Monday, August 1, 2016

በጎንደር ከተማ የተካሔደውን የዐማራ ተጋድሎ ዓላማውን ለመሸፋፈን የቀረበ በማር የተለወሰ መርዝ

በጎንደር ከተማ የተካሔደውን የዐማራ ተጋድሎ ዓላማውን ለመሸፋፈን የቀረበ በማር የተለወሰ መርዝ MULUKEN TESFAW
· ኢቢሲ በዚሁ መሠረት ዜና ሰርቶበታል
(ይህን ጽሑፍ እያነበባችሁ በምትችሉት ሁሉ በትኑት)
ይህን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ብዙ ተጨንቄያለሁ፤ ሆኖም በቀጣይ የዐማራውን ትግል ለመጥለፍ የሚፈልጉ ኃይሎች ‹‹አውቀናል›› ካላሏቸው የማይተኙ ሆነው በመገኘታቸው ይህን መልእክት ለማዘጋጀት ወሰንኩ፡፡ በማንኛውም መልኩ የዐማራውን ሕዝብ ትግል የሚጎዳ እንቅስቃሴ ላይ በሕይወት እስካለሁ አልታገስም፤ ለዚህም ነው ይህን ጦማር ያዘጋጀሁት፡፡
በጎንደር ከተማ የተካሔደውን ሰልፍ ወያኔ ሊቀር እንደማይችል የዐማራውን ቁርጠኛነት ካየ በኋላ አስቀድሞ ያውቅ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በአንድ በኩል ‹‹አልተፈቀደም›› እያለ በማስፈራራት በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹እቅድ ለ›› የሚባለውን መርሐ ግብር ነድፎ መንቀሳቀስ የጀመረው ሰልፉ ሊካሔድ አንድ ሳምንት ሲቀረው ጀምሮ ነበር፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋነኛ ማጠንጠኛም ስለ ‹‹እቅድ ለ›› በማር የተለወሰ መርዝ መርሐ ግብር ምንነት ማስረዳት ነው፡፡
ሕወሓትን አንድ ነገር ያስፈረዋል፤ እርሱም የዐማራ የማንነት ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ማንነት ጥያቄ እንዲደፋፈን በእጅጉ ይፈልግ ነበር፡፡ ይህን የወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ማንነት ጥያቄ ላለማጉላት ሌላ ማኅበረሰባዊ ችግር እንዲጎላ ማድረግ ወሳኝ ዓላመው አደረገ፡፡ ይህን ዓይነት የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን በሰፊው ማስተጋባት በሌላም መልኩ ቢሆን ለሕወሓት ይጠቅመው ነበር፡፡ ምናልባትም ግጭት ቢፈጠር የተያዙ መፈክሮችን እንደ ናሙና በመውሰደ ‹‹የአሸባሪ ኃይሎች›› ዓላማ ነው በማለት በጅምላ ሕዝብ ለመጨፍጨፍ ወይም የወልቃይት የዐማራ የማንነት ጥያቄን ለመደበቅ አመቺ አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ ይህ እቅድ ለሕወሓት ሦስተኛም ጥቅም አለው፤ እርሱም በሰልፉ ላይ እንዲነሱ የተደረጉ መፈክሮችን የሚቃወሙ አካላት ከመጡ ከአሮሞው እና ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጋር ለማጋጨት በር ይከፍትለታል፡፡
በዚህ ሁኔታ የሰልፉ ቀን ደረሰ፤ የወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢዎች ደጋፊ አካላት የዐማራውን በደል በዝርዝር ጽፈው ስለወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ማንነት ጥያቄ ብሎም ስለታሰሩት የኮሚቴው አባላትና የወልቃይት ጠገዴ ዐማሮች ጉዳይ መፈክሮችን ያዘጋጁ ጀመር፡፡ ሕወሓትም እዚህ ላይ ጎን ለጎን ሥራውን ጀመረ፡፡
የትግሬው ጠባብ ቡድን ያደረገው የሚከተለውን ነው፡፡ ጎንደር ተወልደው ያደጉ የትግራይ ተወላጆችን በተለይም ደግሞ ‹‹እኔ ጎንደሬ እንጅ ዐማራ ወይም ትግሬ አይደለሁም›› የሚሉ የአገር አንድነት ፈላጊ የመሠሉ በምንም የማይጠረጠሩ በገዥው ቡድን ‹‹ተቃዋሚ›› ተብለው የተፈረጁ ግለሰቦችን መረጠና ከፍተኛም በጀት መደበ፡፡ እነዚህ የተመረጡ ግለሰቦች (ቡድን) የአገር አንድነትን የሚሰብኩ የሚመስሉ ሆኖም ግን አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ያዘጋጀው የሚመስሉ ‹‹ጥሩ ጥሩ›› መፈክሮችን አሳተሙ፡፡
እነዚህ መፈክሮች ከሰልፉ አስቀድመው እየወጡ ሲበተኑ የሰላማዊ ሰልፉን የሚያስተባብሩትን አካላት በስልክ ጠየቅኩ፤ እነርሱም እንደማያውቁ ሆኖም ይህ እየተደረገ ከሆነ ሆን ተብሎ የማንነት ጥያቄያችን ለማዳፈን የተደረገ ሴራ ሊሆን እንደሚችል ገለጹልኝ፡፡
Muluken Tesfaw's photo.
መፈክሮቹ በትግሬዎች መታተማቸውን ለማስረዳት ያክል አንዱን እንመልከት፡፡ በዚህ ቡድን ከተዘጋጁት መፈክሮች አንዱ ‹‹ሀፍታሙ ሆይ ከጎንህ ነን›› ይላል፡፡ ‹‹ሀብታሙ›› የሚለውን መፈክሩን እንዲያሳትም የተነገረው ትግሬ በሚያውቀው ቋንቋ ‹‹ሀፍቶም›› ከሚለው ጋር ተመሳስሎበት ይሆናል፡፡
‹‹በኦሮሚያ የሚደረገው የወንድሞቻችን ግድያ ይቁም፤ የሕዝብን ጥያቄ መጠየቅ ሽብርተኛነት አይደለም፣ ስብሀት ሆይ ኢትዮጵያ አትፈርስም!! አንተና ማፍያው የሕወሓት ቡድን ታሪክ የምትሆኑበት መባቻ ላይ መሆናችሁን እወቁ›› ወዘተ የሚሉ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ልብ አድርጉ!
ሰልፉ የተጠራው ለምንድን ነው? ይህ ሰልፍ የተጠራው የወልቃይት ጠገዴ የዐማራ የማንነት ጥያቄን ለማስተጋባት ብቻ ነው፤ ሌላ ከፍም ዝቅም የሚል ዓላማ አልነበረው፡፡ የዐማራ ሕዝብ ችግሩ ይህ ብቻ ነው ወይ? የሚል አንባቢ አይጠፋም፡፡ የዐማራ ሕዝብ ችግር በአንድ ሰልፍ አይደለም አንድ ዓመት ተሰልፈን ጮኸን የማንጨርሰው ችግር አለብን፡፡ እርሱን ማንም ያውቃል፡፡ ግን ሁሉንም በአንድ ጊዜ ማድረግ ከምንም ሳይሆኑ መቅረትና ሀሳብን በታትኖ የቁራ ጩኸት ማድረግ ነው፡፡
ከላይ እንደገለጽኩት የቀረቡት መፈክሮች በሙሉ ችግር የለባቸውም፤ ችግሩ ያለው የዐማራውን ተጋድሎ አቅጣጫ ለማስቀየር የተደረገው ጥረት ነው፡፡ ይህን እንደተገነዘብኩ በዜና መልክ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ለማስተላለፍ ሞከርኩ፡፡ ከዚያም አልፎ ይህን እየበተኑ ያሉ አካላትን እንዲያቆሙ ወይም ምክንያታቸውን እንዲገልጹልኝ ጠየቅኩ፡፡ ሆኖም እኔን ብቻም ሳይሆን ለዐማራው ሕዝብ ሌት ተቀን እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላትን ሁሉ በስድብ መሞለጭ ሆነ መልሱ፡፡ የኢሳትን ባልደረቦች ያለውን ሴራ አስረድቼ የዐማራውን ሕዝብ ጥያቄ ትኩረት እንዲያደርጉም ሞከርኩ፡፡ ሆኖም እንዲያውም ያን በተመለከተ የሰጠሁት አስተያየት ተቆርጦ ሳይተላለፍ ቀረ፡፡
እነዚህ አካላት ሌላው የሠሩት ደባ ከላይ የተገለጹትን መፈክሮች ያሉበትን የሰላማዊ ሰልፍ አካባቢ ብቻ እየቀረጹና ፎቶ እያነሱ በተከታታይ ለኢሳትና ለአንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች ቶሎ ቶሎ ማስተላለፍ ያዙ፡፡ ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩ የኢሳት ባልደረቦች አንድም የእኔን ሀሳብ ባለመረዳት አሊያም ባላወቅኩት ምክንያት በዚህ የወያኔ መረብ ውስጥ በቀላሉ ወደቁ፡፡
በዚህ ጮቤ የረገጠው የትግሬ ማፍያ ቡድንም ምሽቱን እነዚህን ጉዳዮች ብቻ በማንሳት ‹‹የመልካም አስተዳደርና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች›› ብሎ አታሎ እንዲያልፍ የማርያም መንገድ አገኘ፡፡ እርግጥ ነው ሰልፉ በዚህ መልኩ አሰናካዮች ቢበዙበትም ዓላማውን የመታ እንደነበር ለመናገር እወዳለሁ፡፡
ሌላው የዐማራውን አንድነት የማይወዱ ከጠባብ ትግሬዎች ውጭ የሆኑ ብዙ አካላት እንዳሉ ማስመር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ቡድኖች ከወያኔ እኩል የዐማራው ጠላቶች መሆናቸው እናውቃለን፤ ወደ ፊት እኩል ከወያኔ ጋር የምንዋጋቸው ይሆናል፡፡ ለዛሬ ግን ትንሽ ጣል አድርጌ ጽሑፌን መደምደሙ የተሻለ ይሆናል፡፡
Muluken Tesfaw's photo.
የኦሮሞ ወንድሞቼን በጣም ከማደንቅበት አንዱ ትግላቸውን ለማኮላሸት የሚመጣን ማናቸውን ዓይነት ኃይል አይታገሱም፡፡ በዐማራው ትግል ላይ ግን ማንም ፌስ ቡክ የከፈተ ሁሉ እንደ እርጎ ዝምብ ጥልቅ ይልበታል፡፡ ይህ የዐማራውን ሕዝብ የመቻልና ለአገር አንድነት ያለውን ሥነ ልቦና ተጠቅመው የዐማራውን የነጻነት ጉዞ የኋሊት እየጎተተው ይገኛል፡፡ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ ዛሬ በተለያዩ ከተሞች የዐማራ የተጋድሎ ሰልፎች ተካሒደዋል፡፡ ሆኖም የዐማራውን አንድነት የማይፈልጉ ኃይሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ሀሽ ታግ ሲያደርጉ ‹‹የዐማራ ተጋድሎ›› ማለት አይፈልጉም፡፡ ዐማራ የሚውን ቃል እንደ አንዳች ነገር ወይ ይፈሩታል፤ አሊያም ባላቸው ውስጣዊ የተደበቀ ጥላቻ ይጠየፉታል፡፡ ስለሆነም ዐማራ ከማለት ‹‹የጎንደር ተቃውሞ›› ማለትን ይመርጣሉ፡፡
ከኦሮሚያው ተቃውሞ ጋር አነጻጽረው ለመግለጽ ሲፈልጉ እንኳ የሚጠቀሙት ‹‹በጎንደር እና በኦሮሚያ›› ብለው ነው፡፡ እዚህ ላይ ከሁለቱ ላንደኛው ያላቸው አመለካከት እጅግ የተዛባ እንደሆነ ማየት ቀላል ነው፡፡ ኦሮሞን የሚመጥነው ዐማራ የሚለው የሕዝብ ስም ነው፡፡ ጎንደር የቦታ እንጅ የማንነት መጠሪያ አይደለም፡፡ ጎንደር እንደ ሐረር አሊያም እንደ ወለጋ የአንድ የቦታ ስም ነው፡፡ ሰሞኑን በሐረርጌ የሚካሔደውን የኦሮሞ ተቃውሞ ‹‹የሐረርጌ ተቃውሞ›› ብሎ አንድ ሰው ሀሽ ታግ ሲያደርግ አላየሁም፡፡ ቢያደርግ ደሞ ጀግኖቹ የኦሮሞ ልጆች ‹‹እጅህን አንሳ የማታውቀውን አትዘላብድ›› ማለታቸው አይቀርም፡፡ በእርግጥ ቁርጠኞቹ የዐማራ ወጣቶች ከዚህ በኋላ ማንንም አይታገሱም፡፡
በመጨረሻም እንደዚህ ያለ በማር የተለወሰ መርዛማ ሴራ የሚሸርቡ ብሎም የዐማራውን ተጋድሎ ወደ ኋላ ለመጎተት የሚሞግቱ አካላትን በተቻለን መጠን ሁሉ ሳናሳልስ እኩል ከወያኔ ጋር መዋጋት እንዳለብን ለሁሉም የዐማራ ወጣቶች ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡
ይህ ሁሉ ግን የመጨረሻው መጀመሪያ ነው፤ የዐማራ ሕዝብ ትግል ያሸንፋል

No comments:

Post a Comment