Monday, May 8, 2017

ከእባብ እንቁላል ርግብ መጠበቅ፣ አንድም ጅልነት ወይ አለማወቅ

   


ከእባብ እንቁላል ርግብ መጠበቅ፣ አንድም ጅልነት ወይ አለማወቅ
————————————————————–

ባለፈው ሰሞን ሕወሓት ለሁለት ተከፍሏል የምትል ቀልድ አይሉዋት ቧልት ነገር እንደሃገራችን የክረምት ጸሃይ ብልጭ ብላ እንደገና ጥፍት ብላለች፣ ፣ ይቺው እንዳዲስ የተተወነች ድራማ ወያኔ ኢሃዴግ ውስጥ ያለው ቅራኔ ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል፣ ከችግሩም መባባስ የተነሳ እነ ሃይሌ ገብረስላሴ፣ ኤፍሬም ይስሃቅ እንዲሁም የኢትዮጵያ ጥንታዊ አርበኞች ማህበር ሊቀመንበር ሳይቀሩ ባስታራቂነት ደፋ ቀና እያሉ ነው በማለት አትታለች፣ ፣ ቧልቷ ለክፍፍሉ መነሻ የሆነው ምክንያት ኢትዮጵያን አሁን በያዝነው መልኩ ህዝብን እየጨፈጨፍንና እየረገጥን እንቀጥል ወይንስ፣ ህዝባችንን በዲሞክራሲ አምበሽብሸንና እኛም ለህግ ተገዥ ሆነን እንቀጥል በሚሉ ቡድኖች ጸብ የተነሳ መሆኑን የምታመላክት ማጣፈጫም ተጨምሮባታል፣ ፣
ለመሆኑ እንዲህ አይነትና መሰል ቀልዶችን፣ ምን ያህል ጊዜ ሰማናቸው? እነኝህ የአንድ ሰሞን ቀልዶችስ ከቀልድነት በዘለለ ምን ውጤትን አመጡ? የሚሉትንና መሰል ጥያቄዎችን ካነሳንና እነኝህንም የወያኔ ተደጋጋሚ ተግባራት በአይነ ህሊናችን መለስ ብለን ካየናቸው፣ አሁንም እየሰማን ያለነው ምንም አዲስ ያልሆነና ‘’የሞኝ ዘፈን ሁል ጊዜ አበባየ’’ አይነት ነጠላ ዜማ መሆኑን መረዳት የሚከብድ አይመስለንም፣ ፣ እንዲህ አይነት ማዘናጊያና ማደናገሪያ ተግባራት የወያኔ ኢህአዴግ ቁልፍ መለያዎች ናቸውና፣ ፣
የአሁኑዋን የወያኔ ኢህአዴግ ተውኔትን ቧልትነት ከሚያመላክቱት ነገሮች ውስጥ አንደኛው፣ መረጃው በአሻንጉሊቱና ጠቅላይ ሚንስቴር ተብየው ሃይለማሪያም ደሳለኝ አማካኝነት በመግለጫ ብጤንት መቅረቡዋ ነው። አድርግና ተናገር የተባለውን ሁሉ ያለምንም ማቅማማት የሚያደርገው ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ በብአዴንና በህወሃት አመራሮች መካከል ያለው አለመግባባት አሁን የተፈጠረ ሳይሆን ገና ድርጅቶቹ በመሳሪያ ትግል ላይ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ የነበረ ነው ይለናል፣ ፣ ይሁን እንጂ አንዳንድ መረጃዎች የሚያመለክቱት ደግሞ በወያኔ ኢህአዴግ አመራሮች መካከል ተነሳ የተባለው አለመግባባት ዋናው ምክንያት እነኝሁ ዘራፊ ወምበዴዎች በአብዛኛው የተቆጣጠሩት ቁልፍ የመንግስት ሥልጣን ቦታዎችና ከአቅማቸው በላይ በዘረፋ ያካበቱት ሃብት ጉዳይ ነው የሚል ነው። በከፍተኛ ሙስና የአገር ሃብትን በመዝረፍ ላይ የተሰማራው ይህ ቡድን ድርጊቱን ለመሸፋፈን ሲጠቀምባቸው ከቆዩት ስልቶች ውስጥ አንዱ በተለያዩ ክልሎች እዚያም እዚህም ተጀመሩ ተብለው ዳንኪራ የተመታላቸው የልማት ስራ ተብየዎች ናቸው፣ ፣ ይሁን እንጂ እነኝህ የልማት ስራ ተብየዎች በአብዛኛው ገና ከጅምር ላይ እንዳሉ መቋረጣቸውን እንደ አብነት መጥቀስ የሚቻል ሲሆን በተለይም በነዚህ የልማት ስራ ቦታ ተብየዎች ላይ ቀደም ብሎ ይኖሩ የነበሩ ዜጎች ቦታው ለልማት ይፈለጋል እየተባሉ ከተፈናቅሉ ቦኋላ ልማት የተባለው ነገር በተግባር ሳይታይ በርካታ አመታት መቆጠሩ የአደባባይ ሚስጥር መሆኑም ይታወቃል።
ከዚህም በተጨማሪ ወያኔ ኢህአዴግዎች በተለይም ካለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ወዲህ በመላው አገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ቅርጾችና ስልቶች እየተቀጣጠሉ የቆዩትን ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች ለማፈን የማይቆፍሩት ጉድጓድና የማይጠቀሟቸው መንገዶች እንደሌሉ የሚያሳየው ሌላው አመላካችና ወጣቶችን ለማዘናጋት አነጠጥሮ የቆየው ነጠላ ዜማ “ ዋና ችግራችን ሥራ አጥነት ነው” ፣ አሥር ቢሊዮን ብር በካዝናችን ተቀምጧልና ወጣቶች ብድር ለመውሰድ ተሽቀዳደሙ የሚለው እንደነበር ልብ ይሏል።
ይህና እንዲህ አይነት ይዘት ያላቸው ተመሳሳይ ተውኔቶች የወያኔ ኢህአዴግዎች መገለጫ ባህሪያቸው መሆናቸው ቢታወቅም ‘’ልብ የሌለው ውሻ ማር ይቀላውጣል’’ እንዲሉ፣ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፍን ሃይላትና የወያኔ ግፍና መከራ ገፈት ቀማሹ የኢትዮጵያዊ ህዝብ ለእንዲህ አይነቱ የወያኔ ኢህአዴግ መሰሪ ተንኮል በትንሹም ቢሆን እውነት ይሆን፟? የሚል ቀቢጸ ተስፋ የታከለበት መዘናጋትን ማሳየቱን አልቀረም፡፡ ባንጻሩ ደግሞ እንዲህ አይነት ተውኔቶችን ወያኔ ኢህአዴግዎች ላለፉት ከሃያ አምስት በላይ ለሆኑት አመታት እንደዋና የሃሳብ ማስቀየሻ ስትራቴጂ እየተጠቀሙባቸው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ ይህን ሂደት ጠለቅ ብለን ካየነው በተለይም በአማራው ህብረተሰብ ላይ በተደጋጋሚና በግርድፉም ሲታይ በተሳካ ሁኔታ ተፈጻሚ ሲያደርጉት ይታያሉ፡፡በአማራው ላይ ይህን በደል በተደጋጋሚ የሚፈጽሙበት ዋናው ምክንያትም በጫካ ውስጥ ካሉበት ጊዜ ጀምሮ በአማራው ህብረተሰብ ላይ ካሳደጉት መራር ጥላቻና ይህንም ተከትሎ ሌሎች የሃገራችን ብሄረሰቦች አማራውን በክፉ እንዲመለከቱ ለረጂም ጊዜያት በተግባር ሲያከናውኑት ከቆየው መርዛማ ድርጊታቸው አንጻር መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡
የወያኔ ኢህአዴግዎች መርዛማ ድርጊትና ተግባር እንዲህ በአደባባይ በሚታይበት ሁኔታ አሁንም በተቃዋሚው ጎራ እየታየ ያለው ቀቢጸ ተስፈኝነትና የትኩረት ወይንም ፎከስ መዋዠቅ ለወያኔ ኢህአዴግዎች እድሜ መራዘም ቁልፍ ሚናን እየተጫወተ መሆኑ አለ የማይባል ሃቅ ነው፡፡ ቧልቱ እውነትነት ኖሮት ተከፋፈሉ ቢባልም እንኳን ወያኔ ኢህአዴግዎች እንዲህ አይነቱን መናጋት ራሳቸውን በአዲስ መልክ ለማጠናከርና ለማደስ ሲጠቀሙበት የቆየ ዘዴ ለመሆኑ ታሪካቸው በተጨባጭ ያስረዳል። ወያኔዎቹ ኢህአዴግ አፈር ልሶ የሚነሳ እባብ የሆነ ድርጅት ነው ይሉ የለ፡፡
በመሆኑም ወያኔ ኢህአዴግዎች ሁኔታዎችንና ወቅትን ጠብቀው የሚለቁዋቸው ቧልትና ቀልዶች የኢትዮጵያዊያንን የግፍና የመከራ ኑሮ ከማራዘም ውጪ የሚፈይዷቸው አንድም ተግባራት እንደሌሏቸው መረዳት፥ እንዲሁም ይህ ስልትና ስትራቴጂያቸው ያረጀና የፈጀ መሆኑን መገንዘብ በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፍነው ሃይሎች ለአንድ ደቂቃም ቢሆን ሳንዘናጋ ልንረዳው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ሃይል ንቅናቄ (አዴሃን) በጥልቅ ያምንበታል።
ለእንዲህ አይነት ቧልትና ቀልዶች ጊዜና ጉልበት ማጥፋትን አቁመን ሁሌም ትኩረታችን ይህን ዘረኛና ግፈኛ አገዛዝ ከኢትዮጵያዊያን ጫንቃ ላይ በማሽቀንጠር ቀጣይ በሆኑና ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ መሰረታዊ በሆኑት ተግባራት ላይ በጋራና በመግባባት ልንሰራ ይገባናል እንላለን።

No comments:

Post a Comment