Monday, January 30, 2017

‹‹…ነገሩ አልሆን ብሎ፣ ሁኔታው ሲጠጥር ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር…›› የሚሉ በሳሎች ያስፈልጋሉ፡፡


   

Addis Admass ርዕሰ አንቀፅ
ልማድ የልጅነት አባዜ አለው፤ አድጎ ተመንድጎም ራሳችን ላይ ፎቅ ሊሰራብን ይችላል። መላቀቅ ያለብን ብዙ ልማድ አለ! ይሄ ከባህላችን፣ ከማህበራዊ ኑሯችን፣ ከፖለቲካችንና ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው፡፡ ስነ ልቦናዊ ግንኙነቱም ከዚሁ የሚመነጭ ነው፡፡ ይሄን ወደ አገር ጉዳይ መንዝሮ ማየት ጉዳዩን በሚገባ መሰረት ያበጅለታል፡፡ እየተዘወተሩና እየተለመዱ የሚመጡ የአገራችን ጉዳዮች ውለው አድረው፣ ጎልበተው መታየታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ትናንሽ ዕቅዶች ወደ ትላልቅ ፈቅዶች የሚያድጉት ትናንሾቹ በአግባቡ ሲፈፀሙ ነው፡፡ ለዚያ የጊዜ ስሌት፣ የዝርዝር አያያዝና የቁጥጥርና ግምገማ ሥርዓት በአግባቡ ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ይህን ፈፃሚውና አስፈፃሚው አካል፣ የራሱ አቅልና ብስለት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የራስ አመለካከት ከአገር አመለካከት ጋር ይራራቅና ጣጣ የሚያመጣው፡፡ እያንዳንዱን ሰው ቀርፆ፣ ሰው ለማድረግ አዳጋች ነው፡፡ ይህን የሚሠሩ ተቋማት እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ ለዚህ ብሩህ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የሲቪል ማህበራት ቁጥርም፣ አቅምም በጣም ውስን ነው፡፡ ይህ የሆነው ፋይዳቸውን ከልቡ ያመነበት ወገን ባለመኖሩ ነው፡፡ ጊዜም ባይኖር ጊዜ ወስዶ፣ ለጥያቄው መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አማካዩ መንገድ ይሄው ነው፡፡ ከገዢው ፓርቲና ከተቃዋሚው ድርድር ባሻገር የህዝብን አስተሳሰብ የሚያሰባስብ፣ ወደ ተግባር እንዲያመራም የሚያግዝ ኃይል ያስፈልጋል፡፡
‹‹ከእናንተ ሌላ እኛም አለንኮ›› የሚል የህብረተሰብን ክፍል ማን ይታደገው ማለት አለብን፡፡ በጥቁርና በነጭ መካከል ያለውን ግራጫ መስመር፣ ስፋቱን ስለማንገነዘብ ጠቀሜታውም የዚያኑ ያህል ይሳሳብናል፡፡ ‹‹መካር የሌለው ንጉሥ፣ ለአንድ ዓመት አይነግሥ›› የሚለው አባባል፣ አበው ያለ ነገር አላሉትም፡፡ ለአመራሩ፣ ለገዢው ክፍል፣አማካሪ ያስፈልገዋል፡፡ በእርግጥ አማካሪ ሲባል በዕውቀት የረቀቀ፤ በልምድ የበለፀገና  ጊዜ ያስተማረው ሊሆን ይገባል! መንግሥት ሲቸኩል የሚያለዝበውም፣ ሲጠጥር የሚያልመው፤ ግትር ሲል የሚያላላው፣ አይዞህ ባይም፣ ገሳጭም፣ ነው የሚያሻው፡፡ የጥንት የጠዋቱ ገጣሚ ገሞራው፤ እንዳለው፡- ‹‹…ነገሩ አልሆን ብሎ፣ ሁኔታው ሲጠጥር ጠጣሩ እንዲላላ፣ የላላውን ወጥር…›› የሚሉ በሳሎች ያስፈልጋሉ፡፡ በመደራደር ብዙ መንገድ መሄድ ይቻላል፡፡
ነገር ግን አንድ ዕውነት መረሳት የለበትም፡፡ ማናቸውም ወገን ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ገና ሶስተኛም ወገን ተጨምሮ አይበቃም ብሎ ማሰብ ብልህነት ነው። ጉዳዩን መሠረታዊ የሚያደርገው የሀገራችን ችግር ስፋት ነው፡፡ የፍትሕ መጓደል፣ የዲሞክራሲ አለመብሰል፣ የሀብት አለመደላደል፣ የተቋማት ሥርዓት አለመሻሻል፣ መልካም አስተዳደር አለመታደል፣ ያልተመለሱት ጥያቄዎች መልስ አጥተው መንሳፈፍ፣ ወዘተ ምኑ ቅጡ! ለዚህ ነው አገር ሙሉ ድርጅት ቢፈጠር እንኳ የአገር ቋት አይሞላም የምንለው!
እነዚህ ሁሉ በቅጡ ቢሰባሰቡና ኢኮኖሚውን ካቀረቀረበት ቢያቀኑት ድንገት ፎቀቅ እንል እንደሁ እንጂ ነገረ-ሥራችን እንኳ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነብን መቸገራችን የዕለት የሠርክ ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ ተራው ዜጋ ‹‹የምበላው ሳጣ፣ ልጄ ጥርስ አወጣ›› ቢል አይፈረድበትም! ኑሮው ከሥረ-መሠረቱ እናሻሽልለት! በዓል በመጣ ቁጥር የሚሰቀቀው አያሌ ነው! የእኛን መጥገብ ብቻ አንይ!! ይህንን ተደራዳሪዎቹ ወገኖች፣ እነሆ ወቅቱ መጥቷልና በምን መቀነቻ አጥብቀን እንያዘው ብለው ማሰብ ይገባቸዋል፡፡ ፀፀታችንን ሳይሆን ነገርአችንን እናስብ! የመሪዎችን ጉባኤ ስናስብም የአገራችንን መረጋጋት እንፈይድ!!

No comments:

Post a Comment