Sunday, May 21, 2017

የዉሸት የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ -(ምላሽ ለአቶ ኤፍሬም ማዴቦ) #ግርማ_ካሳ



የግንቦት ሰባት አመራር አቶ ኤፍሬም ማዴቦ የጻፉትን አንድ ጽሁፍ አነበብኩ። በአውስትራሊያ አካባቢ ስላደረጉት ጉብኝት የተወሰኑ ነገሮችን ጀባ ብለዉናል። ምን ያህል አሮፕላን ላይ ላይ እንደቆዩ፣ አቀባበሉ እንዴት እንደነበረ ወዘተረፈ ጽፈዋል። ብዙም እዚያ ላይ አላተኩሩም።
በጽሁፋቸው ወደ መጨረሻ አካባቢ አንዳንድ ያስገረመኝ ሀሳቦችን መወርወር ጀመሩ። ስለኢትዮጵያዊነት የጻፉት ልቤን ማረከው። “ትላልቅ የኢትዮጵያዊነት እሴቶች ተረስተዉ በአንዳንድ የፖለቲካ መድረኮች ላይ በአገር መዉደድ ስም ብሄረተኝነት እየተሰበከ ነዉ። ይህ አደገኛ ስብከት አገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ በሚገባ ካለመረዳት፥ ከግድ የለሽነት፥ ለራስ ጥቅም ከመቆምና አገር ወዳድነትንና ብሄረተኛነትን ለያይቶ ካለማየት የሚመጣ በግዜ ካልታከሙት የማይድን በሽታ ነዉ” ሲሉ የዘረኝነትን መጠፎ ገጽታ ለማሳየት ሞክረዋል። የጻፉትን ሳነብ እኔ የጻፍኩት እስኪመስለኝ ድረስ “ትክክል ነው” እያልኩ ነበር ያነበብኩት።
“ብዙም አልቆየም፣ ወረድ ብዬ ጽሁፉን ማንበቤንን ስቀጥል “አይ አቶ ኤፍሬምና ግንቦት ሰባቶች” አልኩኝ። በጥሩ ጀመረው ነገሩን አበላሹት። የዘረኝነትን መጥፎነት በመናገር ጀምረው የለየለት ዘረኛ ሆኑብኝ።
አቶ ኤፍሬም ከሌላው ማህበረሰብ ነጥለው፣ በአማራ ስም በተደራጁትና የአማራ ብሄረተኝነት አቀንቃኝ በሆኑት ላይ ላይ ጠንካራና የሰላ ትችት ነው ያቀረቡት። “ከቅርብ ግዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረኮች ላይ መሰማት የጀመረ አንድ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ ስብከት አለ . . እሱም የ“አማራዉ አማራ ሆኖ መደራጀት የአማራንም የኢትዮጵያንም ነፃነት ያፋጥናል” የሚለዉ ምንም አይነት መሠረት የሌለዉ ስብከት ነዉ” ይላሉ አቶ ኤፍሬም ። ሲያጠቃልሉም “ እዉነቱን እንናገር ከተባለ የአማራዉ በዘር መደራጀት በአንድ በኩል ህወሓት ከተቃዋሚዉ ጎራ የሚፈልገዉ ትልቁ ስጦታ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የአማራዉ በዘር መደራጀት ኢትዮጵያ ከተጋረጡባት አደጋዎች ሁሉ ትልቁ ነዉ። ለዚህም ይመስለኛል የአማራዉን በዘር መደራጀት ከማንም በላይ አብዝቶ የሚኮንነዉ አማራዉ እራሱ የሆነዉ” ሲሉ በአማራ ስም መደራጀቱ ኮንነዋል።
ትችቱ ባልከፋ ነበር። በአማራ ስም በመደራጀቱ ዙሪያ ያለኝ አመለካከት የታወቀ ነው። ኦሮሞ፣ ትግሬ በሚል ስም መደራጀቱ ጥቅም እንደሌለው ስገልጽ እንደነበረው፣ አማራ ብሎ መደራጀቱ እንደማይመቸኝም በማስቀመጥ ደጋግሜ ጦምሪያለሁ። እንደ አገር የሚያዋጣን ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ መባባል ሳይሆን ዘርና ቀለም ሳንለይ እንደ ኢትዮጵያዊ በአንድ ላይ መያይዝ እንደሆነና ፣ አሁን ያለው በዘር ላይ የተመሰረተ አወቃቀር መቀየር እንዳለበት ጽፊያለሁ።
አቶ ኤፍሬም ማዴቦና ድርጅታቸው ግንቦት ሰባት፣ በገሃድ ያሳዩን ነገር ቢኖር ግን አማራ ለሚባለው ማህበረሰብ አንድ መለኪያ፣ ለሌላው ደግሞ ሌላ መለኪያ እንዳላቸው ነው። ፈረንጆች double standards የሚሉት ማለት ነው። በአንድ ወገን ከለየላቸው በዘር ከተደራጁ ፣ ያዉም መገንጠልን ሲያቀንቅኑ ከነበሩ፣ ምን አልባትም አሁንም በልባቸው ከሚያቀነቅኑ፣ ድርጅቶች ጋር ጥምረት እየፈጠሩ፣ ዉሏቸው ሙሉ ለሙሉ ከነርሱ ጋር ሆኖ፣ አሁን ያለውን በዘር የተዋቀረ ፌዴራሊዝምን እየተቀበሉ፣ ኢትዮጵያዊነትን ሊሰብኩን መሞከራቸው ግብዝነታቸውን ነው የሚያሳየው። “ኦሮሞ ነን፣ ትግሬ ነን፣ ሶማሌ ነን፣ ሲዳማ ነን፣ አፋር ነን…” እያሉ ሌሎች በዘር ከተደራጁ ድርጅርቶች ጋር አብረው እየሰሩ፣ አማራ የሚባለው ማህበረሰብ ሲደራጅ ወደ ወገዛ መሄዳቸው አንደኛ ሰዎቹ መርህ የለሽ መሆናቸውን የሚያሳይ ሲሆን ሁለተኛ ጠባቸው ዘረኝነቱ ላይ ሳይሆን አማራ በሚባለው ማህበርሰብ ላይ እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነው።
በኔ እይታ፣ “ኢትዮጵያዊነት ነው አላማችን” ብለን ፣ በዘር የተደራጁ ሌሎቹን (ኦዴፍ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ደሚት…) እያባበልን፣ በአማራ ስም የተደራጁት ላይ ጦርነት ማወጅ በራሱ ዘረኝነት ነው። በነገራችን ላይ አንዳንድ የአማራ ብሄረተኞች “ግንቦት ሰባት የአማራው ጠላት ነው” ብለው መጻፋቸው ትክክል ነበር ማለት ነው።
እርግጥ ነው አማራ የሚባለው ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊነት ልቡ ዉስጥ ነው። ሆኖም ይሀ ማሀብረሰብ እኮ በአማራ ስም መደራጀት የጀመረው ወዶ ሳይሆን ተገዶ ነው። የሕልዉና ጉዳይ ሆኖበት ነው። “አማራ” እየተባለ የዘር ማጽዳት ወንጀል ሲፈጸመብት፣ አገር በዘር ተሸንሽና መሬቱ ሲወሰድበት፣ ለመኖር የግድ “ራሳችንን ማደራጀት አለብን” ብለው ተነሱ። የአማራ ማህበረሰብን ጥያቄ ባስተናገደ መልኩ ፣ ይሄን ማህበረሰብ ፣በማሳመን እና በማግባባት እንደ ድሮው በኢትዮጵያዊነት ማእቀፍ ውስጥ ትግሉን እንዲቀጥል ማግባባት ሲገባ፣ ዳግማዊ ሕወሃት በመሆን ይሄንን ማህበረሰብ በአደባባይ ነጥሎ መዝለፍ ነዉር ብቻ ሳይሆን አደርባይነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት ማለት ሁሉንም በእኩል ማየት ማለት ነው። ከወቀሱ ሁሉንም፣ ከደገፉም ሁሉንም ነው። እንጅ እየለየን ለጊዜው የፖለቲካ ትርፍ ስለምናገኝበት ብቻ፣ ተመሳሳይ አካሄድ ያላቸውን ድርጅቶች፣ የተወሰኑትን ነቅፈን ሌሎችን ከደገፍን ኢትዮጵያዊነት ፖለቲካች የዉሸት ነው ማለት ነው።
በኔ እይታ ግንቦት ሰባት በኢትዮጵያዊነት ላይ የተንሸዋረረ አመለካከት ያለው በጣም አደገኛ የሆነ ድርጅት ነው። በብዙ መስፈርቶች ከሕወሃት ጋር የሚመሳሰል።
1. ሕወሃት ነጥሎ አንድን ማህበረሰብ(አማራ የሚባለውን) ያጠቃ እንደነበረ፣ ግንቦት ሰባትም ልክ እንደ ሕወሃት ይሄንኑ የአገራችን ማህበረሰብ ክፍል ነጥሎ እያጠቃና እየኮነነ ነው።
2. ሕወሃት ስልጣን ሲጨብጥ አጋፋሪዎቹ በሙሉ በዘር የተደራጁ ድርጅቶች እንደነበሩ፣ አሁንም ግንቦት ሰባት አጋፋሪዎቹ ሁሉም በዘር የተደራጁ ናቸው። (ደሚት፣ ኦዴፍ፣ የሲዳማ የአፋር ፣ ሰሞኑን ደግሞ የኦጋዴን ነጻ አውጭ ….)
3. ሕወሃት በዘር የተደራጁ ድርጅቶችን ሲሰበስብ፣ በአማራ ስም የተደራጀ ድርጅት እንዳልነበረ ፣ አሁንም ግንቦት ሰባት ሌሎች ዘሮች ሲሰበስብ በአማራ ስር ከተደራጁ ጋር ግን፣ እንኳን ሊሰራ እንደ ጠላት ነው የሚመለከታቸው። ( በቅርቡ ግንቦት ሰባትና ሶስት የዘር ድርጅቶች አቋቋሙት በተባለው ንቅናቄ እንደ ሞሬሽ ያሉ ድርጅቶች ተጠይቀው በዉይይቱ ለመሳተፍ ፍቃደኛ ሆነው የነበሩ ቢሆንም፣ ግንቦት ሰባት እነርሱ መኖር የለባቸውም በማለቱ የንቅናቄው አካል ሊሆኑ አልቻሉም)
4. ሕወሃት በሻእቢያ ይታገዝ እንደነበረው አሁንም ግንቦት ሰባት በሻእቢያ ቀሚስ ስር ቁጭ ብላ ቆሎና ፍርፋሪ እየተወረወረለት፣ ድርጅታዊ ነጻነቱን ተነፍጎ ያለ ድርጅት ነው።
5. ሕወሃት ስልጣን ከመጨበጡ በፊት ብዙ ተስፋ ለህዝብ ይሰጥ ነበር። ዴሞክራሲ እንደሚኖር ቃል ገብቶ ነበር። ግንቦት ሰባትም ልክ እንደ ሕወሃት ብዙ የተስፋ ቃል እየሰጠ ነው።
6. ሕወሃት አገሪቷ በዘር እንድትከፋፈል ያደረገ ነው። ግንቦት ሰባትም አሁን ያለው በዘር ላይ የተዋቀረ ፌዴራሊዝም እንዲቀጥል የሚፈለግ ነው።
7. ሕወሃት ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ያደረገ፣ አሰብ የኤርትራ ናት የሚል አቋም ያለው ነው ። የግንቦት ሰባት አመራሮች ግን በቅንጅት ጊዜ ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል የሚለውን አቋማቸዉን ትተወ፣ 180 ዲግሪ የፖለቲካ ጂምናስቲክ ሰርተው፣ የኢትዮጵያን የባህር አልባነት አምነው የተቀበሉ ናቸው።
8. ሕወሃት ሚስጥራዊ ድርጅት ነው። በውሸትና በሽፍጥ የተሞላ። የሚቆጣጠረዉንም ሜዲያ ለተራ የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ የሚጠቀምበት። ግንቦት ሰባትም ግልጽነትና ተጠያቂነት የሌለበት፣ ኦዲት ተደርጎ የማያውቅ፣ አመራሮቹ የሚዋሹ፣ እንደ ኢሳት፣ ኢካዴፍ ያሉ ሜዲያዎችን በመጠቀም ተራ ፕሮፖጋንዳ የሚረጭ ድርጅት ነው።
እርግጥ ነው ሕወሃት እና ግንቦት ሰባት በጣም የሚለያቸው አንድ ነገር አለ። እርሱም ፣ ሕወሃቶች የወሬ ሰው አልነበሩም። ነፍጥ አንስተው፣ በየበረሃው በኮንጎ ጫማ ሜዳ ተራራዉን እያቋረጡ እየሞቱ፣ እየቆሰሉ፣ ተዋግተው ነው ደርግን የጣሉት። እነ ስዬ አብርሃ፣ እነ ጻድቃን ፣ እነ ሳሞራ፣ እነ አርከበ ..ሁሉም በረሃ ነበሩ። ግንቦት ስባቶች ግን በጎንደር በጎበዝ አለቃ የተደራጁ ወገኖች በአንዳንድ ቦታዎች የሚያደርጉትን ዉጊያ እየጠቀሱ “ግንቦት ሰባት ይሄን አደረገ “ከማለት ዉጭ፣ ያደረጉት ነገር የለም። መሪዎቻቸውም የት እንዳሉ፣ የት እንደሚኖሩ አገር ሁሉ የሚያወቀው ነው።
ታዲያ ከላይ በተጠቅሱት መስፈርቶች ግንቦት ሰባት ዳግማዊ ህወሃት ቢባል ስህተት ነውን ?
አበቃሁ !!!!

No comments:

Post a Comment