ሽፍታና ወንበዴ ስብስብ የሆነው ህወሓት ሥልጣን ላይ አስካለ ድረስ የኢትዮጵያ አርበኞች ውለታ በተገቢ ሁኔታ ሊታወስም ሆነ ተተኪ ትውልድ ማፍራት የሚቻል አይደለም፡፡
ክብር ለኢትዮጵያ አርበኞች!!!

No comments:

Post a Comment