Wednesday, May 10, 2017

በዘረኝነት ላይ የተመሰረተው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር መልሶ እንዲደራጅና ሕጎቿ እንዲሻሻሉ ተጠየቀ

   


በዘረኝነት ላይ የተመሰረተው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር መልሶ እንዲደራጅና ሕጎቿ እንዲሻሻሉ ተጠየቀ የችግሮች ዋነኛ መንሥኤ፥ የሕግና የሥርዓት መጣስና ዘመኑን የዋጀ አለመሆን ነው፤ ተብሏል ቅዱስ ሲኖዶስ፥ ለውጡን የሚያስተባብርና የሚያስፈጽም አካል እንደሚሠይም ይጠበቃል ምልአተ ጉባኤው፣ በይደር በተያዘው የአዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመትም እንደሚነጋገር ተጠቁሟል
Patriarch Abune Mathias of the Ethiopian Orthodox Church
ላለፉት ሁለት ሺሕ ዓመታት አያሌ ፈተናዎችን በመቋቋም ሐዋርያዊና ሀገራዊ ተልእኮዋን ስትወጣ የቆየችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ችግሮች ዋነኛ መንሥኤ፥ “የሕግና የሥርዓት መጣስና ዘመኑን የዋጀ አለመሆን ነው፤” ያለው አንድ ጥናት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና በማስጠበቅና ቀጣይነቷን በማረጋገጥ ለትውልድ ለማሸጋገር፣ መዋቅሯን መልሶ ማደራጀት፤ ሕጎቿን፣ ደንቦቿንና መመሪያዎቿን በፍጥነት በማስተካከል የለውጥ ሥራ ማካሔድ እንደሚኖርባት አሳሰበ፡፡
ጥናቱን ያቀረበው፥ በተመረጡ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንትና ምእመናን ስብጥር የተቋቋመውና ባለፈው ዓመት ጥቅምት ላይ በቅዱስ ሲኖዶስ የተሠየመው ከፍተኛ ኮሚቴ ሲሆን፤ ችግሮችን ከሥር መሠረታቸው ለማረምና ለማስተካከል የሚያስችል አዲስ መዋቅርና አደረጃጀት እንዲሁም መሠረታዊ የሆኑ ሕጎችን፣ ደንቦችንና የአሠራር ሥርዓቶችን በመቅረጽና መልክ በማስያዝ የለውጥ ሥራውን የሚያካሒድ፣ ራሱን የቻለ የባለሞያ አካል መሠየምና በአስቸኳይ መተግበር እንደሚያስፈልግ አሳስቧል፡፡
ከላይ ወደ ታች፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ የሚደርሰውን መዋቅር፣ ተግባርና ሓላፊነት፥ ከተጠሪነት፣ የሰው ኃይል አደረጃጀትና የማስፈጸም አቅም ጋራ በማዛመድ የገመገመው ጥናቱ፥ መዋቅራዊ አደረጃጀቱ በአግባቡ አለመዘርጋቱን፤ የዕዝ ሰንሰለቱ፥ የላላ፣ የተንዛዛ፣ ለሓላፊነትና ለተጠያቂነት የማያመች መሆኑ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ዋነኛ ችግሮች በመሠረታዊ መንሥኤነት አስቀምጧል፡፡
የቋሚ ሲኖዶሱን መዋቅርና አደረጃጀት በቀዳሚነት ያነሣው ጥናቱ፣ የቅዱስ ሲኖዶሱን የዕለት ተዕለት ሥራዎች ለማከናወን በምልአተ ጉባኤ ቢወከልም፣ አባላቱ በየሦስት ወሩ መቀያየራቸው፣ ጉዳዮችን በስፋትና በጥልቀት አጥንቶ በመወሰን በኩል የአሠራር ችግር ማስከተሉን አመልክቷል፡፡
የፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት፣ ለፓትርያርኩ የአስተዳደር አገልግሎት ድጋፍና ለጽሕፈት ነክ ሥራዎች ቢታሰብም፣ ያለአግባብ ራሱን የቻለ ከፍተኛ የመዋቅርና የሥልጣን አካል አድርጎ እንደሚሠራ ጠቅሶ፥ “ለሕግና ሥርዓት መዛባት፣ ለመልካም አስተዳደር ዕጦትና ለመሳሰሉ ችግሮች ቀዳዳ የከፈተ አሠራር ሆኖ ታይቷል፤” ብሏል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የቤተ ክርስያኒቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አካልና የሥራ መሪ ኾነው ሳለ፣ የቋሚ ሲኖዶሱ አባል ሆነው መሥራታቸውም ለቁጥጥር እንደማያመችና ፍትሕ ሊያዛባ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡
የቁጥጥርና ምርምራ አገልግሎት፣ የሥርዓትና ሥነ ምግባር ኮሚሽን፣ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት፣ የሊቃውንት ጉባኤና የውጭ ጉዳይ መምሪያዎች፣ የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን፣ የመንፈሳውያን ኮሌጆች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና መመሪያዎች፣ የአህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶችና የሥራ ዘርፎች እንዲሁም የአጥቢያ ሰበካ ጉባኤ መዋቅራዊ አደረጃጀት፣ ሓላፊነትና ተጠሪነት፥ ከውጤታማ የአሠራር ሥርዓት፣ ከመፈጸም ብቃት፣ ከሥራ ቅልጥፍናና የውሳኔ አሰጣጥ አኳያ ያሉባቸው ችግሮች በጥናቱ ከተዳሰሱት መካከል ይገኙበታል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አወቃቀር፣ እንደሌሎች አህጉረ ተመሳሳይ ሆኖ አለመደራጀቱንና “የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት ነው” የሚለው ድንጋጌም ግልጽ ባለመሆኑ ለበርካታ ውዝግቦች መነሻ መሆኑን ጥናቱ አስረድቷል፡፡ ይህን በመጠቀም፣ አንዳንድ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ክፍሎችና የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት፣ “ተጠሪነታችን ለፓትርያርኩ ነው” በሚል ከሕግና ሥርዓት ውጭ በመሆን፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የሚሰጠውን አመራር ያለመቀበል አዝማሚያ እንደሚያሳዩና ይህም ለመልካም አስተዳደር ችግር፣ ለምዝበራና ለሌሎችም አግባብ ለሌላቸው ተግባሮች በር መክፈቱን ዘርዝሯል፡፡
በአጠቃላይ መዋቅርና አደረጃጀቱ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተልእኮ የሚያሳካና ዓላማዎችንና ግቦችን ለማስፈጸም የሚያስችል እንዳልሆነ፤ በተለይም፣ ሥልጣን ሁሉ ተጠቃሎ በአንድ ቦታ ተከማችቶ መገኘትና የሥራና የሓላፊነት ክፍፍል አለመኖሩን፤ የሥራ አስፈጻሚው ተግባርና የዳኝነቱ ሥራ ተቀላቅሎ እንደሚሠራና ለአሠራር ሥርዓት ክፍተትና ለፍትሕ መዛባት ምክንያት እንደሆነ ያስረዳው ጥናቱ፤ ሕግን የማውጣት፣ ሕግን የማስፈጸምና ሕግን የመተርጎም የሥልጣን መርሖዎች፣ ከቋሚ ሲኖዶሱ ጀምሮ በየደረጃው ተለያይተውና ተመጣጥነው በአጥጋቢ ሁኔታ የሚዘረጉበት ተቋማዊ ሁኔታ ሊኖር እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ መዋቅሩንና አደረጃጀቱን ከላይ እስከ ታች መልሶ የማደራጀቱና የማስተካከሉ ተግባር፣ ስትራቴጂያዊና መሠረታዊ በሆነ መልክ መፈጸም እንዳለበትና በጉዳዩ ላይ ቁርጠኛ አቋም ሊያዝ እንደሚገባ ጥናቱ አስገንዝቧል፡፡
ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ተሟልቶ አለመገኘትና ያሉትንም እንደየወቅቱ ሁኔታ እየታየ ማሻሻያ አለማድረግ፥ ለክፋትና ለተንኮል፣ ለግል ጥቅም ለተሰለፉ ወገኖች የተመቻቸ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ጥናቱ ጠቅሶ፤ የአሠራር ሥርዓቱን በአግባቡ ለማከናወን የሚያስችሉ ሕጎችና ደንቦች ያለመኖራቸውን በተጨማሪ መሠረታዊ መንሥኤነት አስቀምጧል፡፡
የበላይና ዋነኛ የሆነውና በሥራ ላይ የሚገኘው የ2007 ዓ.ም. ሕገ ቤተ ክርስቲያን፣ እጥር ምጥር ብሎ በግልጽ አቀራረብ፣ ጠቅላላ ድንጋጌዎችን፣ መሠረታዊ መርሖዎችንና ፖሊሲዎችን ይዞ በኮንስቲቱሽን መልክ እንደገና ተስተካክሎ እንዲጻፍና በየጊዜው ሳይቀያየር ቋሚና ዘላቂ እንዲሆን፤ ቃለ ዓዋዲው፣ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ደንብ በመሆኑ እንደገና ተሻሽሎ ሕጉን መሠረት በማድረግ፣ ሰበካ ጉባኤ ነክ የሆነው ተግባር ብቻ በሚገለጽበት ሁኔታ ተስተካክሎ እንዲጻፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመፍትሔነት የጠቆመው ጥናቱ፣ በአዲሱ መዋቅር የሚደራጀው የሥራ አስፈጻሚው አካል ተግባርና ሓላፊነቱን በብቃት ለመወጣትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችሉ የተለያዩ የሥራ ማስፈጸሚያ ሕጎችና ደንቦች(ቃለ ዐዋዲዎች) ሕገ ቤተ ክርስቲያኑን እያጣቀሱ መውጣት እንደሚኖርባቸው አመልክቷል፡፡
ከፍተኛ ኮሚቴው፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅር በሁለንተናዊ መልኩ መልሶ ለማደራጀትና ለማሻሻል ያስችላሉ ያላቸውን ሦስት የመዋቅር ለውጥ አማራጮችን ከማብራሪያዎቻቸው ጋራ በጥናቱ በማካተት ያቀረበ ሲሆን፤ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ፣ ቃለ ዓዋዲውና የሠራተኛ አስተዳደር ደንቡ፥ የመልካም አስተዳደርና የሥነ ምግባር ችግሮችን በመቅረፍ፣ ወጥ የሆነ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ዋነኛ ተልእኮዋን በብቃት ለመወጣት በሚያስችላት አኳኋን የሚሻሻሉበትን ይዘትና ሊይዟቸው የሚገቡ ዋና ዋና ሐሳቦችንም አመልክቷል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር እጅግ አሳሳቢና የለውጥ ሥራውም የሁሉንም ትብብርና ድጋፍ እንደሚጠይቅ ያስገነዘበው ከፍተኛ ኮሚቴው፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ ችግሩን ለመፍታት ያሳየው ተነሣሽነትና ቁርጠኝነት ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን ገልጿል፡፡
የአሁኑ የጥምር ኮሚቴው ጥናታዊ ሪፖርት፣ ቀደም ሲል በተለያዩ አካላት በቀረቡ ሰነዶች የተጠቆሙ የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮችና መፍትሔዎች አሳሳቢነት በድጋሚ የተረጋገጡበት እንደሆነ የተናገሩ የቅዱስ ሲኖዶሱ ምንጮች፤ የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤው፣ በመጪው ሳምንት ረቡዕ በሚጀመረው ስብሰባው፣ በዋነኛ አጀንዳነት በመያዝ የለውጥ ሥራውን በባለቤትነት በማስተባበር መልክና ቅርጽ የሚያሲዝ የባለሞያ አካል ሊሠይም እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ምልአተ ጉባኤው፣ ከባለፈው የጥቅምት መደበኛ ስብሰባው የተላለፈውንና የአዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት በሚመለከተው አጀንዳ ዙሪያ ተነጋግሮ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

No comments:

Post a Comment