Tuesday, May 30, 2017

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ተበድረው አልከፈሉም የተባሉ የውጭ ዜጎች በ25 ዓመት እስራት ተቀጡ





ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ተበድረው አልከፈሉም የተባሉ የውጭ ዜጎች በእስራት መቀጣታቸው ተገለጸ፡፡ ተከሳሾቹ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3 ነጥብ 5 ሚሊዬን የአሜሪካ ዶላር መበደራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ገንዘቡን ከተበደሩ በኋላም ወደ ዱባይ ማሸሻቸው ተነግሯል፡፡ ማይክል ማሰን የተባለው ተከሳሽ በትውልድ ደቡብ አፍሪካዊ በዜግነት አሜሪካዊ ሲሆን፣ አይመን አብዱል ሞትሊን የተባለው ሁለተኛው ተከሳሽ ደግሞ በትውልድ ግብጻዊው እንዲሁም በዜግነት አሜሪካዊ መሆኑን የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡
ተከሳሾቹ ገንዘቡን ከባንኩ የተበደሩት በጋራ ባቋቋሙት አንድ ድርጅት ስም መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ‹‹በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ2003 እስከ 2005 ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኘው ስታር ፓይፕ በተባለ ሃገር በቀል ኩባንያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተለያዩ ማሽነሪዎች ማስመጫ በሚል ገንዘብ ተበድረዋል፡፡›› ይላል የዓቃቤ ህግ የክስ ዝርዝር፡፡ ክሱ አክሎም ‹‹ተከሳሾቹ የተበደሩትን 3 ነጥብ 5 ሚሊዬን የአሜሪካ ዶላር ወደ ዱባይ በማሸሽና በራሳቸው የሂሳብ አካውንት በማስገባት ሃሰተኛ ሰነድ አዘጋጅተዋል፡፡›› ያለ ሲሆን፤ ቀጥሎም የማይሰሩ ወይም የተበላሹ በርካታ ማሽኖችን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ማጭበርበር መፈጸማቸው በክሱ ላይ ተጠቁሟል፡፡
ተከሳሾቹ ከባድ የማታለል ወንጀልን ጨምሮ በህገ ወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሃሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ወንጀሎች ክስ እንደተመሰረተባቸው ተነግሯል፡፡ ተከሳሾቹ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት፣ ሚስተር አይመን አብዱል ሞትሊን የተባሉትን እና በክሱ ላይ 2ኛ ተከሳሽ ሆነው የተቀመጡትን ግለሰብ በ25 አመት ፅኑ እስራትና በ252 ሺህ ብር እንዲቀጡ ውሳኔ ማሳለፉ ተሰምቷል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ የሆኑት ግለሰብ ደግሞ የመከላከያ ምስክር እንዲያቀርቡ ለግንቦት 25 ቀን 2009 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡

No comments:

Post a Comment