Wednesday, May 3, 2017

የነፃነት ኃይሎች ጥቃት ከዳር ወደ መሀል! (በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ)



  • ጎንደርና ባህርዳር ከተማ ውስጥ በሁለት ወር ብቻ 9 የቦምብ ፍንዳታ ደርሷል!
  • “ህወሃት የሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያን ክፍል የበቀል መወጫ እያደረገው ነው”፤ ነዋሪዎች
ላይቆም የተቀጣጠለው የሰሜን ምዕራብ ብረት አከል ህዝባዊ አመፅ የትግል ስልቱን እየቀያየረ ባህርዳር ደርሷል፡፡ አስር ወራትን ያስቆጠረው የነፃነት ኃይሎች እንቅስቃሴ ከገጠር ሽምቅ ውጊያ ወደ ከተማ የደፈጣ ቦምብ ጥቃት ተሻግሯል፡፡ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ዘጠኝ የቦምብ ፍንዳታ ደርሷል፡፡ ድርጊቱ ሰላም የነሳው ህወሃት “የአማራ ክልልን የበቀል መወጫ እያደረገው” መሆኑ ይነገራል፡፡
ህወሓት/ኢህአዴግ ሙሉ የደህንነት አቅሙንና የበዛ የመከላከያ ኃይሉን አማራ ክልል ላይ ቢያደርግም የነፃነት ኃይሎች ተከታታይነት ያለው ጥቃት ከመፈፀም ያገዳቸው ኃይል የሌለ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ የመጀመሪያዉ ዙር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከመጠናቀቁ ከአንድ ወር በፊት መጋቢት የመጀመሪያ ሳምንት እስከ ሁለተኛዉ ዙር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመጀመሪያ ወር ሚያዚያ አራተኛ ሳምንት ድረስ ጎንደር ከተማ ውስጥ ሰባት፤ ባህርዳር ከተማ ሁለት በድምሩ ዘጠኝ የቦምብ ፍንዳታዎች ደርሰዋል፡፡
የቦምብ ጥቃቶቹ ያነጣጠሩት በአገዛዙ ማህበራዊ መሰረቶች (ባለስልጣናቱ በእጅ አዙር የሚነግዱባቸው ሆቴሎች፣ የደህንነቱ አባሪ ተባባሪ የሆኑ ስውር ነጭ ለባሾችን ቤት፣ የአገዛዙ ተሽከርካሪዎች፣ . . .) ላይ መሆኑ ደግሞ የነፃነት ኃይሎችን መዋቅራዊ ጥንካሬ አጉልቶ ያሳየ ተብሎለታል፡፡ በሁለት ወር ውስጥ ብቻ ዘጠኝ የቦምብ ጥቃት ባስተናገዱት ሁለቱ ከተሞች የወጣቶች የጅምላ እስር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ከሁለቱም ከተሞች የሰበሰብናቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት “ህወሓት ክልሉን የቂም በቀል መወጫ እያደረገው ይገኛል” ሲሉ ነዋሪዎች ህወሓትን ይወነጅላሉ፡፡ “ከእያንዳንዱ የቦምብ ጥቃት በኋላ ፍንዳታው የደረሰበት ከተማ በተኩስ እሩምታ ሲታመስ ያድራል” የሚሉት ነዋሪዎች “በሌሊት ወጣቶችን ከመኖሪያ ቤታቸው አፍሶ መውሰድ የተለመደ ድርጊት ሆኗል” ይላሉ፡፡
በአንፃሩ በየጊዜው እየደረሱ ባሉ የቦምብ ጥቃቶች የአገዛዙ ልሳን በሆኑ የሚዲያ ውጤቶች መግለጫዎች ሲሰጡ ባይሰማም ከጉዳዩ አሳሳቢነት የተነሳ የአሜሪካ መንግሥት አዲስ አበባ ባለው ኤምባሲው በኩል ዜጎቹ ወደ ባህርዳርና ጎንደር እንዳይጓዙ በይፋ ክልከላ ማድረጉን አሳውቋል፡፡ በየጊዜው እየደረሱ ባሉ የቦምብ ፍንዳታዎችና የሽምቅ ውጊያዎች የተነሳ በሰሜን ምዕራብ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ቁሟል፡፡ ለዕለት ፍጆታነት ከሚውሉ ሸቀጣሸቀጦች ውጪ ይህ ነው የሚባል የንግድ እንቅስቃሴ አለመኖሩ ደግሞ አካባቢው በኢኮኖሚ እንዲደቅ አድርጎታል፡፡
በቀደመው አመፅ የፈራረሰበትን መዋቅር በድህረ-“ተሃድሶ” እንቅስቃሴው መልሶ ማቋቋም የተሳነው ብአዴን የመካከለኛ አመራሩ ሽሽት መቆሚያ አጥቷል፡፡ የሰሜን ምዕራብ የመረጃ ምንጮቻችን ከእያንዳንዱ የቦምብ ጥቃት ጀርባ መዋቅራዊ ሽፋን እንዳለዉ ይጠቁማሉ፡፡
“በርግጥም በእስካሁኑ የቦምብ ጥቃቶች ተጠያቂ የተደረገ አካል አለመኖሩ የነፃነት ኃይሎች መዋቅራዊ ድጋፍ እንዳላቸው አስረጅ ምሳሌ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል” የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ ጎንደር ውስጥ በሁለት ወራት ከደረሱት የቦምብ ጥቃቶች ውስጥ አምስቱ ጥቃቶች በኤፍ ዋን (F one) ቦምብ የተፈፀሙ ሲሆን፤ በተመሳሳይ መልኩ ከሦስት ቀን በፊት ባህርዳር ከተማ ውስጥ በሙዚቃ ድግስ ላይ የደረሰው የቦምብ ጥቃት በፍንዳታና በማፈንጠር አቅሙ አቻ የሌለው እስራኤል ሰራሹ ኤፍ ዋን (F one) ቦምብ መሆኑን የመረጃ ምንጮቻችን ዘገባ ያመለክታል፡፡

No comments:

Post a Comment