የአሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር አቋምን በዜሮ? 38 ቢሊዮን ዶላር ያልበቃዉ የእስራኤል እሮሮ? በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመፍትሄ ሐሳብና መመሪያ 2334 ይታይ ይሁን ተቀይሮ?
በሳዲቅ እህመድ
አረብ ከሆነችዋ ፍልስጤም ጎን ለጎን አይሁዳዊቷ አገር እስራኤል ትዋቀር ዘንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በኅዳር 20/1942 (November 29, 1947) ድምጽ ሰጥቶበታል።ከ69 አመታት በሗላ በታኅሣሥ 14/2009 የተባበሩት መንግስታት የጸጥታዉ ምክር ቤት ቀደም ሲል የነበረዉን ዉሳኔ ዳግም ለማቆየት ድምጽ ሰጠበት።መመሪያ (የመፍትሔ ሐሳብ) 2334 ይፋ መደረጉን በማጤን ሐሳባቸዉን የሰጡት ሐዓሬት በመባል ለሚታወቀዉ የእስራኤል ጋዜጣ የሚጽፉት ጊዲኦን ሌቪ “ባለፉት አመታት ዉስጥ ከነበረዉ የተስፋ መቁረጥና የጨለማ ባህር ተፈንጥቆ የወጣ የተስፋ እስትንፋስ!” ሲሉ ገልጸዉታል።
እስራኤላዊዉ ጸሃፊ ጊዲኦን ሌቪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታዉ ምክር ቤት ይፋ ያደረገዉ መመሪያ በቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አመራር እክል ሊገጥምነዉ እንድሚችል እያመላከቱ የስራ ዘመናቸዉን በመጨረስ ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ኦባማን “ይህንን በስንብት ወቅቶ ላይ ያደርጋሉን?” ስንል በቁጣ መጠየቅ አለብን ይላሉ። እንደ ጊዲኦን ሌቪ አገላለጽ ኦባማ ይህንን ቀደም ሲል ሊያደርጉ ይገባ ነበር። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንያሚን ናትንያሆና ካቢኒያቸዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታዉ ምክር ቤት ያወጣዉ መመሪያ ተገቢ እንዳልሆነ የተቃዉሞ ድምጽ በሚያሰማበት ወቅት የእስራኤል ሚዲያዎች መመሪያዉ ጸረ እስራኤል ነዉ ሲሉ የፕሮፓጋንዳ ስራ ላይ እንደሚሰማሩ አሳዉቀዋል ጊዲኦን ሌቪ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰጥታዉ ምክር ቤት በታኅሣሥ 14/2009 ያወጣዉ የመፍትሔ ሐሳብ ለእስራኤል ከወትሮዉ የተለየ ነበር። እስራኤል በሐይል በያዘቻቸዉ የፍልስጤም ይዞታዎች ላይ የምታደርገዉን መስፋፋት አዉግዟል። እስራኤል የምታደርገዉ ሰፈራ ህገወጥ ነዉ ሲልም አረጋግጧል።ማንኛዉም የመስፋፋትና የሰፋራ እንቅስቃሴ እስራኤል ታቆም ዘንድ አሳስቧል።እስራኤል ለብቻዋ የምታደርገዉን የድንበር መስፋፋትና የምስራቅ እየሩሳሌምን ወደራሷ መጨመሯን ዉድቅ አድርጎታል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታዉ ምክር ቤት ለሚያወጣቸዉ መመሪያዎችና ደንቦች ደንታ ቢስ እንደሆነች የምትታወቀዋ እስራኤል የዘንድሮዉ ዉሳኔን እንደስጋት ተመልክታዋለች። ቀደም ሲል አሜሪካ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ማንኛዉንም እስራኤልን የሚቆርቁር ነገር ከማለዘብ አልፋ ታከሽፍ እንደነበር ይታወቃል። በዘንድሮዉ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታዉ ምክርቤት የድምጽ አሰጣጥ ሒደት ላይ አሜሪካ ድምጸ ተአቅቦ በማድረጓ ማሌዥያ፣ቬንዝዋላ፣ሴኔጋልና ኒዉዝላንድ ያቀረቡት ረቂቅ ሐሳብ አስራ አራት ለዜሮ በሆነ ከፍተኛ ድምጽ በማለፉ የእስራኤል ባለስልጣናት ከጎናቸዉ ያልቆሙትን ፕሬዝዳንት በራክ ኦባማ በግልጽ እስከመዛለፍ መድረሳቸዉን ለማወቅ ተችሏል።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ኦባማ ለናታንሆ የሰጡት የስንብት ስጦታ ሲሉ ተሳልቀዉባቸዋል። አይሁዳዉያን ለሰላም በሚል መጠሪያ ለፍልስጤማዉያን መብት የሚከራከሩ ቡድኖች ዉሳኔዉን ተገቢ ሲሉ አድንቀዉታል። ለኦባማ አመራር ተገቢዉን ክብር የማይሰጡት ናታንያሆ በጸጥታዉ ምክር ቤት የእስራኤልን የመስፋፋትና የሰፈራ ተግባር ህገወጥ ብለዉ ድምጽ ከሰጡ አገራት ጋር የሚኖረዉ የስራ ግንኙነት በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴራቸዉ በኩል የላላ እንደሚሆን አሳዉቀዋል።
የጸጥታዉ ምክር ቤት ያወጣዉን መመሪያ በማርቀቁ ረገድ ግብጽ ተሳታፊ ነበረች። ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለግብጹ የመፈንቅለ መንግስት መሪ ጄኔራል አብዱል ፈታህ አልሲሲ ስልክ በመደወላቸዉ ሳቢያ ግብጽ ረቂቁን ማቅረቡን ትታ አፈግፍጋለች። በአገሩ ብሎም በአረቡ አለምና በሙስሊሙ አለም ተወዳጅ ያልሆነዉ የጄኔራል አልሲሲ መንግስት ያደረገዉ ማፈግፈግ የበለጠ እንዲጠላ አድርጎታል። በጠቅላይ ሚኒስቴር ነጂብ ረዛቅ የሚመራዉና በርካታ አገራዊ ፈተናዎችን እየተጋፈጠ ያለዉ የማሌዥያ መንግስት የግብጽን ቦታ በመተካት የፍልስጤማዉያን አጋር ሆኗል።
በአይሁዳዉያን አሜሪካዉያን የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ጥቅም አስከባሪዎች (Lobbying) አማካኝነት አሜሪካን ወዳሽት አቅጣጫ ትመራ የነበረቸዉ እስራኤል በኦባማ የስራ ዘመን ማብቂያ ወቅት አልተሳካላትም።ከምርጫ ዘመቻ ( Presidential Campaign) ግብረሐይላቸዉ ዉስጥና ሁለት ግዜ ፕሬዝዳንት እስኪሆኑ ድረስ በካቢኔያቸዉ ዉስጥ አይሁዳዉያን አሜሪካዉያንን በቁልፍ ቦታ ያስቀመጡት ኦባማ የሚያደርጉት ምርጫ ባለመኖሩና የታሪካቸዉን ምእራፍ (legacy) ለማሳረግ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዉስጥ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑትን ሳማንታ ፓወር አዘዉ አሜሪካ ባልተጠበቀ መልኩ ከእስራኤል ሳትወግን ድምጸ ተአቅቦ አድርጋለች። አዲሱ የጸጥታዉ ምክርቤት መመሪያና የመፍትሔ ሐሳብ ተግባራዊነት በሒደት የሚታይ ቢሆንም ለእስራኤል የእግር እሳት የሆነባት ”እንዴት እንደፈራለን?” የሚለዉ የበላይነት ስሜት እንደሆነ እየተስተዋለ ነዉ። አንዳንድ የእስራኤል ዜጎች ከሙስሊም አባት የተወለዱትን በራክ ሁሴን ኦባማ “ሁሴንነቱ መጣበት” በማለት ማብጠልጠል ጀምረዋል።
አዲሱ የጽጥታዉ ምክር ቤት 2334 የመፍትሔ ሐሳብና መመሪያ እስራኤል በሐይል የያዘቻቸዉን የፍልስጤም ይዞታዎች ተገቢ አለመሆኑን አይደሉም ያትታል።እስራኤል በአይሁድ ሰፈራ ስም የምታደርገዉን መስፋፋት ህገወጥ ነዉ ብሎ ይደመድማል።
የእስራኤል መንግስት ለአለምአቀፍ ህጎች ተገዢ ሊሆን ቀርቶ…አለም አቀፍ ህግ እንደሚመለከተዉ ማስመሰል ባቆመበት፣ የፍልስጤማዉያንን መሬትን በግልጽ መስረቁን ህጋዊ አስመስሎ ሲሰራ፣ የእስራኤል ካቢኔ አባላቶች የሁለት ግዛቶች መፍትሔን በመተዉ በዉስጧ የአረብ ዜጎች ያሏትን አንዲት እስራኤል ለማዋቀር እምደሚሹ ሲናገሩ፣ ስልጣኑን ሊያስረክብ ሳምንታት የቀሩት የኦባማ ካቢኔ እና አለም አቀፉ ማህበረሰብ እኛም የፍልስጤም ጉዳይ ያገባናል በማለት የላኩት መልእክት ነዉ ሲሉ ማይክል እስካፈር ኡመርማን የተባሉ ጸሃፊ የጽጥታዉ ምክር ቤት 2334 የመፍትሔ ሐሳብና መመሪያ አስመልክቶ ከእስራኤል ሐሳባቸዉን በጽሁፍ አስፍረዋል።
ማይክል ኡመርማን አክለውም እስራኤል በዌስት ባንክ የምታደርገዉን መስፋፋትና ህገወጥ ተግባር አስመልክቶ ከአዉሮፕያዉያን አገራት የሚደርስባትን ጫና ለመመከት ምእራባዉያኑን አንፈልግም ከሩስያ፣ከቻይና፣ከህንድና ከተወሰኑ የፍሪካ አገራት ጋር እተባበራለሁ የሚል ፖሊሲን ተግባሪ መሆን መጀመሯን ይገልጻሉ። እስራኤል ፖሊሲዋን ብትቀይርም አለም በእስራኤል የመስፋፋት ሰፈራ ላይ ያለዉ አቋም የሚቀየር አለመሆኑን አመላክተዋል።የጸጥታዉ ምክርቤት አዲሱ መመሪያ እስራኤልን በጣሙን ሊያሰጋት ከሚችልበት ምክያቶች አንዱ አለምአቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (https://www.icc-cpi.int/)ከእስራኤል ሰፈራና መስፋፋት በተገናኘ መልኩ እስራኤል የጦርነት ወንጀል ፈጽማለች የሚል የክስ ፋይል ሊከፈትባት መቻሉ ነዉ። ይህ ደግሞ የእስራኤል ፖለቲከኞችና የጦር መኮንኖች የወንጀል ምርመራ እንዲደረግባቸዉ የሚያስችል በመሆኑ ለእስራኤል ባለስልጣናት የሚመች አለመሆኑን ጸሃፊዉ ኡመርማን ከእስራኤል ገልጸዋል።
እስራኤል ለሚቀጥሉት አስር አመታት ወታደራዊ አቅሟን የበለጠ ታደራጅ ዘንድ ከኦባማ ካቢኒ 38 ቢሊዮን ዶላር ተመድቦላታል። ይህንን ታላቅ የእርዳታ አሃዝ አሜሪካ ለሌላ አገር በታሪክ ሰጥታ የማታውቀዉ መሆኑን ተንታኞች ያስረዳሉ። በአመት ለእስራኤል 3.8 ቢሊዮን ዶላርን ያጸደቀዉ የኦባማ አስተዳደር የስልጣን ዘመኑ ሊገባደድ ሳምንታት ሲቀሩት በጸጥታዉ ምክር ቤት በኩል ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቱን ሳይጠቀም በድምጸ ተአቅቦ ከእስራኤል ጋር አለመቆሙ “ኦባማ ከጀርባ ወጉን” ብለዉ የእስራኤል ባለስልጣናት እንዲማረሩ አድርጏቸዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንያሚን ናታንያሆ ተኮሳትረዉና ተቆጥተዉ “ለረጅም ግዜ ከወዳጃችን አሜሪካ ጋር የምናደርገዉን ሰፈራ አስመልክቶ የሐሳብ ልዩነት አለን፣ ይህንን የሐሳብ ልዩነት ግን አብረን ልንፈታ ይገባ ነበር፣ወዳጅ ወዳጅን ጸጥታዉ ምክር ቤት አይወስድም፣በጸጥታዉ ምክር ቤት በኩል መፍትሔ እንደማይመጣ ተነጋግረናል፣ ቢሆንም ግን ከሚቀጥለዉ የትራምፕ አመራርና ፓርላማ ዉስጥ ካሉ እንደራሴ ወዳጆቻችን ጋር አብረን በመስራት እናስተካክለዋለን” ብለዋል።
ብዙ አሜሪካዉያንና ለሰላም የሚታገሉ አይሁዳዉያን አሜሪካ እስከመቼ የእስራኤል ሞግዚት ሆና ትቀጥላለች? እስከመቼ የቀረጥ ከፋዮች ገንዘብ ላንዲት አገር ይርከፈከፋል?እስከመቼ አገራችን አሜሪካ በዲፕሎማሲና በደህንነት ጉዳዮች ለእስራኤል ስትል ፈተናን ትጋፈጣለች? በማለት ይናገራሉ።እስራኤል ዉስጥ ያሉ የናታንያሆ ተቀናቃኞች በበኩላቸዉ የቀኝ ክንፍ አክራሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስቴር አገራቸዉን በዲፕሎማሲና በጽጥታ ጉዳይ አጣብቂኝ ዉስጥ እየከተቱ መሆኑን በስጋት ያስረዳሉ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታዉ ምክር ቤት አምስት ቋሚ አባላት አሉት። አምስት ታላቆች በመባል የሚታወቁት ዩናይትድ እስቴትስ፣ሩስያ፣ቻይና፣እንግሊዝና ፈረንሳይ ሲሆኑ ሌሎች ቋሚ ያልሆኑ አስር ተለዋጭ አባላት አሉት። የነዚህን አባላት ድምጽ አንቀበልም ያሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢንያሚን ናታንያሆ እስራኤል በዌስት ባንክ የምታደርገዉን ህገወጥ ሰፋራ አስመልክቶ ድምጽ ከሰጡ 12 አገራት ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዉስን እንዲሆን አዘዋል ሲል ሲል ሲ.ኤን.ኤን የእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። ይህም እርምጃ እስራኤልን ከአለም አቀፉ የዲፕሎማሲ መድረክ እራሷን በራሷ የበለጠ እንድታገል የሚያደርግ መሆኑን እስራኤላዉያን ሳይቀሩ ቢያስረዱ የእስራኤል ባለስልጣናት አሻፈረን ብለዉ ዛቻቸዉን ቀጥለዋል።
የህዝብ ብዛቷ ስምንት ሚሊዮን የሆነው እስራኤል እንደምን ከአለም ጋር ተናቁራ የዜጎቿን ደህንነት ታስጠብቃለች? የሚለዉ ጥያቄ ሁሌ የሚነሳ ቢሆንም የቀኝ ክንፍ አክራሪ የሆነዉ የናታንያሆ መንግስት ለአለም መንግስታትና ለአለምአቀፍ ህጎች ደንታ ቢስ መሆኑን እያሳየ ነዉ። አሜሪካዊዉ ጋዜጠኛ ቤን ዋይት አለም በእስራኤል ላይ ያለዉን አቋም ማጠንከር ይገባዋል ጥንካሬዉ በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባርም መሆን አለበት በማለት ጽፏል። ቤን ዋይት ቀጣዩና አዲሱ አመት እስራኤል አገር አልባ በሆኑት ፍልስጤማዉያን ላይ በዌስት ባንክና በጋዛ ሰርጥ እያደረገቸዉ ያለዉ ወታደራዊ አፈና 50 አመት ይሞላዋል ሲል እያስረዳ አንዲት አፈንጋጭ አገር በዘረኝነትና ከፋፍሎ በመግዛት የምታደርገዉ ጭቆና መቆም አለበት ሲልም ያስረዳል።
ሐአሬት የሚባሌዉ የእስራኤል ሊበራል ጋዜጣ በታህሳስ 18/2009 ባወጣዉ ርእሰ አንቀስ ናታንያሆ እስራኤልን ወደታች እያዘቀጧት ነዉ ብሏል።ናታንያሆ ያለዉን የዉይይት መስመር በሙሉ እየዘጉ ነዉ ያለዉ ጋዜጣ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የገጠማቸዉን የጸጥታዉ ምክር ቤት ዲፕሎማሲያዊ ሽንፈትን ጠቅሶ ግትር የሆኑት ናታንያሆ ከሌሎች አገራት ጋር ያለዉን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየደረመሱ መሆኑን አስረድቷል። ከእስራኤል ጋር ወዳጅ የሆኑ አገራት በድፍረት የእስራኤልን ህገወጥ ሰፈራና መስፋፋት በመቃወም ድምጽ መስጠታቸዉ
ሐአሬት እየገለጸ ናታንያሆ ዲፕሎማሲያዊ አሰራርን ትተዉ አለም አቀፋዊ ህግን አደገኛ በሆነ መልኩ ችላ እያሉ መሆኑን በርእሰ አንቀጹ ላይ ገልጿል።
አያሌ አመታትን ያስቆጠረዉ የፍልስጤምና የእስራኤል ግጭት የሟቾች ቁጥር የሚቆጠርበት ቢሆን እንጂ እልባት አላገኘም። በሁሉም አቅጣጫ ያሉ የሰላም ድምጾች ሲታፈኑ ይስተዋላል። የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ጫናዎች መሰረታዊ ለዉጥ አላመጡም። በሁለት ጎራ ያሉ ሐይላት እኔ ትክክለኛ ነኝ በማለት ፍልሚያ ዉስጥ ይገኛሉ። እስራኤል በምታደርገዉ የመስፋፋትና የሰፈራ ፕሮግራም ፍልስጤማዉያንን እያፈናቀለች ካገራቸዉና ከቀዬ አቸዉ እንዲሰደዱ ማድረጉን ተገቢ አድርጋ እየቀጠለች ባለችበት ወቅት አለም አቀፉ ማህበረሰብ በጸጥታዉ ምክር ቤት በኩል በቃሽ የሚል ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማስደር ሞክርሯል።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ናታያሆ የሚመራዉ መንግስት የጸጥታዉ ምክርቤት የመፍትሔ ሐሳብን አሻፈረኝ በማለት በተለያዩ አገራት ላይ ጣቱን እየጠቆመ ነዉ። ባንድ ወቅት ጥቁሩን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቸል በማለትና ያለ አሜሪካዉ ቤተ-መንግስት እውቅና ዋሽንገተን ዲሲ መጥተዉ በዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ቀላዋጭነት ንግግር ያደረጉት ቤን ያሚን ናታንያሆ ከጥቁሩ ፕሬዝዳንት ጋር የጎሪጥ እንደሚተያዩና እንደማይስማሙ በስፋት ይዘገባል። በኦባማ ካቢኒ ለአስር አመታት የጸደቀላቸዉን 38 ቢሊዮን ዶላር ሳይበቃቸዉ አሜሪካን በጸጥታዉ ምክርቤት ያላትን ድምጽ በድምጽ የመሻር መብት በምርቃት እፈልጋለሁ ያሉት ቤን ያሚንንናታያሆ ለግዜዉ ምርቃቱን አላገኙትም። ያገኙት ነገር ቢኖር የኦባማ የስንብት ስጦታ ነዉ። ናታንያሆ አሻፈረኝ ብለለዉ እየዛቱ ነዉ። የቲዊተሩ ዲፕሎማትና አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቃለ መሃላ የምፈጽምበት ጥር 12/2009 ይድረስ እንጂ ሁናቴዎች ይቀየራሉ በማለት ኦባማን ማብጠልጠል ጀምረዋል።
እምቢተኛዉ ቢን ያሚን ናታንያሆ ድምጽ በሰጡ አገራት ላይ ጣት መጠቆማቸዉን ቀጥለዋል።ለመሆኑ በአለም ህዝብ ላይ እስከመቼ በእብሪት ይዛታል? የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነዉ። በርግጥ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታዉ ምክር ቤት የመፍትሔ ሐሳብና መመሪያ 2334 ተግባራዊ ይሆናልን? በሒደት የሚታይ ይሆናል። ሳዲቅ አህመድ ነኝ! ልብ ያለዉ ልብ ይበል።