Saturday, May 13, 2017

ዓሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል›› ፡ የትግራይ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ምን እያሉን ነው ???


ህወኃት የትግራይ ክልል ህዝብ በልማት ሲበደል ይቀበላልን ፣ በዳዩስ ማን ነው ??

ከግርማ በቀለ
ህወኃት ከ42 ዓመታት በፊት ‹ አማራ › በትግራይ ህዝብ ላይ የብሄር ጭቆና ፈጽሟል በማለት የትግራይ ህዝብን ከዚህ ጭቆና ነጻ አወጣለሁ በማለት ‹‹ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር /ህዝበ ወያኔ ሃርነት ትግራይ›› መስርቶ ዱር ቤቴ ማለቱና በለስ ቀንቶት ለሥልጣን በቅቶ ላለፉት 28 ዓመታት ትግራይን ፣ እርሱ በሚዘውረው መንግስት ሥሙን ሳቀይር ለ26 ዓመታት በኢህአዴግ ሥም ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር መቆየቱ አሌ የሚባል አይደለም ፡፡ ህወኃት በትጥቅ ትግሉ የከፈለውን ከፍተኛ መስዋእትነትና ያበረከተውን የላቀ አስተዋጽኦ እየጠቀሰና እያስጠቀሰ ‹ሌሎች ክልሎች ወይም ከትግራይ ክልል/ህዝብ ያለው ኢትዮጵያዊ በትውልድ ተከፍሎ የማያልቅ ውለታ እንዳለበት በመናገርና በማስነገር (ጠቅላይ ሚ/ር ኃ/ማሪያምን ጨምሮ) ከክልሉ አልፎ በሌሎች ክልሎች ጉዳይ ጣልቃ እየገባ የትግራይ ህዝብን የፖለቲካ የበላይነት ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ተጠቃሚነት አስጠብቆ እስከዛሬ መዝለቁ በኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ሲያስነሳ ቆይቶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶችም ቅሬታና ተቃውሞ እየቀሰቀሰ ለመሆኑ በርካታ አመላካቾች ለአደባባይ በቅተዋል፡፡ ይህ በመጀመሪያ በ1997 ምርጫ ወቅት በግልጽ የወጣ ሲሆን ከዚያም ለአስር ዓመታት ያህል በኃይል ታፍኖ ቆይቶ ዳግም የ2007 ምርጫን ተከትሎ በተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት ተገልጾ ፣ ህወኃት/ኢህአዴግን ብርክ አስይዞ ፣ ‹ችግሮች አሉብኝ› ይህንንም ‹በጥልቅ ተሃድሶ› እፈታዋለሁ፣ በሚል ላለንበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዳበቃን ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡

ከላይ ያነሳነውን የመከራከሪያ ጭብጥ በእንዲህ አጠቃለን ወደ ዝርዝር ጉዳዮች እንግባ፡፡
ወደ ዝርዝሩ ለመግባት ከላይ የተገለጸው የትግራይ ልህቃን የትግራይ ህዝብ በልማት በስውር ስልት ተበደለ መከራከሪያ ላይ ‹‹ የበላቺው ያስገሳታል…›› እንዲሉ Elias G Beyene በጽሁፌ ላይ በሰጡት አስተያየት ‹‹ … ትግራይ በኢንዱስትሪ ብዛት ሰምጣለች ፣ 99.%. ጄነራሎች ትግሬ ናቸው፣ ትግራይ አደገች፣ ተመነደገች ›› ከሚለው የደምመላሽ ፖለቲከኞች ፕሮፖጋንዳ ያለፈ ምንም አዲስ ነገር በጽሁፍህ አላቀረብክም ›› ብለዋል ፡፡ እዚህ ላይ Elias G Beyene መከራከርና ማሳመን ያለባቸው ይህ የፈጠራ ነው – በትግራይ የተገነባው ኢንዱስትሪ ከሌሎች ክልሎች በንጽጽር ያነሰ ነው፣ ከአገሪቱ ጄነራሎች የትግራዮች ቁጥር በንጽጽር ያነሰ ነው ወይም ሹመቱ በዚህና በዚያ ምክንያተው ተገቢ ነው ፣ ትግራይ ከሌሎች ክልሎች በንጽጽር አላደገችም ፣አልተመነደገችም በማለት መረጃና ማስረጃ ማቅረብ ሆኖ ሳለ የተለመደውን ስነልቡናዊ የማስፈራሪያ በትር ‹‹ የደምመላሽ ፖለቲከኞች›› የሚል ፍረጃ ውስጥ መግባት አግባብ አይደለም፣ ለክርክሩም አይጠቅምም፡፡ እኔ ግን እላለሁ ‹‹ የትግራይ ማደግና መመንደግ ማንንም ጤናማና ትግራይን ክልል የኢትዮጵያ አካል፣ የትግራይን ህዝብ ወገኑ (እኔ እስከሚገባኝ እኔን ጨምሮ በአብዛኛው ‹ጦርነት ናፋቂ› ኢትዮጵያዊ ኤርትራም የኢትዮጵያ አካል ናት የሚል እምነት አለ ) አድርጎ ለሚቀበል ሰው የራሱ ነውና አያሳስብም ፣ አያከራክርም፡፡ የልዩነቱ መነሻ የእውነታውን ተገላቢጦሽ ይዞ የሚራመደው የሌላውን ጩሄት የመቀማት ኃሳብ ነው፡፡
በመጨረሻ ተበደልን ብላችሁ ጩሄት በመጀመራችሁና የእኛን (‹‹ የደምመላሽ ፖለቲከኞች››) ለሩብ ምዕተ ዓመት መጮሃችንን በማመናችሁ በደላችሁን የማስረዳት ኃላፊነት በእናንተው ላይ ስለሚወድቅ ከዚህ በታች ከልማት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ስርጭት ጋር በቀጥታ የሚገናኙ በየዘርፉ የቀረቡትን መጠይቆች መልሳችሁ የበደላችሁን ትክክለኛነት አረጋግጡና አብረን እንጩህላችሁ ፡፡
1. የህወኃት የፖለቲካ የበላይነትና የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚነት፣
በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት መዋቅር ውስጥ ወሳኝ የፖለቲካ ሥልጣን በማን እጅ እንደሚገኝ ያከራክራል ካላችሁ መከራከሪያችሁን አቅርቡ፡፡ ከዚህ አልፎ የትግራይ ክልል በሌሎች በስውር ስልት መጎዳቱን አቆዩትና ህወኃት በሌሎች ክልሎች ሥልጣን በተለያየ መንገድ ጣልቃ አለመግባቱንና ሌሎች የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶችን ይህን በደል የማድረስ አቅም ቀርቶ ራሳቸው ለአቅመ-ድርጅትነት መብቃታቸውን አስረዱን ፡፡ በተጨማሪም በፌደራል መንግስት የሥልጣን እርከኖች ያለው ባለሥልጣን ብዛት ከትግራይ ህዝብ ቁጥር አንጻር ትንሽ መሆኑንና በዚህም የደረሰባችሁ በደል ይገለጽልንና ስለተጎጂነታችሁ አብረን እንጩህ፡፡

No comments:

Post a Comment