Thursday, January 19, 2017

የሕወሃት የመጨረሻው ክሽፈት (አያሌው መንበር)

 


ሕወሃት ይዞት የተነሳው የሴራ ፖለቲካ በአብዛኛው ዘንድ ስለታወቀበት ውጥኑን ለማስቀጠል በተለይ ካለፈው ዓመት መጨረሻ ጅምሮ ብዙ ነገሮችን ተግብሯል።
ኢህአዴግን እንጅ ሀገርን ከማይታደግ “ተሀድሶ” እስከ አዲስ ከቢኒ ማቋቋማ፣ ጦሩን በህዝብ ላይ ከማዝመት እስከ አስቸኴይ ጊዜ አዋጅ…ብዙ የከሸፉ ሙከራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
እነዚህ ሁሉ ሙከራዎች የክሽፈታቸው ምክንያት ከጅምራቸው ሴረኛውን ህወሀትን እንጅ ኢትዮጵያን ለመታደግ ከልብ የታደቁ ባለመሆናቸው ነው።በተለይም ነሀሴ ወር ላይ በነበረው የኢህአዴግ ምክር ቤት እና ማዕከላዊ ኮሚቴ (በወቅቱ ሰፊ ትንታኔ ሰጥቸበት ነበር) ግምገማና ያስቀመጠው የተሳሳተ የመፍትሄ አቅጣጫ ህወሃትን ይበልጥ ወደ ቁልቁለት መንገድ እንዲገባ ያደረገ ነበር።ህዝቡ በህይወት የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ እያነሳ ኢህአዴግ ግን እንዲህ ሲል አስቀመጠ፦ “የስርዓቱ ፈተና ስልጣንን በመጠቀም ሀብት ማግበስበስ ነው፤አሁን ለገባንበት ቀውስ መፍትሄውም ሙስናን መዋጋት ነው የሚል።
ሙስና በኢትዮጵያ ከህወሃት የፖለቲካ ርዕዮት ጋር አብሮ የበቀለላ ተላምዶ የኖረ ምናልባትም ስርዓቱ ከወደቀ በኋላም በግለሰቦች ጋር አብሮ የሚኖር ነው።ስለሆነም ባለፉት ሁለት ዓመታት የህዝቡ ጥያቄ ተላምዶት የኖረውን ሙስናን መዋጋት ሳይሆን #የስርዓት_ለውጥ ጥያቄ ነበር።ይህ ለህወሃትም ሆነ ለዱላዎቹ (ብአዴን፣ኦህዴድና ደኢህዴን) ግልፅና የአደባባይ ሚስጥር ነው።ሆኖም ሴረኛው ህወሃት ይህንን የሚያውቀውን ጥያቄ መመለስ ስላልፈለገ ሌሎች ድርጅቶችን ሌላ አጀንዳ በመስጠት እድሜውን ማራዘም ፈለገ።እናም የሀገሪቱ ችግር “ሙስና ነው” በሚል በሮሆቦት በተሞሉ ጥቂት የሀገር ቁማርተኞች መላውን ህዝብና አባሉን እንዲያምን ፈለገ። የህወሃት የመጨረሻ ውድቀቱ ይህ ነው።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያውጅም ህዝቡ እየገደለ መሞትን እንደመረጠ የጎንደርና ጎጃም አማራ ምስክር ነው።ውስጣቸው እያረረም ቢሆን በሰላም ይኖሩ የነበሩ የወልቃይትም ይሁን የጢስ አባይ፣የቡሬም ይሁን የቋራ አርሶ አደሮች ቤትና ንብረታቸውን ጥለው በረሃ የገቡት እኮ ህወሃት በሞከራቸው የዕድሜ ማራዘሚያ የመፍትሄ ሀሳቦች ተስፋ በመቁረጣቸው እንጅ ሀገራቸውን ክደው አይደለም።”እኔ የምታገለው ለአማራ ህዝብ ነው፤ከቻልኩም ኢትዮጵያን ነፃ አዎጣለው፤ የህወሃት ሰላዮች የሌሉበትን ወልቃይትን እሻለው…”እያለ በረሃ የገባው ጎቤ መልኬ እኮ ህወሃት “የውልቃይት ጥያቄ የሚፈታው ሙሰኛ አመራሮች ሲጠየቁ ነው” የሚል አራምባና ቆቦ መልስ በመስጠቱ ጥያቄውን በማሳደግ #ከዚህ_በኋላ_የወልቃይት_የአማራ_ማንነት ጥያቄ የሚመለሰው #የስርዓት_ለውጥ ሲኖር ብቻ ነው ብሎ በማመኑ ነው።አሁን የዚህ ሀሳብ ሚሊዮን ተከታዮች አሉት።
ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ከዚህ ስርዓት ጋር ዳግም ላይገናኝ ተለያይቷል።
ህወሃት በዚህ ሰዓት እንኳን እነአየለ ጨሚሶና የመሳሰሉት ጋር በተለይ መወያየት ቀርቶ #ፕሮፌሰር_ብርሃኑ_ነጋን ጠቅላይ ሚኒስትር ቢያደርግ እንኳን የህወሃትን ስርዓት ተቀብሎ የሚቀጥል የኢትዮጵያ ህዝብ ይኖራል ማለት ዘበት ነው።በተለይም እንደ አማራ ይህ እጅግ ከባድና የማይሆን ነው።በህወሃት በኩልም የማይሞከር።
ባለፈው በተዘጋጀው የፖለቲካ ሰዎችና ባለድርሻ አካላት (እነ ዶ/ር መራራ፣ኢንጅነር ይልቃል፣ልደቱ አያሌው እና ሌሎችም) የተገኙበት ውይይት ላይ የቀረበው የመፍትሄ ሀሳብ ውድቅ ተደግርጎ አሁን ደግሞ ሌላ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ለማድረግ እቅድ መያዙን እየሰማን ነው።በዚህ ላይ እነ አየለ ጫሚሶን የመሰሉ ሰዎች አስገራሚ አስተያየትን እየሰጡ ፈገግ ቢያደርጉንም ከዚህ በኋላ አትዮጵያ ላይ በዚህ መንገድ ኢትዮጵያ ትቀጥላለች ብሎ የሚያምን ነብይ ብቻ ሳይሆን ጠንቋይ እንኳን አይኖርም።ካለም እርሱ ሞኝ ነው።
ዛሬ ዜጎች ከቤት አስወጥቶ በአደባባይ እና ከቤተሰብ ፊት በጥይት የሚረሽን ስርዓት ባለበት፣ለወትሮው በድምቀቱ የምናውቀው የመስቀል፣ገና እና ጥምቀት በዓል በአብዛኛው አማራ ዘንድ ሳይከበር በሀዘን እያለፈ፣ለዘመናት የጥይት ድምፅ የማያውቁት እነ ባህር ዳር እና ጎንደር ዛሬ የቦንብ ፍንዳት እያስተናገዱ፣ሰው ከመንገድ እየታፈሰ ራሱን ማዕከላዊ እያገኘ፣ገበሬው ወታደር ሳያስፈቅድ ከቤቱ እንደሚመጣ አውቆ በተጠንቀቅ እየጠበቀ ፣የእምነት ተቋማት የዘወትር ፀሎት ሀገሬን ጠብቃት ሳይሆን እባክህ ይህንን ስርዓት አስወግድልን ወደሚል ተለውጦ፣……ብቻ ሁሉም ነገር የተገላቢጦሽ በሆነበት በዚህ ዘመን ህወሃት አሁንም እድሜየን አራዝማለው ብሎ ብቅ ቢል መልሱ ፍም ላይ መተኛት ነው ይሆናል።ህዝቡ ስሜቱ ግሏል፤ያገኘውን ሁሉ ያቃጥላል፤…..ይህ ነው የዘመኑ ጉዳይ።
እናም ህወሃት ሰሞኑን ያቀደው “የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት” ነገሩን ከማወሳሰብ ያለፈ አንዳች ፋይዳ አይኖረውም።ትናንትም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ የማታሳስበው ህወሃት ህዝባችን ላይ ሌላ የሞት ድግስ ቢደግስም ቅሉ “#ሞት_ቢደገስልንም_አንፈራም” ያሉት የአማራ ወጣቶች ግን ዛሬም በተጠንቀቅ ላይ ናቸው።የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄና የእነ ኮሎኔል ደመቀ እስራት በተለይ የሰሜን ኢትዮጵያን የፖለቲካ ትኩሳት አግሎታል፤ የህወሃትና የአፈንጋጭ ብአዴን አመራሮች የጎሪጥ እይታ ከኦሮሞ ምሁራን የውስጥ ለውስጥ ትግል ጋር ተዳምሮ የሀገር ውስጥ አለመረጋጋቱንና የፖለቲካ ልዩነቱን ቋፍ ላይ አድርሶታል።የህወሃትና የሀገር ውስጥ ፓርቲዎች የለበጣ ውይይት ሌሎች ጠንካራ ግለሰቦችንና ፓርቲዎችን የበለጠ አስቆጥቶ ህዝቡን ያርቀው ካልሆነ በቀር መልካም አጋጣሚው አይታየኝም።
ዛሬም በህዝቡ ውስጥ ቅቡልነት ያላቸውንና በእስር ቤት የሚገኙትን የእነ እንዷለም አራጌን፣በቀለ ገርባን፣ዶ/ር መራራ ጉዲናን…. ወዘተ ንግግር ከዩቲብ እየፈለገ እየደጋገመ የሚታዳምጥ ትውልድ ባለበት ሀገር ውስጥ የእነ አየለ ጫሚሶ፣ በየነ ጴጥሮስ፣ አብርሃ ደስታ፣…ውይይት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው የሚሆነው።
አሁን ላይ ወደድንም ጠላንም አንድ እውነት አለ።ፖለቲካውም ይሁን የህዝብ ብሶቱ ያገረሸውና ላይመለስ ጫፍ የረገጠው አማራው ውስጥ ነው።ይህ የማይካድ ሀቅ ነው።እናም የመጀመሪያ መፍትሄ የሚሻው ይህ አካባቢ ነው ማለት ነው።ይህ አካባቢ ደግሞ በዚህ ወቅት በሀገር ውስጥ አማራጭ ፓርቲም ይሁን የእኔ የሚለው ተወካይ የለውም።በተወሰነ የሚያምናቸው መኢአዶችም አብዛኛዎቹ ወሳኝ አመራሮች ቃሊቲ ማዕከላዊና ቂሊንጦ ናቸው።ስለሆነም አረናን ወይም ቅንጅትን ሰብስቦ ለአማራ መፍትሄ ይመጣል ማለት የህወሃት ሌላ ክሽፈት ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ መፍትሄ አይደለም።
በአሁኑ ወቅት የቤተ አማራ የፖለቲካ ፍልስፍና ከወጣቱ ብሶት ጋር ተዳምሮ ድሮውን አማራውን ያገለለውን የውጭ እና የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ሚዛኑን ዥዋዥዌ እያጫወተው ይገኛል።እናም በአማራ አካባቢ የተነሳው የህዝብ ተቃውሞ ከዚህ በኋላ የሚኖረው ዘላቂ መፍትሄ በአማራ ፓርቲዎችና በአማራ ህዝብ ፈቃደኝነት ብቻ የተመሰረተ ይሆናል። አሁን ህወሀት የሚሄድበት መንገድ ግን የፖለቲካ ልዩነቱን የበለጠ ያጦዘውና አሁን የምናየውና አልፎ አልፎ የሚያገረሸውን የህዝብ ብሶት ወደ ማዕበል ይቀይረው ካልሆነ በስተቀር ዘላቂ መፍትሄም አያመጣም።

No comments:

Post a Comment