Wednesday, May 10, 2017

የ “ቤተ አማራ” ወይም “ዳግማዊ መአሕድ” ነን ባዮች ማንነትና ስውር የጥፋት ዓላማ ሲጋለጥ! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

     


የ “ቤተ አማራ” ወይም “ዳግማዊ መአሕድ” ነን ባዮች ማንነትና ስውር የጥፋት ዓላማ ሲጋለጥ! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
 0  86  86
በሌሎች ላይ እንዳስተዋልነው ሁሉ የሰው ጭንቅላት የያዘ ሰው በዚህ ደረጃ ደንቁሮ፣ ማየትና ማሰብ ማሰላሰል ተስኖት እንዲህ ያስባል ብሎ ለመገመት እጅግ በጣም በሚያስቸግር ሁኔታ የተወሰኑ ወጣቶች ከሁለት ዓመታት በፊት በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ በአማራ ሕዝብ ስም ድርጅት የመመሥረት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደጀመሩ በእውኔ አይደለም በሕልሜ እንኳ በምንም ተአምር ቢሆን “ከአማራ ተወለድን!” ከሚሉ ወጣቶች እንዲህ ዓይነት ከአማራ ማንነት፣ ሥልጣኔ፣ ባሕልና ሃይማኖት ፍጹም ተቃራኒ የሆነ ፀረ ኢትዮጵያ የጥፋት አስተሳሰብ ይመነጫል ይፈልቃል ብየ አስቤ ስለማላውቅ ልጆቹ ወያኔ አማራን ካለበት የሠለጠነና የበሰለ የአስተሳሰብ ከፍታ ለማውረድ ለማርከስ በውጤቱም ሁለት ሞት ሞቶ እንዲጠፋ ለማድረግ አሠልጥኖ ያሠማራቸው እንደሆኑ እርግጠኛ በመሆን የአስተሳሰባቸውን ድንቁርናና አጥፊነት የሚገልጡ የሚተነትኑ ጽሑፎችን አከታትየ በመጻፍ ሕዝቡን አስጠንቄ ነበር፡፡
እርግጥ አሁንም ቢሆን ሰዎቹ ወያኔ ያደራጃቸው ላለመሆናቸው እርግጠኛ ባልሆንም ከጊዜ በኋላ የተረዳሁት ነገር ምንድን ነው ልጆቹን እንዲያ እንዲያስቡ ያደረጋቸው ወያኔ ሆነው ሳይሆን ወያኔ ሲቪክስ (ሥነ ዜጋ) በሚለው አጥፊ ፀረ አንድነት፣ ፀረ ኢትዮጵያ የሆነ በጠንቀኛ የጎሳ ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) የተመረዘ ትምህርቱ ተመርዘው ያደጉ በመሆናቸው ለዚህ ደንቆሮ ወያኔያዊ አስተሳሰብ የተዳረጉና አስተሳሰባቸው ለአማራ የሚጠቅም መስሏቸው የሚደክሙ የወያኔ የጥፋት ተልእኮ ሰለባዎች መሆናቸውን ተረዳሁ፡፡
“ነገሩ እንዲህ ከሆነ ቀስበቀስ እየበሰሉና ነገር ዓለሙን እየተረዱት ሲመጡ ይስተካከላሉ!” ብየ ስጠብቅ ወያኔ በእነኝህ ሰለባዎቹ የረጨው መርዘኛ የድንቁርና ቫይረስ (ጠንቀኛ ተሕዋስ) በምንሰጣቸው ምክር፣ ትምህርትና ተግሳጽ የማይጠፋ ሆኖ ሰዎቹ የምንሰጣቸው አሳማኝ ሐሳቦች አልዋሐዳቸው እያለ ነጥሮ እየተመለሰ ድንቁርናቸው ከትናንት ዛሬ እየባሰ መምጣቱና አርቆ ማሰብ፣ ግራ ቀኝ መመልከት የማይችሉ፣ የእነሱን ቢጤ ጥቂት የማይባሉ ምስኪን ወጣቶችን እያሳሳቱ ከጎናቸው ማሰለፍ እየቻሉ በመምጣታቸው ለአማራ ብሎም ለሀገራችን ህልውና አደጋ የሚሆኑበት ዕድል ሰፊ እየሆነ መምጣቱ አሳሰበኝና ነው ይሄንን ጽሑፍ ለመጻፍ የተገደድኩት፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት ይህ ቤተ አማራ የተባለው በአማራ ሕዝብ ስም የሚጠቀም የጥፋት ኃይል በሌላ የማወናበጃ ስሙ በዳግማዊ መአሕድ ስም ለግንቦት 6 ማለትም የፊታችን እሑድ በዋሽንግተን ዲሲ የጠሩትን ዓለም አቀፍ የአማራ ጉባኤ የጉባኤው አዘጋጅ ቤተ አማራ ወይም ዳግማዊ መአሕድ የቀደመ አጥፊ አስተሳሰቡን እንደጣለ እንደተወ አድርጌ በመናገር ሁሉም መሳተፍ የሚችለው የአማራ ተወላጅና በአማራ ሕዝብ ስም የተደራጀ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ድርጅቶች በጉባኤው እንዲታደሙና እዛው ላይ ተዋሕደው አንድ የተዋሐደ ጠንካራ የአማራ ድርጅት እንዲመሠርቱ ወይም ለመመሥረት አንዳች እመርታ እንዲያስመዘግቡ ጥሪ ማቅረቤ ይታወሳል፡፡ በተናጠል ስናየው ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ለዚህ ጥሪ አዎንታዊ አስተሳሰብ እንዳለው አረጋግጦ ነበር፡፡ እኔ ይሄንን ጥሪ ሳቀርብ አዘጋጆቹ ቤተ አማራዎች ወይም ዳግማዊ መአሕዶች ነን ባዮች ኃላፊነት ተሰምቷቸው አስቀድሞ የነበራቸውን አጥፊና የደነቆረ አስተሳሰባቸውን በመተው ዘመኑን የዋጀ፣ ደረጃውን የጠበቀ የበሰለ፣ የአማራንና ተነግሮ የማያልቅ መሥዋዕትነት የከፈለላት ውድ የእናት ሀገሩን ህልውና ለአደጋ የማይዳርግ ነገር ግን ጥቅማቸውን የሚያስጠብቅ አስተሳሰብ ወደማራመድ እንዲለወጡ ያደርጋቸዋል፣ ያስገድዳቸዋል ብየ በጣሙን ጠብቄ ነበረ፡፡ ብልጠቴ አልሠራም፡፡
እጅግ በሚያሳዝን መልኩ እስከ ትናንትና ድረስ ስከታተላቸው ሊያደርጉት አልቻሉም አልፈቀዱምም፡፡ ሰዎቹ በዚያ ጽሑፌ ላይ ሁሉም የአማራ ድርጅት በጉባኤው እንዳይገኙ የሚከለክላቸው ምንም ዓይነት ምክንያት ወይም መሰናክል እንዳይኖር ትሁትና አስተዋይ በሆነ አቀራረብ እየቀረቡ ሁሉንም እንዲታደሙ እንዲያደርጓቸው የጣልኩባቸውን አደራ አደራውን የመወጣት ብቃት ፍላጎትና ዓላማ ፈጽሞ የሌላቸው ተመሳስለው ገብተው ብቻ ሕዝቡን የመጥለፍ ስውር ዓላማ ያነገቡ በመሆናቸው ጭራሽም በሚጽፏቸው ጽሑፎች እንዲታደሙ የሚጠበቁ የአማራ ድርጅቶችን በስም እየጠሩ በጠላትነት እየፈረጁ “እናጠፋቹሀለን! እንደመስሳቹሀለን!” እያሉ ዛቻ ሲሰነዝሩ ሲያወግዙ ሲዘልፉ፣ ጽንፈኛ የአማራ ብሔርተኝነትን በማነሣሣት ከኢትዮጵያ የተገነጠለ ነጻ የአባት ሀገርና የአማራ መንግሥት ከመመሥረት ማንም ሊገታቸው እንደማይችል በድንፋታ ሲናገሩ ሰነበቱ፡፡ ሁኔታው እጅግ ያስከፋል፡፡ ይህ ድርጊታቸው አሁንም እንደገና “እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ለማን ነው ተቀጥረው እየሠሩ ያሉት? ዓላማቸውስ ምንድን ነው?” ብየ እራሴን እንድጠይቅ አደረገኝ፡፡ ይሄንንም ትልቅ ስሕተት ከመፈጠሩ በፊት ለሕዝብ መግለጥ ማሳወቅ አለብኝና ይሄንን ጽሑፍ ይዠ ለመቅረብ ተገደድኩ፡፡
ብዙም ባይሆኑ እነኝህ በቤተ አማራ ወይም በዳግማዊ መአሕድ ስም የተደራጁ፣ አስቀድሞም ብአዴኖችና ሌሎችም ለጠላት ተቀጥረውና ለጥፋት ታምነው የሚሠሩ የጥፋት ኃይል የሆነ የትውልድ ክፍል ከአማራ ማሕፀንም በመውጣቱ እኔን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሰው ምን ያህል ሊያሳዝንና ልቡን በሐዘን ሊሠብር እንደሚችል ማንም የሚስተው ሀቅ አይመስለኝም፡፡ “ያልዘሩት ይበቅላል!” ይሉት ብሒል ለካ አባባል ብቻ አይደለም፡፡
ለመሆኑ የቤተ አማራ ወይም የዳግማዊ መአሕድ ነን ባዮች ስውር የጥፋት ዓላማ ምንድን ነው? መባሉ አይቀርምና ወደሱ እንሻገር፦
1ኛ. ርዕዮተ ዓለማቸው (Their Ideology) ፀረ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) ፣ ፀረ ሥልጣኔ፣ ፀረ ሰብአዊ መብት፣ ፀረ ፍትሕ፣ ፀረ የአማራ ባሕልና ሃይማኖት መሆኑ፡፡
2ኛ. የሚናገሩትን ነገር የማያውቁና እጅግ ያልበሰሉ መሆናቸው ነው፡፡
እነኝህኝ ነጥቦች ተንትነን ዕንያቸው፦ “የቤተ አማራ ነን ባዮች ቡድን ርዕዮተ ዓለማቸው ፀረ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) ፣ ፀረ ሥልጣኔ፣ ፀረ ሰብአዊ መብት፣ ፀረ ፍትሕ፣ ፀረ የአማራ ባሕልና ሃይማኖት ነው፡፡ የሚናገሩትን የማያውቁና እጅግ ያልበሰሉ ናቸው!” ሲባል ምን ለማለት መሰላቹህ ለምሳሌ “የምንታገልለት ዓላማ ነው!” ብለው የሚገልጹትን ቃል እንጥቀስ “ጽንፈኛ የአማራ ብሔርተኝነትን በማነሣሣት ከኢትዮጵያ የተገነጠለ ነጻ የአማራ አባት ሀገር መመሥረት ነው!” ይላሉ፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆን ስናይ ከላይ “ናቸው!” የተባሉትን መሆናቸውን ያረጋግጥልናል፡፡
ይሄ ቡድን ይሄንን ዓላማውን ለማሳካት እየሠራበት ያለ አንድ ዋነኛ ስልት (Strategy) አለው፡፡ “አማራን ለራሱ ህልውና የሚያስብ ጽንፈኛ ብሔርተኛ ማድረግ የሚቻለው ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኙትን ገመዶች መቁረጥ፣ ኢትዮጵያን ከጭንቅላቱ አውጥቶ አጥፍቶ እራሱን ብቻ እንዲያስብ ማድረግ ሲቻል ነው!” ብለው አምነው በዚህ መሠረትም እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እንደነሱ እምነት አማራን እያስጠቃው ያለው፣ ለጥቃት እንዲዳረግ ያደረገው “ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! ማለቱ፣ ለዚህች ሀገር ኃላፊነት የሚሰማው መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ይሄንን መተው መጣልና ለራሱ ብቻ ማሰብ አለበት፣ ከዚህ በኋላ ለኢትዮጵያና ለእነኝህ እሴቶች ብሎ የሚከፍለው መሥዋዕትነት መኖር የለበትም!” ይላሉ፡፡
አማራና ኢትዮጵያ እጣ ፋንታቸው አንድና ሊነጣጠል የማይችል መሆኑን አያውቁም ማወቅም አይፈልጉም፡፡ ሥነ ልቡናቸው ሽባና አለቅጥ በፍርሐት የተሞላ ነው፡፡ በአንድ በኩል አማራን ከምድረ ገጽ ማጥፋት የሚፈልጉና እያጠፉም ያሉ የጥፋት ኃይሎች እንዳሉ ያምናሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ “አማራን ኢትዮጵያን እንዲረሳ እንዲተውላቸው በማድረግ ሊያጠፉት ከሚፈልጉ ኃይሎች ጥቃት መታደግ ይቻላል!” ብለው አምነው በሰፊው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ አማራ ኢትዮጵያን ጣለም አልጣለ፣ ተወም አልተወ በአማራነቱ ብቻ የዘር ማጥፋት ጥቃት ታውጆበት እንዲጠፋ እየተደረገ መሆኑን እያወቁ ኢትዮጵያን፣ ታሪክን፣ ማንነትን፣ ቅርስን… ብንተውላቸው እኛን ከማጥቃት ሊመለሱ ይችሉ ይሆናል!” ብለው አማራን የማንነት መገለጫዎቹን በሙሉ አስጥለው እርቃኑን በማስቀረት “ለማዳን ጥረት ማድረግ አለብን!” ብለው ቆርጠው በመነሣት በዚሁ መልኩ በርትተው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ሰዎቹ ያለቅጥ የተሸናፊነት ሥነ ልቡና የነገሠባቸውና ለምንም ነገር የማይጠቅሙ የሬሳ ወይም የተንቀሳቃሽ በድን ስብስቦች ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች አንድም ይሁኑ ሁለት እውነት ከአማራ የተወለዱ ከሆኑ እውነቴን ነው የምላቹህ እንዲህ ዓይነት ጭንጋፍና በቁሙ የሞተ፣ የበሰበሰ ትውልድ ከአማራ በመውጣቱ የሚሰማኝን ሐዘን በፍጹም በቃላት ልገልጸው አይቻለኝም፡፡ እንደ አንድ አማራም አጥንት ሰባሪ ውርደትና ሐፍረት ይሰማኛል፡፡
እጅግ የሚገርማቹህ ነገር እነኝህ ወጣቶች አሳፋሪ ፍርሐት አለቅጥ የነገሠባቸው፣ አዋራጅ የተሸናፊነት ሥነልቡና የሠለጠነባቸው ከመሆናቸው የተነሣ ከላይ የገለጹትን እያደረጉ ያሉ ሆነው እያለ በሌላ በኩል ደግሞ “ጽንፈኛ የአማራ ብሔርተኝነትን ፈጥረን ከኢትዮጵያ የተገነጠለ ነጻ የአባት ሀገር አማራን እንመሠርታለን!” ሲሉ ደግሞ ትሰሟቸዋላቹህ፡፡ የሚናገሩትን የማያውቁ ካልሆኑ በስተቀር “ጽንፈኛ ብሔርተኛ” ማለት የለየለት ፀረ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) ፣ ፀረ ሰብአዊ መብትና ፀረ ፍትሕ የሆነ ንቅናቄ ማለት ነው፡፡ ጽንፈኛ ኃይል ለእነኝህ መርሖዎች አይገዛም፣ አይታዘዝም፣ አያከብርም፡፡ የፍትሕ፣ የሰብአዊ መብት፣ የዲሞክራሲ (የመስፍነ ሕዝብ) ጥያቄዎች ቅንጣት ታክል ሳያሳስበው መንገዱ ላይ የቆሙበትን በሙሉ በጭካኔ ጠርጎ በማስወገድ በመፍጀት ማሳካት የሚፈልገውን ግብ ለማሳካት የሚታገል ኃይል ወይም ንቅናቄ ማለት ነው ጽንፈኛ የብሔርተኛ ኃይል ማለት፡፡
እርግጠኛ ነኝ የጽንፈኛን ቃል ትርጉም ካለማወቅ “የሚጠሉትን አምርሮ የሚጠላና የሚበቀል ጽንፈኛ የአማራ ብሔርተኛ ንቅናቄን እንፈጥራለን!” አሉ እንጅ ከላይ የገለጽኩላችሁን ዓይነት ሰዎች ሆነው እያለ ጽንፈኛ ኃይል የመሆን ወኔ ብርታና ፍላጎት፣ የሥነልቡና ዝግጅት፣ ብቃትና ቁርጠኝነት ይኖራቸዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም የላይኛውና ይሄኛው ሁለት ሰብእናዎች ፍጹም የተራራቁ፣ የማይጣጣሙ፣ ተቃራኒ የሆኑ ሰብእናዎች በመሆናቸው ሁለቱም በአንዴ አንድ ሰው ወይም ቡድን ላይ ሊገኙ ስለማይችሉ ነው፡፡ ይመስለኛል እነሱ “ጽንፈኛ” ሲሉ ለማለት የፈለጉት “ኢትዮጵያዊነትን ወይም አንድነትን ትቶ እረስቶ አማራነትን ብቻ የሚያቀነቅን፣ ራሱን ለማዳን ብቻ የሚታገል” ነው ለማለት የፈለጉት፡፡ የጽንፈኛ ቃልና አስተሳሰብ ትርጉም ግን ይሄ ማለት አይደለም፡፡
ሌላው ምን ማለት እንደሆነ ሳያውቁት የሚናገሩት ቃል ምንድን ነው መሰላቹህ “የአባት ሀገር አማራ!” የሚለው ቃል ነው፡፡ እናት ሀገር ቀርቶ ለምን አባት ሀገር ማለት እንደፈለጉም ከግብታዊ የደነቆረ ፍላጎት ውጭ ሊጠቀስ የሚችል ምክንያት ያላቸውም አይመስለኝም፡፡ ሲገልጹም አይቸም ሆነ ሰምቸ አላውቅም፡፡ “የአባት ሀገር” የሚለው ቃል ከአማራ ባሕል ሃይማኖትና ሥልጣኔ ጋር የሚቃረን ቃል ነው፡፡ እኛ አማሮች ሀገራችንን በሴት አንቀጽ ወይም በአንስታይ ጾታ የምንገልጻት ባሕላችን፣ ሃይማኖታችን፣ ሥልጣኔያችን ይሄንን እንድንል ስላደረገን ነው፡፡ በባሕላችን የሚወደድን፣ የምንሳሳለትን ነገር በሴት አንቀጽ ነው የምንገልጸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ያስደነቀንን ነገር የፈጸመን ሰው ስናደንቅ እንኳ “ወንድ ነሽ!” ብለን ነው በሴት አንቀጽ ጠርተን የምናደንቀው፡፡
ይሄ የቃላት አጠቃቀማችን በዛሬ ዘመን ዓለም ሠለጠንኩ ብሎ “ወንድና ሴት እኩል ናቸው!” እያለ እየሰበከ ከዚህ አስተሳሰብ ከሚገኘው ፋይዳ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት እየተደረገ እንዳለ ታውቃላቹህ፡፡ ይህ “ወንድ ነሽ!” የሚለውና ይሄንን የመሰሉ የአማራ የማነቃቂያ፣ የማበረታቻ፣ የማጀገኛ የቃል አጠቃቀም ሁለቱ ጾታዎች እኩልነታቸውን ማረጋገጡ ያለውን ፋይዳ አማራ ገና ጥንት ተረድቶ ተግባራዊ ማድረጉንና ሥልጣኔውን የሚያሳይ የቃል አጠቃቀም ነው፡፡ ይህ የአማራ ጾታን እኩል አድርጎ የማየት የቃላት አጠቃቀም እስከ እግዚአብሔር ድረስ ይደርሳል፡፡ አማራ እግዚአብሔርን በወንድ አንቀጽ ብቻ አይጠራም፡፡ ቅድስት ሥላሴ በማለትም እግዚአብሔርን በሴት አንቀጽም ይጠራል፡፡ ወደ ሃይማኖቱ ስንሔድም የአማራ ሃይማኖት ማለትም ቀደም ሲል አይሁድነት ወይም ኦሪት በኋላም ኦሪት በተስፋ ይጠብቀው የነበረው ክርስትና ሀገርን በሴት አንቀጽ ነው የሚጠራት፡፡ ኢትዮጵያ የተጠቀሰችበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በሙሉ ብታዩ በሴት አንቀጽ ነው የሚጠራት፡፡ በአጋጣሚ ሳይሆን መሠረታዊ በሆነ ሃይማኖታዊ ምክንያት፡፡
አጋንንት የሚጋልቧቸው አጋንንታውያን ፀረ ኢትዮጵያ ቤተ አማራ ወይም ዳግማዊ መአሕድ ነን ባዮቹ እንግዲህ ይሄንን ሁሉ ተቃርነው ነው “አባት ሀገር አማራ!” እያሉ ያሉት፡፡ ለነገሩ ይሄንን ስሕተት እየተሳሳቱት ያሉት መሳሳታቸውን ሳያውቁ ሳይሆን እያወቁ ይሁነኝ ብለው ነው እየተሳሳቱ ያሉት፡፡ ከላይ በገለጽኩት አማራን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኙትን ገመዶች በመቁረጥ አማራን ጽንፈኛ ብሔርተኛ የማድረግ ስልታቸው አንደኛዋ ተጠቂ ኢላማቸው የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አድርገዋታልና ሳያውቁ የተሳሳቱት ስሕተት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ኢትዮጵያን “ሀገረ እግዚአብሔር፣ የቃል ኪዳን ምድር!” ወዘተርፈ እያለች አማራን ሃይማኖታዊ አስተምህሮ እየሰበከች በሀገር ፍቅር እንዲለከፍና በሀገር ፍቅር ታስሮ እንዲቀር ያደረገች ሃይማኖት በመሆኗ አማራን ኢትዮጵያን የተወ የረሳ ጽንፈኛ ብሔርተኛ ለማድረግ በምናደርገው ትግል ዋነኛ እንቅፋታችን ናት! መመታት አለባት! ብለው ያምናሉ፡፡ ይሄ የደናቁርት ቡድን አጋንንትና የአጋንንት ፈረስ ነው የምለው ከዚህም አንጻር ነው፡፡
በባዕዳን የኮሚኒዝም (የመደብ አልባ ሥርዓተ ማኅበር) ፍልስፍና አብዶ ይህችን ሀገር ከራሷ ሥልጣኔ፣ ባሕል፣ ማንነት፣ ሃይማኖት፣ አስተሳሰብ፣ ፍልስፍና፣ ርዕዮተ ዓለም ወዘተረፈ. ጋር አለያይቶ፣ አቆራርጦ፣ አራርቆ በምዕራቡ ዓለም ማንነት ላይ ለመትከል ሲደክም የነበረው ደንቆሮው ያ ትውልድ ያደረሰብን ኪሳራ፣ የፈጠረብን ቀውስ ገና ሳይለቀን እያዳከረን እያለ ሌላ ተመሳሳይ የጥፋት መንገድ በራሳቸው የደነቆሩ ምክንያቶች የመረጡና ሌላ ዙር ጥፋት በሀገርና በሕዝብ ላይ ለመፍጠር የሚንቀሳቀስ አዲስ የጥፋት ኃይል የመምጣቱን ነገር በፍጹም በቸልተኝነት ልንመለከተው የሚገባ አይመስለኝም፡፡ ይሄንን የአጋንንት አሽከላ የሆነ ቡድን ይሄኔ ተረባርበን በእንጭጩ ማጥፋት ሃይማኖታዊና ኢትዮጵያዊ ግዴታችን ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ይሄ ቡድን ወያኔ ሆን ብሎ የፈጠረው የጥፋት ቡድን ነው የምልበት ሁለት ምክንያቶች አሉኝ፡፡ አንደኛው ቡድኑ “ጽንፈኛ የአማራ ብሔርተኛ ድርጅት ነኝ!” እያለ በሌሎች ላይ ጥፋት የሚያውጅ ቡድን እንደመሆኑ ወያኔ ለአማራ ያለስሙ ስም፣ ያለግብሩ ግብር እየሰጠ ሌሎች ጎሳዎችንና ብሔረሰቦችን እያስፈራራ በእነሱ እንዲጠላ፣ እንዲገፋ፣ እንዲገለል በማድረግ የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም ጥረት ሲያደርግ የቆየ የጥፋት ኃይል እንደመሆኑ ይሄንን በአማራ ስም ተደራጅቶ “እንዲህ አደርጋቹሀለሁ፣ እንዲህ እሠራቹሀለሁ!” የሚልን ቡድን ፈጥሮ አሁንም “አማራ መጣብህ!” እያለ ሌሎች ጎሳዎችንና ብሔረሰቦችን በማስፈራሪያነት በመጠቀም አማራን እስከወዲያኛው ተጠልቶ፣ ተገፍቶ፣ ተገልሎ እንዲቀር ለማድረግ፣ ሌሎች ጎሳዎችና ብሔረሰቦች ድጋፋቸውን እንዲሰጡት፣ ከጎኑ እንዲሰለፉ ለማድረግ በማስፈራሪያነት እያገለገለ ያለ ቡድን በመሆኑ ነው፡፡ ወያኔ ይሄንን ቡድን እንዲህ መስሎ እንዲተውን የሚያደርግበት ምክንያት ሌሎቹን በማስፈራሪያነት እንዲያገለግለው ለማድረግ ነው፡፡ ይሄ አንዱ ሲሆን ሌላው ምክንያት ደግሞ ይህ ቤተ አማራ ወይም ዳግማዊ መአሕድ ወይም መላው አማራ ነኝ የሚለው ቡድን ብአዴንን ዴሞክራሲያዊ የአማራ ብሔርተኛ ቡድን እንደሆነ አድርጎ እየሰበከ ያለ ቡድን በመሆኑ ነው፡፡
እንደምታውቁት ቤተአማራ ወይም ዳግማዊ መአሕድ ወይም መላው አማራ ነኝ ከሚለው ቡድን ውጭ ያለነው የአማራ ስሉጣን (አክቲቪስቶች) እና ማኅበራት እኩልነት በሰፈነባት፣ ሰብአዊና ዲሞክርሲያው መብቶች በተረጋገጡባት፣ አንድነቷ በጠተበቀች ኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ አማራ ከውጭና ከውስጥ፣ ከባዕዳንና ከቅጥረኛ ኢትዮጵያውያን የታወጀበትን የዘር ማጥፋት ጥቃት የግድ ተደራጅቶ እራሱን መታደግ ስላለበት ይሄንን ለማድረግ ይረዳው ዘንድ ሰብአዊ፣ ዲሞክራሲያዊና (መስፍነ ሕዝባዊና) ፍትሐዊ የሆነ ከጽንፈኛነት የራቀ የአማራ ብሔርተኝነት እንዲቀጣጠል፣ እንዲቀሰቀስ የምናደርገውን ጥረት ቤተ አማራ ነኝ የሚለው የወያኔ ቡድን “ብአዴናዊ የዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ነው!” ብሎ የእኛን እንቅስቃሴ በመፈረጅ ብአዴንን ለአማራ ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት የሚሠራ እንደሆነ እንዲቆጠር አድርጎ አቅርቦታል፡፡
ይህ ቡድን ብልጠት በተሞላበት መንገድ ብአዴንን እንዲህ እንዲታይ ጥረት በማድረግ ላይ በመሆኑ ነው ይህ ቤተ አማራ ወይም ምንትስ ነኝ የሚለው ቡድን ወያኔ ሆን ብሎ ያደራጀው የጥፋት ኃይል ነው የምለው፡፡ ምክንያቱም ሁላችንም እንደምናውቀው ብአዴን የወያኔ ቀኝ እጅ በመሆን በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጽምና ሲያስፈጽም የቆየ፣ የአማራን ባሕል፣ ታሪክ፣ ማንነት፣ ቅርስ፣ እሴቶችን ወዘተረፈ. ሲያጠፋና ሲያስጠፋ የቆየ እንጅ በአማራ ላይ ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲቀሰቀስ እንዲፈጠርና አማራ የተጋረጠበትን ፈተና እንዲወጣ፣ ህልውናውና መብቱ እንዲጠበቅ ፈጽሞ የሠራና የሚሠራ ቡድን እንዳልሆነ ሁላችንም ጠንቅቀን እናውቃለንና፡፡
ሌላው ደግሞ ይህ የጥፋት ኃይል በአማራ ሕዝብ ስም “ገንጥለን እንመሠርተዋለን!” ስለሚሉት የአባት ሀገር ጉዳይ በዝርዝር ልለው የምፈልገው ቁምነገር ነበረ፡፡ ጽሑፉ በጣም ሊረዝምብኝ ሆነ እንዴት ይሻላል? በሌላ ጊዜ ከሌሎች ችግሮቻቸው ጋር ልመለስበት? ይሻላል! ለማንኛውም ግን ይሄንን ጉዳይ በተመለከተ የዚህ ቡድን አስተሳሰብ እጅግ ያለበሰለና የአማራን ሕዝብም ለከፋ ችግርና ፈተና የሚዳርግ፣ ሊያመልጥ በማይችልበት ወጥመድ ውስጥ የሚከት የጥፋት አስተሳሰብ ነው፡፡ ቡድኑ ከድንቁርናውና ካለመብሰሉ የተነሣ ሀገር መመሥረት ማለት ቀበሌን የመከለልና የማሥተዳደርን ያህል ቀላል አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጽሑፎቸ እንደገለጽኩት የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የመገንጠል ዕድል ቢያገኝ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ፍላጎት አሟልቶ እንደሀገር ቆሞ ለመቀጠል የሚያስችል አቅምና ሌሎች ሁኔታዎችን ማሟላት የሚችል የሀገሪቱ ክፍል የለም!” ብየ ነበር፡፡ ምክንያቱም የአንደኛው የሀገሪቱ ክፍል እጣ ፋንታ በሌላኛው ላይ የተመሠረተና የተዛዘለ የተሳሰረ በመሆኑ የተሻለ ዕድልና ሕይዎት፣ የዳበረ ብልጽግና የማግኘቱ ዕድል ሊኖራቸው የሚችለው በአንድነታቸው የቀጠሉ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ እሱም ቢሆን ሀገሪቱ በወያኔ የሀገር ክህደት ተግባሩ ወደብ አልባ እንድትሆን መደረጓ ከፍተኛ የሆነ የአቅም ውስንነትን፣ ችግርና የደኅንነት ዋስትና የማጣት ሥጋትን ጋርጦባት ሀገሪቱ በምን ዓይነት የኢኮኖሚና የደኅንነት አደጋ ሥጋት ላይ እንድትወድቅ እንዳደረጋት የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡
ሀገሪቱ ካላት የተፈጥሮ ሀብቷ የተነሣ ያላትን አስጎምጅ ተስፋ ተጨባጭ ለማድረግ ይሄንን የወደብ ብሔራዊ መብትና ጥቅሟን መልሳ በጅ ማድረግ የግድ ይላታል፡፡ ከዚህ ውጪ ባለው የመገነጣጠል አማራጭ ግን ሕዝብን መቀመቅ ለማውረድ ካልሆነ በስተቀር የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበት፣ እንደ ሀገር ቆሞ የመዝለቅ ዕድልም ሆነ አቅም የሚያገኝበት አጋጣሚ የለም፡፡ ይሄንን ሀቅ ነገሮችን ጠልቆና አርቆ የማሰብ አቅም ወይም ችሎታ ያለው በሳል ሰው ሁሉ በቀላሉ ይገነዘበዋል፡፡ ሀገር መመሥረት ማለት ቀበሌ ከልሎ ማሥተዳደር ማለት አይደለም፡፡
ተገንጣይ ጎሳ ተኮር የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ቡድኖች ግን ከአስገራሚና አሳፋሪ ድንቁርናቸው የተነሣ ሀገር መመሥረት ማለት ቀበሌ ከልሎ እንደማሥተዳደር ቀላል ስለሚመስላቸው ተካልለው የተቀራመቱት የሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ቢገነጣጠሉ ሀገር ሆነው መቀጠል የሚችሉ፣ ሀገር ሆኖ ለመቀጠል አቅምና ሌሎች አስፈላጊ አስገዳጅ ሁኔታዎች የሚኖራቸው እየመሰላቸው መገነጣጠልን አጥብቀው ሲመኙ ታዩዋቸዋላቹህ፡፡ የማይሆን አማራጭ መሆኑን ማወቅ አለመቻላቸው አይግረማቹህ አብራርታቹህ ነግራቹሀቸውም የማይገባቸው የማይረዱ በመሆናቸው ይግረማቹህ እንጅ፡፡ ምን ታረጉታላቹህ የእርግማን ልጆች በመሆናቸው እኮነው እንዲህ ዓይነት ጉድ ፍጥረቶች ለመሆን የተገደዱት፡፡ ለእነሱ የተሳካላት ሀገር ምርጥ ዜጋ ከሚሆኑ የተመሰቃቀለ ሀገር ባለሥልጣን መሆንን የሚመርጡ ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ናቸው፡፡ የማዝነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቸልተኝነት መመልከቱን ከቀጠለ፣ እግዚአብሔርም ካልረዳን የሀገርና የሕዝብ ህልውናና ደኅንነት በነዚሁ ድውያን የሚወሰን መሆኑ ነው፡፡ የድንግል ልጅ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከዚህ ይሰውረና ሌላ ምን ይባላል፡፡
እንግዲህ ነገራችንን እናጠቃልልና ቀደም ሲል በቀረበው ጥሪ መሠረት የፊታችን እሑድ የበግ ለምድ የለበሰው ቤተ አማራ ወይም ዳግማዊ መአሕድ ነኝ ባዩ ቡድን ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የአማራ ጉባኤ ይካሔዳል፡፡ እኔ ባቀረብኩት ጥሪ መሠረትም በጉባኤው ለመገኘት የተዘጋጁ ወገኖች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ አሁን የአውሮፕላን (የበረርት) መጓጓዣ ቆርጣቹህ ስንት ነገር በመተው አመቻችታቹህ ቀጠሮ ይዛቹህ እያለ እንደገና ባለቀ ሰዓት “ይህ ጉባኤ የወያኔ ጉባኤ በመሆኑ ከእነኝህ ዕኩያን ጋራ የሚደረግ ምንም ዓይነት ምክክርና የሚመሠረት ድርጅት ሊኖር ስለማይችል ቅሩ! እንዳትገኙ!” ከምላቹህ ተገኙና እንደነቃቹህባቸው፣ ወያኔ መሆናቸውን፣ በእነሱም ሴራ የአማራ ሕዝብ የማይፈታ መሆኑን፣ እርኩስነታቸውን፣ የአጋንንት ጭፍራነታቸውን፣ ድንቁርናቸውን፣ ፈሪነታቸውን፣ ተሸናፊነታቸውን፣ ባንዳነታቸውን ነግራቹሀቸው ውጡ፡፡
“ለማውገዝና ወራዳ ማንነታቸውን ለራሳቸው ለመንገርና ለመርገም ብቻ ብየስ ይሄን ሁሉ ነገር ሠውቸ መገኘት አልፈልግም!” ካላቹህም እነሱን ንቆ መተውና ማግለልም ልናደርገው የሚገባ ትልቅ ሕዝባዊ ቅጣት ነውና ይሄንን ማድረግም ትልቅ ነገር በመሆኑ መቅረት ወይም አለመገኘት ትችላላቹህ፡፡ አበክሬ ማስጠንቀቅ የምፈልገው ነገር ቢኖር ግን በተለይም በጉባኤው በተለያዩ ርእሶች ንግግር እንድታደርጉ ወይም ወረቀት እንድታቀርቡና የሥነኪን ሥራዎቻቹህን እንድታቀርቡ የተጋበዛቹህና ጊዜ የተያዘላቹህ ምሁራንና ከያኔያን በዚህ የጥፋት ኃይል መድረክ ላይ ተገኝታቹህ በተያዘላቹህ አቅድ መሠረት ወረቀቶቻቹህን ማቅረባቹህ፣ ንግግሮቻቹህን ማድረጋቹህ፣ ሥራዎቻቹህን ማቅረባቹህ ሕዝባችን በወያኔ እንዲበላ ከእነሱ ጋር መዶለትና ማሴር በመሆኑ ይሄንን እንዳታደርጉ አበክሬ ማስጠንቀቅ እወዳለሁ፡፡ መገኘት ከፈለጋቹህ የምትገኙት ሕዝባችንን እንዳያወናብዱ፣ እንዳያታልሉ፣ ማንነታቸውን ተወናብዶ ተታሎ ጉባኤያቸው ላይ ለተገኘው ሕዝብ በማጋለጥ በመንገር ሕዝባችንን ከመበላት ለመታደግ ብቻና ብቻ ነው ሊሆን የሚገባው፡፡ እዚህ ላይ ስሕተት እንዳይፈጠር እጅግ ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡
ለጎንደር፣ ለጎጃም፣ ለሸዋ፣ ለወሎ ኅብረቶችና ለሌሎች በአማራ ሕዝብ ስም ለተደራጃቹህ ማኅበራዊ አደረጃጀቶችና የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ድርጅቶች ማስተላለፍ የምፈልገው ጥብቅ መልእክት ቢኖር እናንተ የቤት ሥራቹህን አለመሥራታቹህ በተፈጠረለት ክፍተት ገብቶ ወያኔ ምን ያህል ረቆ እያሴረና እየዶለተ መሆኑን ተገንዝባቹህ ሕዝባችንን ከመበላት ለመታደግና ከየት እንደመጡ በማይታወቁ ቅጥረኞች በሚፈጠሩ ሐሰተኛ ድርጅቶች እየተጠለፈ ለችግር ከመዳረግ ለመታደግ ለማዳን አንድ የተዋሐደ ጠንካራ የአማራ ድርጅት መመሥረት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ እባካቹህ በመሀከላቹህ ያለ ጥቃቅን አለመግባባቶችንና ሌሎች እንቅፋቶችን ወደጎን በመተው ፈጥናቹህ በቅርብ ጊዜ የተዋሐደ አንድ ጠንካራ የአማራ ሕዝብ ድርጅት እንድትመሠርቱና ሕዝባችንን ላለበት መራራ የህልውና ትግል በጽናትና በቁርጠኝነት እንድታታግሉ አደራየ ጥብቅ ነው፡፡ እባካቹህ ይሄንን ሳታደርጉ የምትተኙት እንቅልፍ አይኑራቹህ?
ይሄንን መልእክት ለሁሉም በማዳረስ ወገንን ከወያኔ ሸፍጠኛ ወጥመድ እንታደግ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

No comments:

Post a Comment