የጎንደር ሰላማዊ ሰልፍ በእውነት ሰላማዊ ሆኖ አልፏል፡፡ መንግሰት በዚህ ጉዳይ ጠብ በመጫር ባለመሳተፉ ሊመሰገን ይገባል፡፡ ከመንግሰት የምንጠብቀው ይህንን ነው፡፡ ነገር ግን ከሰልፉ ማብቃት በኋላ መንግሰት ጠብ ጫሪነቱን ቀጥሎበታል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ የአማራ ክልል የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው ሰላማዊ ሰልፍ የሚመለከተውን አዋጅ የሚያውቁት አይመሰለኝም፡፡ አዋጁ ያረጀ ያፈጀ ቢሆንም ሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ አያሰፈልገውም-የሚያስፈልገው ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡ ሰልፍ እንደሚደረግ ለመንግሰት አካል እንዲያውቀው የሚደረገበት ምክንታያት ደግሞ ለሰላማዊ ሰልፈኞችም ሆነ ባጠቃላይ ለህዝብ እና ለንብረት ጭምር ጥበቃ እንዲያደርግ ነው፡፡
የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንደሚሉት በስልፉ ላይ ለተንፀባረቁት ሃሳቦች ኃላፊነት የሚወሰድ አካል ለመፍጠር አይደለም፡፡ በሰላማዊ ሰልፍ ላይ የማህበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊም ሆነ የፖለቲካ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ መንግሰት ሊሚልሳቸው የሚችላቸው ከሆኑ እሰየው ካልቻለ ደግሞ ለሚችል እንዲለቅ ለማስገደድ ጭምር ሊሆን ይችላል፡፡
የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስቂኝ ነገሮች ተናግረዋል፡፡ ከአስቂኞቹ አንዱ ሰልፈኞች ይዘውት የወጡት ባንዲራ ትክክል አይደለም የሚል፡፡ ህዝቡ እየተቃወመው ያለው አንዱ ነገር እኮ ባንዲራችን ላይ ያልተሰማማንበት ነገር በግድ አትጫኑብን፡፡ የተሰማማው ይለጥፍ ያልተሰማማው ያለመለጠፍ መብት አለኝ እያለ ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን ማሰፈራሪያ ህግ እንደወጣ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ይህ በማስፈራሪያ የሚሆን ነገር እንዳልሆነ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በግድ ሲሆን ማርም ይመራል፡፡ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው መስማት የሚፈልጉትን ለመሰማት እኮ ሰለማዊ ስልፍ ሳይሆን እነርሱ የሚጠሩት ስብሰባ ላይ መገኘት ነው የሚያስፈልገው፡፡
ለማነኛውም የጎንደር ሰለማዊ ሰልፍ አንድ ነገር አሰተምሮን አልፎዋል፡፡ ሰልፍ እንደሚደረግ የሚነገረው አካል በተለያየ ሰበቦች የህዝብ ድምፅ ላለመሰማት ሲያሴር፣ ህዝብ ደግሞ እንቢኝ እንደሚል አሳይቶዋል፡፡ ከዓመታት በፊት ተመሳሳይ ነገር በደሴ አካሄደናል፡፡ ሰልፍ እንደምናደርግ ፕሮግራማችንን አሳውቀን እንቢ ሲሉ ግደሉን ብለን ወጥተን በሰላም ተጠናቋል፡፡ አሁን በጎንደር ይህ ተደርግሟል፡፡ የጎንደሩ የተለየ የሚያደርገው ደግሞ ሊቃወሙ የወጡት የክልሉን መንግሰት ብቻ ሳይሆን ተገፍተዋል ያሉትን ወንድምና እህት የወልቃይትና አካባቢው ህዝብ ጥያቄ ለመደገፍ ነው፡፡ የወልቃይት እና የአካባቢው ህዝብ ጥያቄውን ለትግራይ ክልል ቢያቀርብ እንደማይደመጥ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ እኔም ከሚስማሙት ውስጥ ነኝ፡፡ ህውሃት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ስለማይመቸው ማለቴ ነው፡፡
በተመሳሳይ ጉዳይ ትግራይ ውስጥ የወልቃይት ህዝብ ትግሬ ነው የሚል ስልፍ ወጥቶ ተመልክተናል፡፡ ይህን ሰልፍ ለማድረግ ግን የሰለማዊ ሰልፍ ጥያቄ ለማቅረብ እና ለሚፈጠረው ነገር ሃላፊነት ለመውሰድ በሚል ጥያቄ አቅርቦ የተፈቀደለት አካል የለም፡፡
ከዚህ ጋር የተያያዙ አንድ ሁለት ነጥቦች ላንሳ፡፡ በአዲስ አበባ አንድ ማርቆስ የሚባል የሰልፍ ጉዳይ የሚመለከተው ሰው ጋር ንግግር ስናደርግ ለመሆኑ እሰኪ እሰከዛሬ ኢህአዴግ ይህን ሁሉ ስብሰባ እና ሰልፍ ሲያደረግ ጥያቄ ያደረገበትን አንድ ደብዳቤ አሳየኝ አልኩት፤ ደነገጠ ለነገሩ “ጥያቄ ያቀርባሉ ?” አልኩት፡፡ መልስ የለም – መቼም እናንተም እኔም እዚህ ውስጥ ያለው መልስ ይገባቸዋል፡፡ “አንበሳ” ተበድሮ ይከፍላል ወይ? ቢባል ማን ጠይቆት ይባላል፡፡ በዋነኝነት ሰላማዊ ሰልፍ ሲደረግ ሶሰት ሰዎች መጥተው መፈረም አለባቸው የሚሉት ለማስፈራራት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ህገ መንግሰት ድንጋጌ ውጭ ነው፡፡
ሌላ አንድ ጉዳይ ልጨምርላችሁ፡፡ ምርጫ ቦርድ የሚባል አንድ ማፈሪያ ተቋም አለ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ እንዳይኖረው ተገቶ ከገዢው ፓርቲ እና ከደህንነት ጋር የሚሰራ ተቋም ነው፡፡ ሃላፊዎቹም ቢሆኑ በሚጠበቁት ደረጃ ሳይሆን ወሬ በማቀባበል የሚኖሩ ናቸው፡፡ ተቋም መስሎን አክብረነው በምንነጋገርበት አንድ ወቅት “ለመሆኑ በኢህአዴግ፣ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፣ እንዲሁም በአጋር ድርጅቶች ሰብሰባ ላይ ተወካይ ትልካላችሁ ወይ?” የሚል ጥያቄ ለሃላፊው አቀረብኩ፡፡ በፍፁም እንደማይልኩ ነገረኝ፡፡
ለነገሩ በየትኛውም ህግ መገኘት አለባቸው የሚል ባይኖርም ዘወትር በተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብሰባ ላይ ተገኝተው ሂደቱን ሲታዘቡ/ሲሰልሉ ውለው፣ የፈለጉትን ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ ወሬውን ለሚፈልገው አካልም ወሬውን ሹክ ይሉታል፡፡ የፃፉትን ሪፖርት ግልባጭ እንኳን ለፓርቲዎች አይሰጡም፡፡ በተለይ በተደጋጋሚ ለመታዘብ የሚመጡት ሁለት የምርጫ ቦርድ ሰዎች ይህን እንጀራ ብለው ሲበሉ አፍራለሁ፡፡ የምርጫ ቦርድ ሃላፊዎች በፓርቲዎቹ ስብሰባ ላይ ባይገኙም ግን ፓርቲው መንግሰትን ተገን አድርጎ በሚሰበሰባቸው ሚስጥራዊ ስብሰባዎች ግን ይገኛሉ፡፡ የፓርቲውን አቅጣጫ ለማስፈፀም፡፡ በተደጋጋሚ የምክርቤት አባል እያለሁ የፓርቲ ጉዳይ ስለሆነ በሚል እኔ እንድወጣ ተደርጎ የምርጫ ቦርድ ሃላፊዎች ግን ተገኝተው ታዝቢያለሁ፡፡ እነዚህ ናቸው ፓርቲዎችን በአንድ ዓይን እናያለን የሚሉ ማፈሪያዎች፡፡ አንድ ነገር ግን በትክክል ይላሉ – “ሆደ ሰፊነን”፡፡
No comments:
Post a Comment