Thursday, August 4, 2016

አሜሪካ ኤምባሲ በር ላይ ሰልፍ ያደረጉ የኦሮሞ ተማሪዎች ኢፍትሃዊ ስቃይ ቀጥሏል


በኦሮሚያ እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ አመፅ ተከትሎ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን ሰብአዊ መብት ጥሰት በመቃወም የካቲት 29, 2008 ቀን አዲስ አበባ በሚገኘው አሜሪካ ኤምባሲ በር ሰልፍ በመውጣታቸው ክስ ተመስርቶባቸው የታሰሩት 20 ኦሮሞ የአአዩ ተማሪዎች ጉዳይ ከትላንት ወዲያ የአቃቢ ህግ የምስክር ብይን ተሰጥቶበታል።
በተማሪዎቹ ላይ የቀረቡባቸው ሶስት ክሶች የሚከተሉት እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
1.አለም አቀፍ ድርጅቶች አካባቢ ከሚመለከተው የመንግስት አካል እውቅና ውጪ በጋራ እና በመሰባሰብ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ [የሰላማዊ ሰልፍና የፓለቲካ ስነስርአት አዋጅ ቁጥር 3 አንቀጽ 7(1)፣ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/1/ሀ እና የወንጀል ህግ አንቀፅ 482/1/ሀ ን በመተላለፍ]
2.የህዝብን አስተሳሰብ ሊያናውጡ የሚችሉ ሃሰት መፈክሮችን ማሰማት፣ በመንግሰት ላይ የሃሰት ጥርጣሬ አንዲፈጠር ህዝብን ማነሳሳት [የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/1/ሀ እና የወንጀል ህግ አንቀፅ 486(ሀ) ን በመተላለፍ]
3.የተወካዮች ምክር ቤት ያወጣውን የጸረ ሽብር ህግ ሰዎች እንዲቃወሙት ለማድረግ የጸረ ሽብር ህጉ አንዲሻሻል አንፈልጋለን የሚል መፈክር ማሰማት[የወንጀል ህግ አንቀፅ 32/1/ሀ እና የወንጀል ህግ አንቀፅ 487(ለ) ን በመተላለፍ]
በ9ኙ ተከሳሾች ላይ (10ኛ እና ከ12ኛ –19ኛ ያሉ ተከሳሾች) አቃቢ ህግ ያቀረባቸው ምስክሮች የቀረቡባቸውን ክሶች መፈፀማቸውን የሚገልፅ ምስክርነት ስላልሰጡ፤ ሶስቱም ክሶች ውድቅ ተደርጎላቸው መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ተወስኗል። ለተቀሩት 11ዱ ተከሳሾች (ከ1ኛ—9ኛ፣ 11ኛ እና 20ኛ ተከሳሾች) የመጀመሪያው ክስ ድርጊቱን የሚያስረዳ በቂ ምስክር ባለመገኘቱ ውድቅ ሆኖ በተቀሩት ሁለት ክሶች ላይ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።
በነፃ የተሰናበቱት 9ኙ ተማሪዎች ማረሚያ ቤቱ እንዲለቃቸው ትእዛዝ የተፃፈ ሲሆን እንዲከላከሉ የተበየነባቸው ተማሪዎች ለሃምሌ 28, 2008 መከላከያ ምስክሮቻቸውን እንዲያቀርቡ ተቀጥረዋል።

No comments:

Post a Comment