Thursday, August 4, 2016

ትግላችን ረዥምና እልህ አስጨራሽ ነው፤ ግን እንወጣዋለን!!


ውዱ የአማራ ልጅ ኮ/ል ደመቀ ሕዝባችን የገባበትን አስከፊ ሁኔታ ጠንቅቆ የተረዳ ወንድማችን ነው፡፡ ሁልጊዜም በተገናኘን ቁጥር ባለፉት 40 ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ሲደርስ የቆየውን በደል እየጠቀሰ፣ ሕዝባችን እየደረሰበት ካለው መጠነ ሰፊ በደል አንጻር፣ ተደራጅቶ ካልተንቀሳቀሰ በስተቀር ወደፊት ወሮበላው የወያኔ ግፈኛ ቡድን ቢቀየርም ለውጥ ይመጣል ብሎ እንደማያምን ሳይገልጽልን አልፎ አያውቅም፡፡ ኮ/ል ሁልጊዜም “ትግሉ ረዥምና እልህ አስጨራሽ ነው፤ ግን ሁላችንም እንደ አንድ፣ አንዳችንም እንደ ሁላችን ሆነን እንደጀግኖች አርበኞች አባቶቻችን ከታገልን እንወጣዋለን” ይለን ነበር፡፡ ወንድማችን በጣም ትክክል ነው፡፡
አንዳንዶች የወልቃይት አማሮች ያሳዩትን ጀግንነትና ባለፈው እሑድ በጎንደር ከተማ በሌሎች አካባቢዎች የተካሔዱትን ሰልፎች እየገለጹ ሕዝባችን ነጻ ወጣ ሲሉ ታዝበናል፡፡ እርግጥ ነው ሕዝባችን ያሳየው ጀግንነት እጅግ አኩሪና ገና ብዙ ሊጻፍለት፣ ገና ብዙ ትንታኔ የሚያስፈልገው ነው፡፡ በዚህ ላይ ልዩነት የለም፡፡ ልዩነቱ ትግሉ ገና ተጀመረ እንጂ የአማራ ሕዝብ ካለበት የጭቆና መጠን አንጻር ገና ፈቀቅም አላለም በሚለው ነጥብ ላይ ነው፡፡ ገና ብዙ ብዙ ይቀረናል፡፡ ገና ብዙ መስዋዕትነት ይጠብቀናል፡፡ የወያኔ ወሮበላ ቡድን ለአማራ ሕዝብ ያለው ጥላቻ እስከምን ድረስ እንደሆነ፣ የተላላኪዎቹም አጥፊ ተግባር እስከየት ሊደርስ እንደሚችል ይታወቃልና፣ እንዲሁ እንደዘበት ከዚህ አስከፊ የግፍ አገዛዝ ነጻ እንወጣለን ማለት አይደለም፡፡ ጨርሶ፡፡
ኮ/ል ደመቀ እንዳለው ትግሉ ረዥምና እልህ አስጨራሽ ነው፤ ነገር ግን ጠላቶቻችን እነማን እንደሆኑ፣ ስለእኛ ያላቸውን የጥላቻ መጠንና የሕዝባችን ትግል ለማኮላሸት እስከምን ድረስ ሊጓዙ እንደሚችሉ፣ እንዲሁም የሚጠብቀን መስዋዕትነት ምን ያህል እንደሚሆን ጠንቅቀን ካወቅንና እንደ አንድ ሕዝብ ከተንቀሳቀስን ነጻ መውጣቻችን አይቀርም፡፡ ነጻ የምንወጣበት ዘመን የሚያጥረውም ሆነ የሚረዝመው ጠላቶቻችን በሚያዘጋጁል ወጥመድ ብቻ አይደለም፡፡ የጠላቶቻችንን ሁኔታ ጠንቅቀን ካላወቅንና እንደአንድ ሕዝብ በጽናት ካልተንቀሳቀስን እኛም የጭቆናውን ዘመን ማራዘማችን አይቀርም፡፡
ልጆቻችን ጠላታቸው ማን እንደሆነ ማስተማር ይጠበቅብናል፡፡ ወጣቶቻችን ጠላታቸው ማን እንደሆነ ማወቅ አለባቸው፡፡ ወያኔ ጠላት መሆኑን ደግመን ደጋግመን መንገር ይኖርብናል፡፡
ደግነቱ የአማራ ሕዝብ አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከላይ እስከታች ጨቋኙ ማን እንደሆነና ከዚህ አስከፊ ጭቆና ሊወጣ የሚችለው እንደሕዝብ ሲንቀሳቀስ መሆኑን ተገንዝቧል፡፡ ይኼ ትልቅ ድል ነው፡፡ አሁንም ይበልጥ መሰባሰብ፣ ይበልጥ መደጋገፍና መደራጀት ይጠበቅብናል፡፡ ግፈኛውን የወያኔን ወሮበላ ቡድን ከጫንቃችን ላይ ማስወገድ ብቻ ሳይሆን ወያኔ ከወደቀ በኋላ ስለሚኖረን ይዞታ (ሚና) መወሰን የምንችለው እንደሕዝብ ስንደራጅ ብቻ ነው፡፡
እንሰባሰብ፤ እንረዳዳ፤ እንደራጅ፡፡ ትግሉ ረዥምና እልህ አስጨራሽ መሆኑን ተገንዝበን በጥቂት ድሎች አንርካ፤ የሞቅ ሞቅ ትግል ይጥለናል፡፡ ጽናትን ከጀግኖች አባቶቻችን እንማር፡፡ የእነሱን መንፈስ ከያዝን ከቶም አንወድቅም! በግፍ የታሰሩት እንዲፈቱ እንታገል፤ ቤተሰቦቻቸውንና ሌሎችን ታጋዮች እንደግፋቸው፤ ዋናው ጥያቄያችን በ”የታሰሩት ይፈቱ” እንዳይታጠርና መስመሩን እንዳይስት፣ የተነሱለትን ዓላማ አንግበን እንታገል፤ ወንድሞቻችን የምናከብራቸውና ሕዝባችን ነጻ የሚወጣው የተነሱለትን ዓላማ ይዘን ትግሉን ስናቀጣጥለው ነው።

No comments:

Post a Comment