Friday, January 13, 2017

አቶ ሃብታሙ አያሌው በሰላም ለሕክምና አሜሪካ ገብቷል


(ዘ-ሐበሻ) አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ለጋዜጠኞች፣ ለብሎገሮችና ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሲኦል እንደሆነች ነው።ብዙዎች ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ሲሉ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ነው። የሕግ ስርዓቱ የበሰብሰ ነው። በአሥር ሺሆች ከሚቆጠሩ ከራሳችው ትቅም ይልቅ የአገርን ጥቅም ካስቀደሙ ታጋዮች መካከል አቶ ሃብታሙ አያሌው አንዱ ነው።
አቶ ሃብታሙ በሕወሃት ሕግ ወጥ በሆነ መንገድ የታገደው፣ አንጋፋ የነበረው የአንድነት ለዲሞክራሲ ለፍትህ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ የነበረ ሲሆን ፣ ከጥቂት አመታት በፊት በመላው ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሰልፎች በማድረግ ህዝብን ማንቀሳቀስ የቻለው የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴ ግብረ ኃይል ሰብሳቢም ነበር።በሚሊዮኖች ድምጽ እንቅስቃሴ ወቅትም ነበር ሕወሃት “ሽብርተኛ ነህ” በሚል ሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም አቶ ሃብታሙን ወደ ማእከላዊ የቶርቸር ቻምበር አፍኖ የወሰደው።
በማእከላዊ በደረሰበት ኢሰባአዊ ግፍና ቶርቸር ለከፍተኛ ሕመም ተዳረገ። ከሰላሳ ጊዜ በላይ ፍርድ ምልልስ በኋላ፣ ፍርድ ቤቱ ፣ ወደ ዉጭ እንዳይወጣ እገዳ አድርጎ፣ ከወህኒ ዉጭ ሆኖ እንዲከራከር ወሰነ። ሆኖም እስር ቤት እያለ በሕወሃት መርማሪ ነን ባዮች ወንበዴዎች በደረሰበት ትልቅ ጉዳት ለከፍተኛ ሕመም የተዳረገው አቶ ሃብታሙ፣ ራሱን እስኪሰት ድረስ ታሞ ለሆስፒታል ተዳረገ። ሐኪሞች “ከአቅማችን በላይ ነው” በሚል ወደ ዉጭ ሄዶ እንዲታከም ገለጹ። ፍርድ ቤቱ እገዳዉን እንዲያነሳ ጥያቄ ቀረበለት። ሆኖም ፍርድ ቤቱ እገዳዉን አላነሳም አለ። አቶ ሃብታሙ ሕመሙን ተሸክሞ፣ በእግዚአብሄር እርዳታ፣ አገር ዉስጥ ባሉ ሐኪሞች ክትትልና በማስታገሻዎች እስከአሁን ቆይቶ፣ በመጨረሻ ፍርድ ቤቱ የቀረበበትን ክስ ዉድቅ በማድረጉ ለሕክምና ዛሬ ጃኑዋሪ 12 ቀን ወደ አሜሪካ ሊመጣ ችሏል።
አቶ ሃብታሙ ወደ ዉጭ ሄዶ እንዳይታከም ተደረጎ በነበረበት ወቅት “እነአቦይ ስብሃት ከዘጠና በላይአመታቸው የክብር ዶክትሬት ሲሰጣቸው እኔ በዚህ ዕድሜዬ የሞት ደብዳቤ ተጽፎልኛል። በእኔ ላይየሚፈርደው ግን እግዚአብሔር ነው። ዝም ብዬ የእግዚአብሔርን ማዳን እጠብቃለሁ” ነበር ያለው። ይኸው እግዚአብሄር ጠበቆ አላፈረም። በርሱ ቸርነት ይኸው ለዚህ በቅቷል።
ለአቶ ሃብታሙ የአሜሪካ ቆይታዉ መልካም እንዲሆን እየተመኘን፣ ፈጣሪ በቶሎ እንዲፈወሰው እንጸልያለን። ኢትዮጵያዊያንም ከዚህ በፊት ከአቶ ሃብታሙ ጎን እንደነበርን፣ ከዚህም በኋላ ከጎኑ መሆናችንን እንድንቀጥልም ጥሪ እናቀርባለን።

No comments:

Post a Comment