Friday, May 12, 2017

ጠብመንጃና አማራ ምንና ምን ናቸው? – ጋሻው መርሻ



ጠብመንጃና አማራ ምንና ምን ናቸው?
……….. ጋሻው መርሻ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ቴሌቪዥን የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን እከታተላለሁ። እውነት ለመናገር ሃገር ውሥጥ ካሉት ሚዲያዎች ለህዝብ የቀረበ ነገር በማቅረብ አማራ ቴሌቪዥንን የሚደርሥበት የለም። ጋዜጠኞቹ እሾህ ላይ ቁመውም ቢሆን ማሥተላለፍ የሚፈልጉት ነገር እንዳለ መረዳት ይቻላል። በጣቢያው ከሚተላለፉ ፕሮግራሞች መካከል “አንድ ለአንድ (የክልሉን ባለሥልጣናት በጥያቄ የሚያፋጥጥ ፕሮግራም ነው)፣ ምክር ከአበው፣ የከተሞች መድረክ እና የወጣቶች ፕሮግራም ትንሽ መሻሻል ቢደረግባቸው ለክልሉ ብሎም ለሃገሪቱ እንደ አማራጭ ሚዲያ ማገልገል፣ ለጣቢያውም የመታየት እድሉን ያሠፋለታል ብየ አሥባለው። በተለይ እንደ አድዋ ድል፣ የአርበኞች የድል ቀን የመሣሠሉትን ሃገራዊ ክብረ በዓላት የሚዘክሩበት ርቀት ይበል የሚያሠኝ ነው። ከዚህ የተነሣም ነው የትግራይ ብሄርተኞች የአማራ ቴሌቪዥንን ሃገር ውሥጥ ያለ ኢሣት ሲሉት የሚደመጠው። ያው ሃገር ውሥጥ ያሉ ጣቢያዎች ህዝባዊ ወገንተኝነታቸውን ትተው መንግሥታዊ የፕሮፖጋንዳ ማሽን እንዲሆኑ የመፈለግ ጠቅላይነት ክፉ ልክፍት።
.
ህጻናት እያለን በክረምት ከብት ሥናግድ በሠፈር እረኛ የሌላቸውን ሠወች ከብቶች ጨምረን እናግድ ነበር። ታዲያ በነጻ አይደለም። በቀን 10 ወይም 15 ሣንቲም እየተከፈለን እንጅ። ሌላው ደግሞ ከብት በምናግድበት አካባቢ ያለን ማሣ በክፍያ አረም በመንቀል፣ በመኮትኮት፣ እህሉን በማጨድ ትንንሽ ክፍያ እናገኛለን። እንዲሁም ዘመድ አዝማድ ቤተሠብ ሊጠይቅ ሲመጣ ስሙኒም ሃምሣ ሣንቲምም ይቸረናል። ሌላው ደግሞ ከበግ ጸጉር ኮፍያ ሠርተን በመሸጥ፣ ከሠኔል ወይም ግራምጣ ገሣ በመሥራት ሣንቲም እናገኛለን። ይህን ሣንቲም ታዲያ አጠራቅመን ከረሜላ አንበላበትም ወይም ለእሥክብሪቶ ወይ ለእርሣሥ አናወጣውም። ይልቁንም ሥናጠራቅም ከርመን መሥከረም ሲጠባ ጥይት እንገዛበታለን እንጅ። ጥይቱ ከአባታችን ወይም ከወንድማችን ሊሆን ይችላል የምንገዛው። ያኔ እኔ የምገዛው ከአባቴ ሲሆን አንድ የአብራረው ጠብመንጃ ጥይት 1 ብር አካባቢ ነበር። ታዲያ ባጠራቀምነው ሣንቲም ሁለት ሶሥት ጥይት እንገዛለን። የመሥቀል እለትም የገዛነውን ጥይት በቤተሠቦቻችን ጠብመንጃ እንደ ፈንድጃ እናጣጣዋለን። የመሠቀል እለት መንደሩ ከታች በደመራ ከላይ በጥይት እሣት ይንቦለቦላል። የአካባቢያችን ጋራዎች ድምጹን ተቀባብለው ለማዶው ሠው ያሠሙታል። የእዛኛው ማዶ ጋራም ለእኛ ያሠማል። ከዚያ በኋላ የአተኳኮሥ ጀብዱአችን እሥከ ቀጣይ መሥቀል ድረሥ ሥንተርክ እንከርማለን። በሠርግና በሃዘን ጊዜም ጠብመንጃ ማድመቂያው ነው። የእያንዳንዱ አማራ ከጠብመንጃ ጋር ያለው ቁርኝት እንደዚህ ነው የሚጀምረው። ይሄ የሁላችንም የአማራ ልጆች ታሪክ ነው ብየ አሥባለሁ። በአጭሩ ነው ለመተረክ የሞከርኩት። ሌላ ጊዜ በሠፊው እመለሥበታለሁ!! በአዲሥ መሥመር ወደ ዋናው ጉዳየ ልግባ።
የአማራ ቴሌቪዥን ትናንት ማታ ያሥተላለፈውን “ፍለጋ” የተሠኘ ድራማ ተመለከትኩት። ድራማው አንድ ወጣት ልጅ የሆነች ልጅ ወዶ እንዴት የራሡ ማድረግ እንዳለበት፣ አንድ ሌላ ሠው ደግሞ ሠው በድሎት ምን ማድረግ እንዳለበት ዘዴ ሲያፈላልጉ የሚያትት ነው። ታዲያ በመካከል አንደኛው ልጅ ጠብመንጃ መግዛት እንዳለበት ለሌላኛው ይነግረዋል። ሌላኛው ግን ጠብመንጃ ለወጣት ብሎም በዚህ ዘመን የማያሥፈልግ ዕቃ እንደሆነ ሊያሥረዳው ይታትራል። በመካከል ሁለቱም ወደ ሌላ ጓደኛቸው ዘንድ ይሄዳሉ። ቤቱ ሲደርሡ ጓደኛቸው ጠብመንጀ ፈትቶ እየወለወለ ይደርሣሉ። ከዚህ በኋላ ያለው የድራማው ክፍል ነው የሚያናድደው!! ወጣቱ ልጅ ጓደኛው ጠብመንጃውን በእጁ እንዲያሥነካው ሲለምነው ያሣያል። ተመልከቱ! ለአንድ የአማራ ወጣት ጠብመንጃ በእጅ መንካት ብርቅ ሲሆን። ባለጠብመንጃውም ጠብመንጃ ከሚገዛ በሬ እና ላም ቢገዛ የተሻለ እንደሚሆን ሊያሥረዳው ይሞክራል። በመካከል ጠብመንጃውን ወልውሎ ከገጠመ በኋላ ሲሞክረው(ሙከራው ያለ ጥይት ነው) ያ ጠብመንጃውን እንዲያሥነካው ሲለምነው የነበረው ልጅ በጣም ይደነግጣል። ድንጋጤው ከአንድ አማራ ወጣት የሚጠበቅ አይደለም። የምር ያናድዳል። ማንኛውም አማራ ለጠብመንጃ አዲሥ አይደለም። ከላይ የጠቀሥኩት አሥተዳደጋችን ለጠብማንጃ አዲሥ እንዳልሆንን የሚያሥረዳ ይመሥለኛል። ታዲያ የዚያ አማራ ወጣት ያን ያክል ለጠብመንጃ መደንገጥ ምን አመጣው? ያልን እንደሆነ ነው ቁምነገሩን የምናገኘው። መንግሥት አማራን ከምድረ ገጽ አጥፍቸ አማራ አልቦ የሆነች ሃገር እመሠርታለሁ ብሎ በያዘው ሥትራቴጅይ መሠረት አማራን ለማንበርከክ ልጆቹን ጠብመንጃ ጠል ማድረግ የመጀመሪያ ሥራው ነው። የዚህ ድራማ ዋና አጀንዳም ይሄው ነው። አማራን ከጠብመንጃው ጋር ማራራቅ፣ ጠብመንጃ የፋራ ነው የሚል መልዕክት መሥጠት፣ ያኔ አማራን እንደፈለጉ አርቆ (ር ጠብቆ ይነበብ) መግዛት ይቻላል ብሎ ከማሠብ የተሠራ አጉል ሥሌት። ልብ አድርጉ አማራ ራሡንና ሃገሩን አሥከብሮ የኖረው በነፍጠኛነቱ ነው። የታጠቀን ህዝብ ማንም እንደፈለገ ሊሸልልበት አይችልም። ህዝብ ራሡን እንዲያሥታጥቅ የሚፈለገውም ለዚህ ነው። አማራ ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት ሲባል ከሚወዳት ጠብመንጃው ጋር ወደ ጦር ሜዳ ይዘምታል። በዚህ አዋጅ ጊዜ ማንም ወሥልቶ አይቀርም። ጠብመንጃ ለአማራ ህልውናው ነው፣ ማንነቱ ነው፣ የአማራነቱ ምልክት ነው። ለአማራ ጠብመንጃ በብቸኝነቱ ጊዜ የሚያነጋግረው ጓደኛው ነው። በክፉውም በደጉም ጊዜ የማይለየው የእሡነት የአጽም ፍላጭ ነው። አማራ ያለ ጠብመንጃ ምንም ነው..! አማራ ጠብመንጃን ፈርቷር አያውቅም!! ይልቁንሥ እንዴት እንደሚያናግራት ያውቃል እንጅ!! እንዲህ እንዝጋው..!
አማራ እና ጠብመንጃ ምንና ምን ናቸው፣
የጆሮ ጉትቻ የአንገት ማተብ ናቸው።
.
በመጨረሻም እደግ ተመንደግ፣ ክፉ አይንካህ ብለን እንትፍ እንትፍ ያልንበት የአማራ ቴሌቪዥን ምራቃችን ሣይደርቅ እንዲህ አይነት ዋልጌ ፕሮግራሞችን ከማሥተላለፍ ቢቆጠብ ለነገው እድገቱ ይጠቅመዋል ሥንል እንመክራለን። ከዚህ በኋላም እንዳይደገም ይሁን!! አማራነትን ዝቅ የሚያደርግ የአማራ ቴሌቪዥን ማየት አንሻም!!

No comments:

Post a Comment