20 የሚደርሱ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከ235 ሚሊዬን ብር በላይ ቢያጭበረብሩም፣ ስለ ጉዳዩ ሪፖርት አናደርግም ማለታቸው ተጠቆመ፡፡ ከሃያዎቹ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ገንዘቡን በተመለከተ እስካሁን ድረስ ሪፖርት ያደረጉት ሁለት መስሪያ ቤቶች ብቻ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ግን ገንዘቡን የት እንዳደረሱት ለመናገር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ይሔ ሁሉ ገንዘብ የተሰወረው በስድስት ወር ውስጥ ብቻ ሲሆን፣ ጉዳዩን በተመለከተም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሪፖርት እንዲደረግለት ከሁለት ወር በፊት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ እና በመንስግት ስር የሚተዳደሩ መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ ገንዘብ ማጉደላቸውን ጠቅሶ ለከተማዋ አስተዳደር ምክር ቤት ሪፖርት አቀርቦ የነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ኦዲተር፣ በሪፖርቱ ላይ እንዳመለከተው ከሆነ፣ የገንዘብ ጉድለትን ጨምሮ፣ ያለደረሰኝ የደመወዝና የአበል ክፍያ መፈጸም፣ ከደንብና መመሪያ ውጪ የሆኑ ጨረታዎችን ማካሔድ፣ የንብረት አለማስመለስ እና የመሳሰሉ ችግሮችን ጠቅሷል፡፡ የገንዘብ ማጭበርበር የፈጸሙ መስሪያ ቤቶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ስለ ጉዳዩ ሪፖርት እንዲያደርጉ ጊዜ ተሰጥቷቸው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ባለው መረጃ መሰረት ግን ሪፖርት ሳይቀርብ ሶስት ወራት ተቆጥረዋል፡፡
ከፍተኛ ገንዘብ በማጭበርበር የከተማዋን የመንግስት መስሪያ ቤቶች በግንባር ቀደምነት የሚመራው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ሲሆን፣ 137 ሚሊዬን ብር በተለያዩ ሰበቦች ቀርጥፎ መብላቱን መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ ከህግ ውጪ የ13 ሚሊዬን ብር ዕቃ ግዢ በመፈጸም እና ግዥውን ተገን በማድረግ በሚሊዬን የሚቆጠር ገንዘብ በማጭበርበር ደግሞ የከተማዋ ስምንት መስሪያ ቤቶች ተጠቅሰዋል፡፡ ከስምንቱ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና አዲስ ዙ ፓርክ የተባሉት ከፍተኛ ገንዘብ በማጭበርበር የመንገዶች ባለስልጣን መስሪያ ቤትን በሁለተኝነት ይከተላሉ፡፡
የዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል፣ የራስ ደስታ ዳምጠው መታሰቢያ ሆስፒታል፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት፣ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት እና ራሱ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገንዘብ ያጭበረበሩ መስሪያ ቤቶች ሆነው መገኘታቸው ከዚህ ቀደም መገለጹ አይዘነጋም፡፡ በአጠቃላይ 237 ሚሊዬን ብር ካጭበረበሩት 20 የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ፣ 18ቱ ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርት ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡
ምንጭ: BBN news
No comments:
Post a Comment