Sunday, January 1, 2017

“ለህዝቧ የተመቸች ሀገር መገንባት አለብን” አቶ ቡልቻ ደመቅሳ


• የፌዴራል ስርአቱ የአባልነት እንጂ የአንድ አገዛዝ ባህሪ ሊኖረው አይገባም
• አሁን ያለው የዲሞክራሲ መጠን ለብዙ ሰው አልተስማማም
• ተቃዋሚዎች የደቀቁት ለሃገር የሚበጅ ሃሳብ አጥተው አይደለም፤ ገንዘብ ስለሌላቸው ነው
አዲስ አድማስ  – አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ከነበሩ የኦሮሞ ተወላጆች አንዱ ሲሆኑ በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ በምክትል ሚኒስትርነት አገልግለዋል፡፡
የአብዮቱን መፈንዳትና የደርግን ወደ ሥልጣን መውጣት ተከትሎም ባህር ተሻግረው አሜሪካ ገቡ። እዚያም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለ25 ዓመታት ሰርተዋል፡፡ ከደርግ ውድቀት በኋላ ወደ ሀገር ቤት የተመለሱት ቡልቻ፤ በአገራችን የመጀመሪያውን የግል ባንክ፣ አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ከመሰረቱት ኢንቨስተሮች አንዱ ናቸው፡፡
በፖለቲካው መስክም በተቃዋሚነት ለመሳተፍ የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ፓርቲን መስርተው በ97 ምርጫ በመወዳደር አሸንፈው ፓርላማ ገብተዋል፡፡ ከ5 ዓመት በኋላ ከፓርላማ የወጡት አቶ ቡልቻ፤ፓርቲያቸው ኦፌዴን በዶ/ር መረራ ጉዲና ከሚመራው የኦሮሞ ህዝቦች ኮንግረስ (ኦህኮ) ጋር ውህደት እንዲፈጥር አድርገዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን አልቀጠሉም፡፡ ከፓርቲ አመራርነት ራሳቸውን በማግለል እረፍት መውሰድ ጀመሩ፡፡ በቅርቡ ህመም ጠንቶባቸው በታይላንድ ባንኮክ ህክምና ተከታትለው መመለሳቸውን ይናገራሉ፡፡ አሜሪካም እየተመላለሱ ይታከማሉ፡፡ ዕድሜና ህመም ያደከማቸው ቢመስሉም ‹‹አሁን ደህና ነኝ›› ይላሉ – የ86 ዓመት አዛውንቱ አቶ ቡልቻ፡፡
ከአደባባይ ጠፍተው የከረሙት አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ፤ በቀድሞ የመኖሪያ መንደራቸው ሲኤምሲ ግቢ ውስጥ ከምትገኝ ካፍቴሪያ በረንዳ ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተገናኝተው፣ በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በስፋት አውግተዋል፡፡ እነሆ፡-
ምነው ጠፉ? በሚዲያ እንኳ ብቅ ብለው አያውቁም ?
ኒውዮርክ መኖሪያ አለኝ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እዚያ እኖራለሁ፡፡ አሞኝ ወደ ኤሽያም ሄጄ ነበር፡፡ ባንኮክ ታክሜ ነው የመጣሁት፤ አሁን በጣም ደህና ነኝ፡፡ በፊትም ብዙ አልታመምኩም ነበር፤ እርጅናም ስላለ ክትትል ለማድረግ ነው፡፡
የሀገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እየተከታተሉ ነው?
አዎ! ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ በንቃት ስከታተል ነበር የከረምኩት፡፡
በተለይ ባለፈው ዓመት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተቃውሞዎች—ግጭቶች—አለመረጋጋቶች —ተከስተዋል፡፡ እንደ ፖለቲከኛ ምን ተገነዘቡ?
የታዩት ነገሮች ሁሉ የሚያመላክቱት አሁንም መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አያስፈልግም የሚል ሰው ካለ፣ እንደገና ቢያስብበት መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ የዚህን ሀገር መሪነት ሲቆናጠጥ ብዙ ቃል ገብቷል፡፡ አዲስ ዘመን መጣ፣ ብሎ ህዝቡ በደስታ ተቀብሎት ነበር፡፡ የነገስታት አገዛዝ፣ የአምባገነኖች ዘመን አከተመ ተብሎ፣ ሁሉም ወደ የስራው ይመለሳል ብለን ነበር፡፡ “ዛሬስ ምን ይፈጠር ይሆን?” ከሚል የጦርነትና የግጭት ሰቀቀን ተገላገልን ብለን አምነን ነበር፡፡ በወቅቱም ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል ታይቷል፡፡ በኋላ ግን የማናለብኝነት አሰራር መጣ። እርግጥ ነው ህዝቡ የእነ መንግስቱንም አገዛዝ ያየ በመሆኑ፣ ይሄ ብዙም አልገረመውም ነበር፡፡ እኛ ተምረናል፤ ለህዝባችን ዲሞክራሲ መጣ፣ እኩልነት ፍትህ ሊሰፍን ነው ብለን ተስፋ ላደረግነው ግን ነገሮች እየተቀየሩ ሲመጡ ደነገጥን፡፡ ግማሹ ጥሩ ነው ይላል፤ ሌላው ኧረ አይሆንም እያለ፣ ይሄው 25 ዓመት አስቆጥረናል፡፡ በዚህ መሃል ህዝቡ ከኛ ርቆ ሄዶ ለውጥ ፈልጓል፡፡ ገበሬውም ነጋዴውም ተማሪውም ለውጥ ያስፈልገኛል ያለበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
ምን ዓይነት ለውጥ ነው የሚፈለገው?
ለውጥ ሲባል እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው ባልልም፤ ለምሳሌ ኢህአዴግ ላለፉት 25 ዓመታት ሲስተሙን ሲለውጥና አዲስ ነገር ሲያመጣ አላየነውም፡፡ ለምን አዲስ ለውጥ አያመጣም? እኔ በደንብ የማውቀው የኃይለሥላሴን ዘመን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ ሀገር የሆነችው ኦሮሞዎች ከተጨመሩ ነው፡፡ ኦሮሞዎች ወደ ኢትዮጵያ ከተጨመሩ እንኳ ከ500 ዓመት በላይ ነው፡፡ ከ500 ዓመት ወዲህ እንኳ ብንወስድ፣ በዚህች ሀገር ብዙ መልካም ያልሆኑ ለውጦች ነበሩ። ነገስታቱን የጠቀሙ ህዝቡን ያጎሳቆሉ ለውጦች ነበሩ፡፡ እስካሁን ድረስ ህዝቡ በልቶ ጠጥቶ፣ ረክቶ ኖሮ አያውቅም፡፡ እንግዲህ ኢህአዴግ የዛሬ 25 ዓመት ስልጣን ሲይዝ፣ ህዝቡ ውስጥ የተፈጠረው ተስፋ፣ ያ ጨለማ ዘመን አበቃ የሚል ነበር፡፡ ግን በጠበቀው መጠን የፍላጎቱን አላገኘም፡፡ የኢትዮጵያ ምሁራን፣ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት፣ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በሙሉ፣ ስለ ህዝቡ የለውጥ ፍላጎት ምንነት አበክረው ማሰብ አለባቸው። የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ምንነት መርምረው ማወቅ አለባቸው፡፡ የተሻለ ዲሞክራሲ፣ የተሻለ ኢኮኖሚ፣ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፣ እነዚህን ሁሉ ይፈልጋል፡፡ ምግብና ልብስ፣ መጠለያ፣ ለሰው ልጅ በጣም አስፈላጊ ነው፤ ግን ዲሞክራሲ ደግሞ ከሁሉም በላይ ነው። ነፃነት ከሁሉም በላይ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ከምግብ ይበልጣል፣ ዲሞክራሲ ከልብስና ከመጠለያም ይበልጣል፡፡ ዲሞክራሲ ከሁሉም የሰው ልጆች ፍላጎት የላቀው ነው። ዲሞክራሲ ሲኖር፣ ነፃነትና መብት በአግባቡ ይጠበቃል። በዚህች ሀገር ይሄ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ለተፈጠሩ ችግሮችም መልሱ ይሄ ነው፡፡
አሁን የጠቀሷቸው—–ዲሞክራሲና ነጻነት እንዴት ነው የሚመጡት?
በመነጋገር ነው ሁሉም ነገር ሊስተካከል የሚችለው። መፍትሄው በሁላችንም እጅ ነው ያለው። ለውጡን ማምጣት የሚችሉት ኢትዮጵያውያኖች ናቸው፡፡ የውጭ አካላት ሊለውጡት አይችሉም፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውን፡- ጉራጌውም፣ ኦሮሞውም፣ አማራውም፣ ትግሬውም— ሌላውም ተሰባስበው፣” ይሄ መንገድ አያዋጣንም፣ በዚሁ ከቀጠልን እንተላለቃለን” ብለው መክረው፣ ሃገሪቱ የምትፈልገውን ዲሞክራሲ ማምጣት አለባቸው፡፡ ሁሉም ችግር የሚፈታው በመነጋገር ነው፡፡ ዝም ብለን መቀጠል የለብንም፡፡
ዲሞክራሲ ማለት የህዝቡ ውስጣዊ ሠላም ሲሻሻል ማለት ነው፡፡ አሁን መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፤ ብዙ ነገር መናገር አልችልም። ነገር ግን ያለው ሁኔታ መቀጠል እንደማይችልና ለውጥ መኖር እንዳለበት እሙን ነው፡፡ ስብሰባዎች በመንግስት ተጠርተው፣ ህዝቡ በሃገሩ ጉዳይ መምክር አለበት፡፡
የኦሮሞ ፓርቲ መስራችና መሪ ነበሩ፡፡ የኦሮሞ ህዝብ መሠረታዊ ጥያቄ ምንድን ነው ይላሉ?
በዚህች ሃገር ውስጥ ኦሮሞ ትልቅ ድርሻ አለው፤ ወደ 50 ሚሊዮን ተጠግቷል፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ በራስ የመተዳደር ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ በትክክል ይስራ ነው ጥያቄው፡፡ የፌደራል ስርአቱ ሁሉም ብሄሮች በኢትዮጵያ ጥላ ስር ሆነው፣ በራሳቸው እንዲተዳደሩ፣ ግብር ራሳቸው ጥለው እንዲሰበስቡ፣ ውጪና ገቢ ራሳቸው ተቆጣጥረው እንዲተዳደሩ ነው የሚፈልገው፡፡ ማንም ከበላይ ሆኖ ይቀጣኛል ብሎ ሳያስብና ሳይሰጋ የሚኖርበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው የሚፈለገው፡፡ የራሳቸው አስተዳዳሪዎች ሙሉ ስልጣን እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ፡፡ ኢህአዴግም ከበረሃ ሲመጣ ይሄን አስቦ ይመስኛል፤ በመሃከል ነገሩ ተበላሸ እንጂ፡፡ ይሄ የተበላሸ ነገር ደግሞ ዛሬም አልረፈደም፤ መታረም ይችላል፤ መታረምም አለበት፡፡
በተቃውሞዎቹ ወቅት የመገንጠል ጥያቄ ተንጸባርቋል፤ እርስዎ በመገንጠል ጥያቄ ላይ ያለዎት አቋም ምንድ ነው?
እንደኔ አሁን የመገንጠል ጥያቄ አያስፈልግም። እኔ መገንጠል አልደግፍም፡፡ ይሄ ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ አይሆንም፡፡ ግን ፌዴሬሽን ሲባል ትክክለኛ ፌደሬሽን መሆን አለበት፡፡ ፌዴሬሽን አካላዊ ህመም የለውም፡፡ ቁንጥጫው አይሰማም – እንደመገንጠል፡፡ ህመም የለውም፡፡ መገንጠል የተሠነጠቀ ቁስል ይዞ ነው የሚመጣው፡፡ ቁስል አለው፡፡ ፌዴሬሽን የለውም፡፡ ለዚህ ነው ፌዴሬሽን ይሻላል የሚለውን ፅኑ አቋም የያዝኩት፡፡ ለምሳሌ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አለ፡፡ ኢትዮጵያ የህብረቱ አባል ነች፡፡ ሌሎች ሃገራትም አባል ናቸው። የማይዋደዱ ሃገራት እንኳ በዚህ ህብረት ስር አሉ። የኛ ፌዴሬሽንም እንደዚህ ነው መሆን ያለበት። የተባበሩት መንግስታት የተቆጣጣሪነት ሚና ነው ያለው፡፡ ሠብዓዊ መብት ሲጣስ ለምን ይላል፡፡ የፌዴራል መንግስታችንም እንዲህ ነው መሆን ያለበት፡፡ የፌዴራል ስርአቱ የአባልነት እንጂ የአንድ አገዛዝ ባህሪ ሊኖረው አይገባም፡፡
ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሄው ምን ይመስልዎታል?
እኔ ይበልጥ ዲሞክራሲያዊ ከሆነ ብዙም ችግር የሚፈጠር አይመስለኝም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ መለወጥ አለበት፡፡ መንግስት ችግሮችን እንዳመነው ሁሉ ማስተካከል አለበት፡፡ ወደ ዲሞክራሲ መግባት አለብን። የህዝብ ወኪሎች ተቀራርበው መነጋገር አለባቸው። ለውጥ ሲባል፣ ሁሉን ማጥፋት ሳይሆን ከህዝብ ተወካዮች ጋር መነጋገርና አዲስ መፍትሄ ማምጣት ማለት ነው። ኢህአዴግም የዚህ መፍትሄ አካል መሆን አለበት። በማንኛውም የሃገሪቱ ጉዳይ ላይ ኢህአዴግ ድርሻ ሊኖረው ይገባል፡፡ ባለፉት 25 አመታት የተለፋው ሁሉ ዜሮ ነው ማለት አይቻልም። ግን ብዙ የሚቀር ነገር አለ፡፡
እርስዎ እንደሚሉት፣የቅራኔ ሃይሎች ተቀራርበው በመነጋገር ችግሩን ይፈቱታል? ተስፋስ አለ ብለው ያስባሉ?
አዎ! ተስፋ አለ፡፡ ሁሉም የሚነገሩ ነገሮች ጥፋት አይደሉም፡፡ ለበጎ ተብለው የሚነገሩ ነገሮች ከሁሉም ወገኖች እየታዩ ነው፡፡ ሁሉም የሚናገረው፣ ውስጡ፣ በጎ ነገሮች ተሸክሟል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ በገንዘብ የተገዛ ሊሆን ይችላል፤ ጥፋትን የሚመኝ አለ፡፡ ጥፋትን የሚመኘውን አንቀበለውም፡፡ ወዲያ ሂድ ልንለው ይገባል፡፡ ለወገኖቿ፣ ለህዝቦቿ የተመቸች ሀገር ግን መገንባት አለብን፡፡ ስለዚህ ጨለምተኛ አንሁን፤ ተስፋዎች አሉ፡፡ ገዥውም ሆነ የሚቃወመው፣ ጫካ የገባውም ጭምር፣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ ተሰባስበን እንደገና በፅኑ መሞከር አለብን፡፡ እርግጥ ነው እንዲህ ያለው ጉዳይ በአንድ ጊዜ የሚሆን አይደለም፤ የራሱን ጊዜና ሂደት ይጠይቃል፡፡ ለምሳ እንግሊዝን ብናይ፣ እንዲህ የተጣራ ስርአት ኖሯት የምናየው፣ በብዙ የማጣራት ሂደት ውስጥ አልፋ ነው። አሜሪካም ብዙ ጣጣ ነበረባት፤ በሂደት አጣርታ ነው አሁን ያለችበት ቦታ የደረሰችው፡፡ ሁሌ እንደተዋጉና እንደተላለቁ አይሆንም፡፡ እንደ አዲስ አፍርሶ መጀመርም አይሆንም፡፡ ባለው ላይ የሞተሩ ጥርሶች እንዳይደርቁ፣ ዘይት ማጠጣት ነው የሚያስፈልገው። ዘይት መቀየር ነው የሚያስፈልገው፡፡
በሀገሪቱ ያልታረቁ የዘመናት ቅራኔዎች አሉ በሚል የሚሞግቱ፤ እርሶ በዚህ ላይ ያለዎት ሀሳብ ምንድን ነው?
ባለፉት ዘመናት ስለነበሩ ቅራኔዎች የምንነጋገር ከሆነ፣ እርግጥ ነው በሀገሪቱ የተለያየ ማንነት ይዞ፣ ለአንድ ገባር የሆነ ህዝብ ነበረ፡፡ ይሄ መታረቅ የሚችለው በእውነተኛ ዲሞክራሲ ነው፡፡ ዛሬ ስለ ዲሞክራሲ ህፃናት ሳይቀሩ ያውቃሉ፡፡ እንግዲህ አንዴ ዲሞክራሲ እናሰፍናለን ተብሎ ከአፍ ካመለጠ በኋላ፣ የሚያስፈልገው የግዴታ ማስፈን ነው። ካለፈው ዘመን አሁን የተሻሻሉ ሁኔታዎችም እኮ አሉ። ለምሳሌ ድሮ ፖሊስ ዝም ብሎ ሰው ይዞ ያስራል፤ ዛሬ የፍርድ ቤት ማዘዣ ወረቀት ማምጣት አለበት፤ እነዚህ መሻሻሎች ናቸው፡፡ ይሄን ገፍተን የበለጠ እናሻሽለው ነው የኔ ሀሳብ፡፡ አሁን ዲሞክራሲን በአፍ ብቻ እያወሩ አለመተግበር አይቻልም፡፡ አሁን ያለው የዲሞክራሲ መጠን ለብዙ ሰው አልተስማማም የሚል ነው ሀሳቤ፡፡
እርስዎ —— ለችግሮቹ መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
ለኬንያ ችግር መፍቻ የዋለው ዘዴ፣ እኛ ጋ ላይሠራ ይችላል፡፡ ለኛ ልዩ የሆነ የሚስማማንን ሃሳብ ነው ማምጣት ያለብን፡፡ እርግጥ ነው አንዳንዱ ለሁሉም የሰው ልጅ የጋራ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- የሰብአዊ መብት ጉዳይ፡፡ ነገር ግን ለኛ ብዝሃነት መፍትሄው ምንድን ነው የሚለው መታወቅ አለበት፡፡ የህዝብ ፍቃድ መፈፀም አለበት፤ የህዝብ ፍቃድ ስንል የፖለቲካ ቡድኖች ፍላጎት ማለት አይደለም፡፡ የቡድኖቹ ፍላጎት ምናልባት ጠባብ ሊሆን ይችላል፡፡ የህዝብ ግን ሠፊ ነው፤ የጋራ ነገርም አለው፡፡
ዲሞክራሲ በሚፈለገው መጠን ላለመምጣቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከኢህአዴግ ያልተናነሰ ድርሻ አላቸው ይባላል፡፡ እርስዎ በዚህ ይስማማሉ?
እግርጥ ነው፤ የሚጠበቅባቸውን ያህል አልሄዱም፡፡
ለምን አልሄዱም?
ገንዘብ የላቸውማ፡፡ በሌላ ሃገር እኮ ለተቃዋሚዎች መንቀሳቀሻ ገንዘብ የሚሰጠው መንግስት ነው። እዚህ ሃገር ተቃዋሚዎች የደቀቁት ለሃገር የሚበጅ ሃሳብ አጥተው አይደለም፤ ገንዘብ ስለሌላቸው ነው። እኔ የማውቃቸው፣ ጎበዝ ሆነው መልካም አስተሳሰብ ያላቸው፣ ከሠለጠኑ ሃገሮች መሪዎች የማያንሡ ሰዎች አሉ፤ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ባዶ እጃቸውን ናቸው፡፡ ተንቀሳቅሰው አላማቸውን ለህዝብ ማድረስ አይችሉም። “መንግስት አደቀቃቸው” የሚባለው እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ምክንያቱ እሱ ብቻ አይደለም፤ ባዶ እጃቸውን ናቸው፤ ገንዘብ የላቸውም፡፡ ስብሰባ አድርገው ሰው መጥራት የሚችሉበት የገንዘብ አቅም የላቸውም። እርግጥ ነው አባላት ያዋጣሉ፤ ግን እሱ አይበቃም። ከአዲስ አበባ ውጪ ደርሶ ለመመለስ በትንሹ 500 ብር ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ከየት ይመጣል?
ተቃዋሚዎች ገንዘቡን ከየትና እንዴት ነው ማግኘት ያለባቸው?
እንዴ! መንግስት ፈንድ ማድረግ አለበት፡፡ እርግጥ ነው አባላትም ማዋጣት አለባቸው፤ ግን በቂ አይሆንም። መንግስት ገንዘብ ሊሰጣቸው ይገባል፤ ገንዘቡ ደግሞ የህዝብ ነው፡፡፡
የኦፌኮ በርካታ አመራሮች ታስረው ፓርቲው እየተዳከመ መምጣቱ ተዘግቧል፡፡ ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብዎ?
በጣም አዝኛለሁ፡፡ በቀለ ገርባን እኔ ነኝ ወደ ፓርቲያችን ያመጣሁት፡፡ እሱ በጣም አዋቂና አሳቢ ነው፡፡ “አቶ ቡልቻ፤ በኛ ሀገር ለውጥ ማምጣት ይቻላል ወይ?” ብሎ ጠይቆኝ፣ ብዙ የማሳመን ጥረት አድርጌያለሁ። እሱ ብዙ መፅሐፍት ያነበበ፣ የፃፈ፣ የተመራመረ ሰው ነው፡፡ ይቻላል ብዬው ነበር፡፡ በቀለ ገርባ በጣም አስተዋይ ሰው ነው፡፡  እነዚህ የታሰሩ ሰዎች በደንብ አውቃቸዋለሁ፤ ለሀገራቸው ቀና ሀሳብ ያላቸው ናቸው። ዶ/ር መረራንም አቶ በቀለንም በደንብ አውቃቸዋለሁ ኢትዮጵያን ለማሳደግ ነው እንጂ የሚፈልጉት ለማጥፋት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ተበጣብጣ—–ኦሮሞ ለብቻው፣ አማራ ለብቻው፣ ጉራጌ ለብቻው እንዲሆን አይደለም የሚፈልጉት፡፡ እኔ ይሄንን ስለ ሀቅ እመሰክርላቸዋለሁ፡፡ ምናልባት እነዚህ ሰዎች የወጡበትን ማህበረሰብ የበለጠ ለማሳደግ ሀሳብ ይኖራቸው ይሆናል እንጂ ለሰው ልጅ ሁሉ አሳቢዎች ናቸው፡፡ በቀለ ገርባ መንፈሰ ጠንካራ ነው። በፍልስፍናው በእምነት መርሆቹ ጠንካራ ነው። በደንብ እውቀት ያለው፣አዕምሮው ብሩህ ሰው ነው። ዶ/ር መረራ ደግሞ ምሁር ነው፡፡ ከሁሉም የበለጠ፣ ሰፋ ያለ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡ “የኦሮሞ ህዝብ በቁጥሩ ልክ መብቱ ይጠበቅ እንጂ፣ ከሌላው ህዝብ ይብለጥ አይደለም” – የእነዚህ ሰዎች ትግል፡፡
የሀገሪቱ ችግሮች በውይይት ይፈቱ የሚሉ ሀሳቦች ይቀርባሉ፡፡ ግን ማንም ተነሳሽነቱን ወስዶ ሲፈጽመው አይታይም፡፡ አስታራቂ የሀገር ሽማግሌዎች ለምን ጠፉ?
ያለፉት መንግስታት እንዲህ አይነት ሽማግሌዎች እንዳይኖሩ አድርገዋል፡፡ “ተው እንጂ፤ ይሄ ለሀገር አይበጅም” የሚሉ ሰዎች የጠፉት ለዚህ ነው፡፡ እዚህ ሀገር ጎበዝ ወታደር አለ፣ ጎበዝ መምህር አለ፣ ጎበዝ የህግ ባለሙያዎች አሉ፤ ግን የሃገር ሽማግሌዎች የሉንም። ስለዚህ መንግስት ተነሳሽነቱን ወስዶ፣ ከየወገኑ አዋቂ ሰዎችን በፍቃዳቸው ጠርቶ፣ “አንድ የሚሰራ ሲስተም እንፍጠር፤እሡን እስክንፈጥር መለያየት አይገባም” በሚል መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ሁሉንም ልዩነቶች በልበ ሰፊነት የሚመለከትና የሚያስተናግድ መኖር አለበት። መፍትሄው ሁሉ መምጣት ያለበት ከኛ ነው፤ ሌላ እንዲያመጣልን መጠበቅ የለብንም፡፡ ለራሳችን ተቻችለን፣ ለጋራ ቤታችን መፍትሄዎች መሆን አለብን፡፡
ሰው ማሰር መፍትሄ አይሆንም፤ ችግሩን የበለጠ ያወሳስበዋል እንጂ፡፡ በሃሳብ መታሰር ደግሞ ተገቢ አይደለም፡፡ ሃሳቦች ነፃ መሆን አለባቸው፡፡ አሁን ሃይለኛ ተናጋሪ ፖለቲከኞች አሉ፡፡ መኖራቸውን ማመን ያስፈልጋል፡፡
ይባስ ብሎ ደግሞ ህዝብ ሁሉ አፍ አውጥቷል፡፡ “ይህን አልወድም፣ አልፈልግም” ማለት ችሏል፡፡ እንዲህ ያለውን ሁሉ እያሰሩ መዝለቅ አይቻልም። መፍትሄው ከህዝብ ጋር መመካከር ነው። ወደ አደላው ሃሳብ ነው መሄድ ያለብን። ለምሳሌ ኦሮሞዎች በቁጥር ብዙ ናቸው፤ ግን “በቁጥራችን ብቻ እንገዛለን” ብለው ማሰብ የለባቸውም፤ አያዋጣም፡፡ በመጀመሪያ በፌዴሬሽን ደረጃ ራሳቸውን ማስተዳደር፣ ከዚያም በሃሳብ ካሸነፉ ብቻ ነው መምራት ያለባቸው፡፡ በዚህች ሃገር ገዥ ሊሆን የሚገባው – አስተሳሰብ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment