ሐምሌ 27/2008 የወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ “ በሚል ርእስ ሥር፣ የወያኔው ተላላኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብዬ፣ ባህር ዳር ከተማ በተካሔደው የዲያስፖራ ቀን ተገኝቶ፣ “የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ የሕዝብ ሳይሆን የጥቂት አመራሮች ችግር ነው” ማለቱን ነግሮናል፡፡ ይህ ግለሰብ ይህን የሚሰለ የተንሸዋረረ አስተያየት እንዲሰጥ ያደረገው አሳዳሪዎቹን ለማስደሰት ያለው ከፍተኛ ፍላጎት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በርካቶች የሞቱለትንና ከፍተኛ መስዋዕትነት ሲከፍሉለት የቆዩትን ጥያቄ፣ ይህን ነውረኛ ንግግር ከማድረጉ ከሁለት ቀን በፊት በሺሕዎች የሚቆጠሩ አማሮች ተሰልፈው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያሰሙለትን ጥያቄ፣ በርካቶች እስር ቤት ገብተው የግፈኛው ቡድን የቶርቸር ሰለባ በመሆን ላይ የሚገኙበትን የሕዝብ ጥያቄ የጥቂት አመራሮች ጥያቄ ነው ማለቱ የሚያስቆጣ ቢሆንም፣ አስተያየቱ የተሰጠው በአንድ ተራ የወያኔ ተላላኪ ግለሰብ በመሆኑ፣ እሱን ተሻግረን ማተኮር ያለብን በዋናው ጠላታችን ላይ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ተብየው በማን እንደሚዘወርና ማንን እንደሚያገለግል ለአማራ ሕዝብ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፤ በዚህ ገልቱ ግለሰብ አስተያየት ላይ መወያየትም እርባና የለውም፡፡ የእኛ አጀንዳ ግፈኛው የሕወሓት ወሮበላ ቡድን የአማራን ሕዝብ ጥያቄ ለማኮላሸት ምን ያህል ሊሠራ እንደሚችል፣ ለዚህ ደግሞ ክልሉን አስተዳድራለሁ የሚለው ብአዴን በተባለው የሕወሓት ቅምጥ ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ አመራርነትና በዘዋሪነት የተቀመጡት እንደበረከት ስምኦንና ካሳ ተክለ ብርሃን ያሉ የአማራ ሕዝብ ደመኞች ምን ያህል በተለመደው የጥፋት ተግባራቸው ሊገፉበት ቆርጠው እንደተነሱ ከሕዝባችን ጋር መወያየት፣ መተንተንና አቅጣጫ ማስቀመጥ ነው፡፡
በሕወሓት ሠራዊትና የደኅንነት አካላት እየተዋከቡም ቢሆን ሕዝባቸውን ለማገልገል የቆረጡ በርካታ የብአዴን አባላት እንዳሉ ጥርጥር የለውም፡፡ እነዚህን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እናከብራቸዋለን፤ እንደግፋቸዋለን፡፡ ይሁን እንጂ ከወሮበላው ሕወሓት ጋር አንድና ያው ሆነው ብአዴንን የሚያሽከረክሩት እንደ በረከት ስምኦን፣ ካሳ ተክለብርሃንና ታደሰ ካሳ ያሉት ምንደኞች በመሆናቸው፣ ብአዴን ራሱን ከሕወሓትና ከእነዚህ የሕወሓት መሣሪያዎች ነጻ አውጥቶ ለአማራ ሕዝብ ይቆማል ማለት አይቻልም፤ ተግባሩ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡
ለዚህ ነው ትግሉ መራራና እልህ አስጨራሽ መሆኑን ማወቅ የሚገባን፡፡ ትግሉ መራራ ቢሆንም የገባንበትን አስከፊ ሁኔታ ተረድተን እንደ ሕዝብ ከተንቀሳቀስን ግን የማንወጣው አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ የትግል ስትራቴጂያችን ወዳጅና ጠላትን በሚገባ የለየና ጥራት ያለው እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ስኬታችንም ውድቀታችንም በዚህ ስትራቴጂያችን ድክመት ወይም ጥንካሬ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment