Saturday, May 20, 2017

የዲሲ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በሐራጅ የመሸጥ አደጋ ገጥሟታል

   


በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ውስጥ የምትገኘውን ርዕሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በፍቅረ ንዋይ ያበዱ ካህናት በምዕመናን የተመረጠውን ህጋዊ የአስተዳደር ቦርድ (ሰበካ ጉባኤ) በአድማና በአመጽ ከተቆጣጠሩ ሁለት ዓመት ሊሞላቸው ነው። በአሁን ሰዓት ይህችን ቤተክርስቲያን በቁጥጥራቸው ስር ያደረጉ ለእግዚያብሔርንም ሆነ ለሰው ህግ የማይገዙ ጩሉሌዎች በጫካ ህግ በመጠቀም ሰብረው በመግባት የያዙትን በምዕመናን አንጡራ ሃብት የተገዛ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚሰበስቡትን ገንዘብ በደሞዝና በተለያየ መንገድ ተከፋፍለው በማመናመን ለመንግሥት መከፈል የሚገባቸውን ግብር መክፈል ተስኗቸው ቤተክርስቲያኗን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ዳርገዋታል። አንዳንድ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ምዕመናን እንደሚናገሩት ከሆነ በአሁኑ ጊዜ ዋሽንግተን ከተማ ውስጥ ለህንጻ ግንባታ የሚሆን ቦታ እጥረት ስላለ፣ ለመንግሥት የሚገባውን ግብር ባለመክፈል ቤተክርስቲያኗን በሃራጅ አሽጠው ገንዘቡን ለመቀራመት ነው ይላሉ።
በየሳምንቱ እሁድና በተለያየ ጊዜ ከምዕመናን የሚሰበስቡት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በወቅቱ ግብር ሳይከፍሉ በመቅረታቸው መንግስት ለቤተክርስቲያኑ ማስጠንቀቂያ ማውጣቱ በአጠቃላይ በአሜሪካ ውስጥ ለሚገኙ የኢ/ተ/ተ/ቤ/ክ ምዕመናን እጅግ አሳፋሪና አንገት የሚያስደፋ ድርጊት ነው። በውንብድና ከሥልጣን የተወገደው ህጋዊው ቦርድ የቤተክርስቲያኑን አስተዳደር በአጥጋቢ ሁኔታ ሲያካሂድና የመንግሥትንም ግብር በወቅቱ ሲከፍል እንደነበር የሚታወቅ ነው።  በተለይ እንደ ዶክተር አክሊሉ ሐብቴ፣ አቶ ቢልልኝ ማንደፍሮና ሌሎችም አንቱ የተባሉና የኢትዮጵያ ሕዝብ አስተምሮ ለከፍተኛ ሥልጣንና ክብር ያበቃቸው ግለሰቦች እንዴት እንደዚህ ዓይነት ወራዳ ድርጊት ውስጥ እንደገቡ ብዙዎችን ግራ ያጋባ ጉዳይ ነው። እ.አ.አ. መስከረም 27 ቀን 2015 “በዶክተር አክሊሉ ሐብቴ የሚመሩት ጋጠወጦች የተዘጋ ቤተክርስቲያን ሰብረው ገቡ”በሚል ርዕሰ ተጠናቅሮ የነበረው ዜና ጉዳዩን ለማስታወስ ያህል እዚህ ላይ አቅርበንላችኋል። http://www.mereja.com/amharic/468218
የግብር አለመክፈል ጉዳይን አስመልክቶ የቤተክርስቲያኒቷ ህጋዊ የአሥተዳደር ቦርድ ያወጣውን መግለጫ ከዚህ በታች ይመልከቱ።
ከርዕስአድባራትደብረ ስላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ህጋዊ የባለአደራዎች ቦርድ የተሰጠ መግለጫ
ግንቦት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም./ MAY 19, 2017
ሰሞኑን በዋሽንግተን ዲሲ የመንግሥት ግበር ሰብሳቢ ጽሐፈት ቤት (IRS) በ1350 BUCHANN ST WASHINGTON DC  የምትገኘዋ የርዕሰ አድባራት ደብረሰላም ቅድስት ማርያም  ቤተክርስቲያን የንብረት ግብር (TAX) ለሦስት ተከታታይ ክፈያ ባለመከፈሉ የወጣውን እጅግ አስደንጋጭና አሳሳቢ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተመልክተነዋል። ምንም እንኳን ከተመክሯችን እንዲህ ዓይነቱ ነገር መከሰቱ የለመድነው ቢሆንም በጥቂት ራስ ወዳድና ኃላፊነት በጎደላቸው ግለሰቦች ምክንያት መላ ምዕመኑ ለ27 ዓመታት ባደረገው ያልተቋረጠ ድካምና መስዋዕትነት ለባለንብረትነት ያደረሳት ቤተ ክርስቲያን ለእንዲህ ዓይነቱ አደጋ ስትጋለጥ ማየት እንደማንኛውም ኃላፊነት የሚሰማው ወገን በእጅጉ አሳስቦናል።
ህግ በህገ ወጦች ተሽሮ፣ ፍቅርና ሰላም በራስ ወዳዶችና በረብሸኞች ታውኮ ፣ የተከበረው የቤተ ክርስቲያናችን አውደ ምህረት በጥቂት ካህናት አጋፋሪነት  በተነሳው አምባጓሮ ረክሶ፣ በብዙ ድካም የተገነባውን አድነታችን ልዩ ተልዕኮ ባላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲበተን ተደርጎ፤ ህጋዊውን የባለ አደራዎች ቦርድ በጫካ ህግ አፍርሰውና እርስ በርስ ተመራርጠው የተዘጋ ቤተ ክርስቲያንን ሰብረው ገብተው ቤተ ክርስቲያኗን በጉልበት ከተቆጣጠሩት እነሆ 2 ዓምት ሊሞላቸው ጥቂት ወራት ነው የቀራቸው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከሚሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰባቸውን ያወጁ ሲሆን ይህን የተጠየቀውን 40ሺ የማይሞላ የንብረት ግብር ለመክፈል አቅሙ እያላቸው እስከዛሬ ቀን ድረስ አለመክፈላቸው እጅግ ግራ ከማግባቱ ባሻገር ቤተ ክርስቲያናችን ምን ያህል ኃላፊነት በማይሰማቸውና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ግድ በሌላቸው ግለሰቦች እጅ መውደቋ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ ግልጽ ሆኗል።
ለመንግሥት የሚገባውን መክፈል እንደሚገባ በዓለማዊውም ሆነ በመንፋሳዊው እሳቤ ተገቢ መሆኑን የሚያጣው ስለማይኖር አለማወቅ እንዳልሆነ ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። አቅሙ ኑሮ ሁሉም ነገር ተመቻችቶ እያለ ለሦስት ተከታታይ ጊዜ የመንግሥትን ግብር አለመክፈልና የቤተ ክርስቲያናችንን ህልውና ለአደጋ ማጋለጥ፤ የቤተ ክርስቲያኗ ኃላፊዎች ነን ባዮች ንዝህላልነትና ቸልተኝነት ብቻ ነው ብሎ የሚታለፍ ሳይሆን፤ እነኝህ ግለሰቦች ምን ያህል ኃላፊነት የማይሰማቸው እንደሆኑና በራሳቸው ጥቅም ላይ ብቻ ያተኮሩ፣ ነገንና ትውልድን የማያስቡ፣ እምነታቸውን ለጊዚያዊና ለሥጋዊ ፍላጎታቸው መጠቀሚያ ከማድረግ አልፈው ለቤተ ክርስቲያኗ ምንም ራዕይ እንደሌላቸው የሚያረጋግጥ ክስተት ነው።  እንደዚህ ዓይነቱን ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ስናይ ለእኛ አዲስ አይደለም ትናንትም የሆነና  ወደፊትም ከዚህ በከፋ መልኩ የምናየው እንደሆነ እንገነዘባለን።  የተከበረችውን ታላቋን ደብራችን ለብዙዎች መመኪያና መጠጊያ ፣ ለታዳጊ ህፃናቶቻችን ተስፋ እንዳልነበረች ሁሉ ርካሽ ጥቅምና አሳፋሪ ተልዕኮን ለማሳካት ሲባል ያደረሱት በደል ቀላል እንዳልነበረ በከፍተኛ ቁጭትና ኃዘን የምናስታውሰው ነው።
ዛሬ ቤተ ክርስቲያኗን በሕገ ወጥ መንገድ ተቆጣጥረው በሳምንት 10ሺ ዶላር እያሰባሰቡና በሰበብ አስባቡ ምዕመናንን ያለማቋረጥ ተጨማሪ ገንዘብ እየለመኑ ባሉበት ሰዓት ይህንን ዋጋው እጅግ በጣም ትንሽ ነገር ግን አስፈላጊነቱ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ኃላፊነት መወጣት አቅቷቸው የቤተ ክርስቲያኗን አጠቃላይ ንብረት ለአደጋ ሊጋለጥ ቀን እየቆጣረ መሆኑን መስማት እጅጉን ያስደነግጣል። ገንዘብ ማሰባሰብ የዘወትር ሥራቸው ያደረጉት እነኝህ ግለሰቦች ግድግዳ እየቀባቡ ምዕመኑን ከመሸንገልና ምንም ዕርባናና ዋጋ ከሌለው መሞካሸትና መሸላለም በፊት እንዲህ ዓይነቱን ኃላፊነት መወጣት እንደሚገባ ማወቅ ነበረባቸው። ባለቀ ሰዓት ተነስቶ የሚደረግ ሽር ጉድ ጥንካሬን ሳይሆን ድክመትን ፣ ብስለትን ሳይሆን እርባና የለሽነትን፣ ኃላፊነትን ሳይሆን መረን የለቀቀ ግድየለሽነትንና ንቅዘትን ከማሳየት ሌላ ምንም ትርጉም የለውም።
ህጋዊው የባለአደራዎች ቦርድ ቤተ ክርስቲያኗን በሚያስተዳድርበት ወቅት እነሱ ሰበሰብን ከሚሉት ገንዘብ ያነሰ እየሰበሰበ፣ አገልጋይ ካህናቶችን ከየትኛውም ቤተ ክርስቲያን በተሻለ እየተንከባከበና ሁሉንም ኃላፊነቶችን በብቃት እየተወጣ የቤተ ክርስቲያኗን ዘላቂ ህልም  ለማሳካት ለህንፃ ማሰሪያ የሚሆን ብዙ ሚሊዮን ዶላር ተቀማጭ በማድረግ ይታወቃል።  ይህም በግልጽ በቤተ ክርስቲያኗ ድረ ገጽ WWW.DSKMARIAM.ORG ላይ የተቀመጠ በመሆኑ ማንም ሰው ሊያየውና ሊገነዘበው የሚችል ሀቅ ነው። ህጋዊው የባለ አደራዎች ቦርድ የህዝቡን ፍቅርና አመኔታ በንፁህ ሥራው  ያረጋገጠ ነበር እንጂ ዛሬ እንደምናየው ርካሽ በሆነ ጊዜያዊ ድለላ ወይንም የልጅ ሥራ በሚመስል የልደታ ድግስ አልነበረም።
በመጨረሻም 40ሺ ዶላር ለማይሞላ የመንግሥት ዕዳ ከ15ሚልዮን ዶላር በላይ የሚያወጣው  የቤተ ክርስቲያኗ ንብረት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ማድረግ እጅግ አሳፋሪ፣ ምንም አመክንዮ የሌለውና ኃላፊነት የጎደለው ተግባር በመሆኑ ህጋዊው የባለ አደራዎች ቦርድ በጥብቅ ያወግዘዋል። እነኝህ ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት ምንም ዓይነት ሰበብ ሳይደረድሩ ዛሬውኑ ይህንን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በጥብቅ እናሳስባለን። ማንኛውም ከህዝብ የሚሰበሰበው ዶላር በቀጥታ ለህዝብ ጠቀሜታ መዋል እንዳለበት እያስገነዘብን በዚህ ሳቢያ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ለሚደርሰውን ጉዳት ህጋዊ የባለ አደራዎች ቦርዱ በህግ እንደሚጠይቅ በአፅንዖት ያሳስባል።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የርዕሰ አድባራት ደብራ ስላም ቅድስት ማርያም የባለአደራዎች ቦርድ

No comments:

Post a Comment