Monday, May 8, 2017

የተመድ ኮሚሽነር አቶ በቀለ ገርባን እስር ቤት ሔደው ማነጋገራቸው ተጠቆመ


 0  205  205

በኢትዮጵያ ጉብኝነት ሲያደርጉ የነበሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራኢድ አል ሁሴይን፣ እስር ቤት በመሔድ አቶ በቀለ ገርባን እንዳነጋገሯቸው ምንጮች ጠቆሙ፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ፣ ኮሚሽነሩ በሽብር ወንጀል ተከስሰው ቂሊንጦ ወህኒ ቤት ከሚገኙት አቶ በቀለ ገርባ በተጨማሪም በእስር ላይ የሚገኙ ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን አነጋግረዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ያነጋገሯቸው የተቃዋሚ ፖለቲካ እስረኞች እነማን እንደሆኑ የታወቀ ነገር ነገር ባይኖርም፣ አቶ በቀለ ገርባን ማነጋገራቸው ግን ተረጋግጧል፡፡

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ በእስር ቤት በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ የሚፈጸመውን ግፍ እና በደል፣ እንዲሁም ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ በተመለከተ ለኮሚሽነሩ ገለጻ እንዳደረጉላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኮሚሽነሩ በበኩላቸው ጉዳዩን ከመንግስት ባለስልጣናት በተለይም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርም ደሳለኝ ጋር እንደሚወያዩበት እንደገለጹላቸው ምንጮች ለቢቢኤን ገልጸዋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ እና በቂሊንጦ የሚገኙ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች፣ ወህኒ ቤቱ ሆን ብሎ የሚፈጽምባቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ጉዳያቸውን ለያዘው ፍርድ ቤት ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል፤ በአዲስ አበባ ጉብኝት ሲያደርጉ የነበሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ዘይድ ራኢድ አል ሁሴይን፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከአዲስ አበባ ውጪ የትም እንዳይሔዱ ከልክሏቸው እንደነበር ታውቋል፡፡ በተለይ ባለፈው ዓመት ከፍተና ህዝባዊ ተቃውሞ ሲደረግባቸው ወደነበሩት ወደ አማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እንዳይሔዱ በመንግስት ክልከላ ተጥሎባቸው እንደነበርም ተነግሯል፡፡ ኮሚሽነሩ በመንግስት አማካይነት ወደ ክልሎቹ እንዳይሔዱ የተደረጉት፣ በሁለቱ ክልሎች የተፈጸሙትን አሰቃቂ ግድያዎች እና እስራት እንዳያውቁ ተብሎ መሆኑም ተገልጽዋል፡፡

No comments:

Post a Comment