Wednesday, May 3, 2017

ዶ/ር ቴዎድሮስ ባይመረጡ ምርጫዬ ነው !

   


ዶ/ር ቴዎድሮስ ባይመረጡ ምርጫዬ ነው !

[[ዓለም አቀፍ ትኩረት የሳበው በሃገራችን የተፈጸመው የሰብዓዊ ጥሰት ፣ዜጎች በሃገራቸው ጉዳይ በሚያራምዱት የፖለቲካ አመለካከት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ነው ። ታዲያ እውነታው ይሄ ሆኖ እያለ “የፖለቲካ ልዩነት ሣይገድበን እሳቸው እንዲመረጡ ድጋፍ እንስጥ”የምትሉ ይህን እውነት የት ሸሽጋቹት ነው ?! ]]

ዘረኝነትን አጥብቄ እቃወማለሁ! እኔ በግሌ የሰው ወገን የሆን ሁሉ አንድ ነን ብዬ አምናለሁ ! የራሴን ምክንያታዊ ሃሳብ ለማቅረብ ወይም የሌላውን ሃሳብ በአመክንዮአዊ አመለካከት ለመሞገት፤ እኔ እና የእኔ ቤተሰቦች የምንናገረው ቋንቋ ፣ የምናመልከው አምላክ እና የምንከተለው ሐይማኖት፣ እንዲሁም የቆዳ ቀለማችን ፈጽሞ መመዘኛ አይሆነኝም።አንድን ሰው በሃሳቡ ወይም በሥራው ለመቃወም ሆነ ለመደገፍ የነገሩ ጠቃሚነት ወይም ጎጂነት ብቻ መስፈርቱ ሆኖ ያገለግለኛል ። ዘረኝነት “ከቀለም ወይም ከዝርያ ልዩነት የተነሣ ራስን የተሻለ አድርጎ በመገመት ሌላውን መናቅ መጨቆን የበታች አድርጎ ማየት” እንደሆነ ይነገርለታል፤እንዲህ አይነቱ አጸያፊ ነገር የምጠየፈው ቆሻሻ ነው።

ቆሻሻ በሆነው በምጠየፈው ዘረኝነት፣ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለአለም የጤና ድርጅት (WHO) መሪነት የሚያደርጉትን ውድድር ለመደገፍም ሆነ ለመቃወም እንደ-ምክንያት አያገለግለኝም።እኔ የእሳቸውን መመረጥ የማልደግፍበት ከዚህ የተሻለ በቂ ምክንያት አለኝ። የእሳቸው መመረጥ ሌሎቹ እንደሚሉት የፖለቲካ ልዩነት እና ብሔራዊ ክብር ይለያል፣የእሳቸው መመረጥ እንደ- ሃገር ክብር ነው፤በማለት እራሴን ለማሞኘት የምዳክር ሞኝ አይደለሁም ። እንደ-ሃገር አልጠቅም ያለው እሳቸው እና ጓደኞቻቸው የሚከተሉት የፖለቲካ ሃስተሳሰብ የተግባር ውጤት እንጂ ሌላ ምን ሆነና ?! ስለዚህም ለእኔ ከዚህ የሚበልጥብኝ ምንም ምክንያት የለኝም።

እሳቸው የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲ መብቶች ለአገዛዙ ሥርዓት እስካልጠቀም ድረስ ሊገድብ የሚችል መንግሥት መስራች እና በተለያየ ቦታ በኃላፊነት የሰሩ ሰው ናቸው።እሳቸው ባለፉት 26 ዓመታት ዜጎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ በኢትዮጵያ ልተፈፀሙ ፣ እስር እና እንግልቶች ተጠያቂ የሚሆን መንግሥት ባለሥልጣን ከሆኑት ውስጡ አንዱ ናቸው። እሳቸው በኃላፊነት የሚመሩት የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፣ ኢትዮጵያዊያን ላይ በደቡብ አፍሪቃ፣ በሳዊዲ አረቢያ ፣ በየመን ይደርስባቸው ለነበረ ሞትና እንግልት፣ በየአገሩ የሚገኙ ኢምባሲዎችና ቆንፅላ ጽ/ቤቶች ያሳዩት የነበረው ቸልተኝነት እሳቸው ከባላይ ሆነው የሚያዙት መሥሪያ ቤት ነበር። በቅርብ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍለ ሃገሮች ውስጥ 669 (ይህ ቁጥር) መንግሥት በይፋ ያመነው ነው። ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ሞተዋል። 336 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል ። የዜጎቻችን ሞት እና የአካል ጉዳት መንስኤ”የመልካም አስተዳደር እጦት”እና እሱን ተከትሎ የመጣ እንደሆነ መንግሥት በተለያየ ወቅት በተለያየ መንግድ አምኖ ሲግልጽ እንደነበረ የሚታወቅ ነው። መልካም አስተዳደር በሥልጣን ላይ ያለ መንግሥት የሚመዘንበት ዋና መስፈርት ነው። በመስፈርቱ መሰረት ዶ/ር ቴዎድሮስ የሚያገለግሉት መንግሥት እና እሳቸው ! በሃገራችን ለታየው የመልካም አስተዳደር እጦት እና እሱን ተከትሎ ለመጣው ነገር ሁሉ ተጠያቂ ናቸው።

ከምንም በላይ በሃገራችን የተፈጸመው የሰብዓዊ ጥሰት ከእኛ ኢትዮጽያዊያን አልፉ ፤ የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የአውሮፓ ህብረትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አሳስቧቸው በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ እስከ መጠየቅ ደርሰዋል ። ይህ አይነቶ አለም አቀፍ ትኩረት የሳበ የሰብዓዊ ጥሰት የተካሄደው እሳቸው እና ጓደኞቻቸው በሚመሩት መንግሥት ነው። እንዲህ አይነቱ አሳሳቢ የሰብዓዊ ጥሰቶች የተፈጸሙት ዜጎች በሃገራቸው ጉዳይ በሚያራምዱት የፖለቲካ አመለካከት ነው ። ታዲያ እውነታው ይሄ ሆኖ እያለ “የፖለቲካ ልዩነት ሣይገድበን እሳቸው እንዲመረጡ ድጋፍ እንስጥ” የምትሉ ይህን እውነት የት ሸሽጋቹት ነው ?! ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ለአለም የጤና ድርጅት (WHO) መሪነት የሚያደርጉትን ውድድር እኔ በግሌ አልደግፍም። የእኔ አለመደገፍ በውድድሩ ውጤት ላይ የሚያመጣው ልውጥ ምንም ይሁን ምን፣ እኔ ግን ዶ/ር ቴዎድሮስ ባይመረጡ ምርጫዬ ነው ! — (ይድነቃቸው ከበደ)

No comments:

Post a Comment