የዐማራ ተማሪዎች ስቃይ በዓለማያ ዩንቨርሲቲ- ተማሪ ሀብታሙ ጌታቸው እንደማሳያ፤ (ብራና )
የዐማራ ተማሪዎች ስቃይ በዓለማያ ዩንቨርሲቲ- ተማሪ ሀብታሙ ጌታቸው እንደማሳያ፤
ተማሪ ሀብታሙ ጌታቸው ይባላል፤ ትውልዱና እድገቱ ከወደ ጎጃም ሲሆን የሁለተኛ ዓመት የሕግ ተማሪ ነው፤ ከዲፓርትመንቱ በውጤት እሱን የሚስተካከል ተማሪ የለም፡፡ ባለፈው ዓመት ጀምሮ ውጤቱን አስጠብቆ መሔዱ ያናደዳቸው ጠባብ ብሔርተኞች ከትምህርቱ እንዲሰናከል ወይም እንዲያቋርጥ ጥረት ማድረግ የጀመሩት ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ሴሚስተር ውጤት ከታየ በኋላ ነበር፡፡ ሀብታሙ የሚደርስበትን ትንኮሳና ዛቻ ከምንም ሳይቆጥር ትኩረቱን ትምህርቱ ላይ አደረገ፡፡
ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ቤተ መጽሐፍት ሲያነብ ቆይቶ ወደ መኝታ ክፍሉ በመመለስ ላይ ሳለ አራት ከሳሽና መስካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ወንጀል አቀናባሪዎች አብረውት መንገድ ጀመሩ፤ አንደኛዋ ሴት ናት፡፡ ሁለቱ በኤርፎን ሙዚቃ ያዳምጣሉ፤ አንደኛው ማዳመጫውን ነቅሎ ሙዚቃውን አስጮኸው፡፡ የሚሰማው የቴዲ አፍሮ አዲሱ ሙዚቃ ነበር፡፡ ከመካከል ሴቷ ልጅ ‹‹ስለምን የነፍጠኛ ዐማራ ሙዚቃ ታዳምጣለህ›› የሚል ሀሳብ ታነሳለች፤ አካሔዳቸው ሀብታሙን ማናደድና ወደ ጠብ መገፋፋት ቢሆንም ሀብታሙ ጌታቸው ግን ዝም ብሎ ንቋቸው መንገዱን ቀጠለ፤ እነርሱ እረፍት ሳይሰጡት ግልጽ የሆነ ስድብ ይሰድቡት ጀመር፤ አሁን በዚህ ሳይናደድ ገብቶ ተኛ፡፡
ወዲያውኑ ብዛት ያላቸው ፖሊሶች መጥተው ሀብታሙን እየደበደቡ አፍነው ወሰዱት፡፡ ለምን ብለው የጮኹ ጥቂት የዐማራ ተማሪዎች በጥይት አስፈራሯቸው፡፡ ሌሊት በመሆኑ ብዙ ልጆች መሰባሰብ አልቻሉም ነበር፡፡ ሀብታሙ ጌታቸው ትምህርቱን አቋርጦ በዓለማያ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ሲደበደብ ከሰነበተ በኋላ ‹‹የትምከተኝነት›› ክስ ተመሰረተበት፡፡ ተማሪ ሀብታሙ በቀጣይ ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2009 ዓ›ም ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሏል፡፡
በዓለማያ ዩንቨርሲቲ የዐማራ ተማሪዎች ላይ እየደረሰ ያለው ሰብአዊ መብት ረገጣ ከቀን ወደ ቀን እየከፋ እንደሔደ በዩንቨርሲቲው የሚማሩ ተማሪዎች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፡፡ የኦሮሞና የትግሬ ተማሪዎች በግቢው ውስጥ ማኅበር አላቸው፡፡ የትግሬ ተማሪዎች በዩንቨርሲቲው ተደግሶላቸው ከአንድ ሳምንት በፊት በዓል አዘጋጅተዋል፡፡
ሚያዚያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም በዩንቨርሲቲው በነበረው የባሕል ፌስቲቫል የዐማራ ተማሪዎች ባሕላቸውን ካዘጋጁ በኋላ የትኽምከተኛ ባሕል በዩንቨርሲቲያችን አይቀርብም ተብሎ የሌሎች ብሔሮች ሲቀርብ የዐማራው ተለይቶ ቀርቷል፡፡ ለምን ብለው የጠየቁ ተማሪዎችም ታስረዋል፡፡
በዩንቨርሲቲው የዐማራ ተማሪዎችን ቸግር ሊፈታ ወይም ሊያዳምጥ የሚችል አንድም አካል አለመኖሩም ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል ብለውናል፡፡
No comments:
Post a Comment