ትራምፕ ባለፈው ማክሰኞ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሁለት ግዛቶች በመራጭነት የተመዘገቡ አሉ፣ ህጋዊ ያልሆኑ መራጮች ተመዝግበዋል፣ በህይወት የሌሉ ሰዎች ድምጽ ለመስጠት ተመዝግበዋል የሚሉትን ጨምሮ ከመራጮች ጋር በተያያዘ ተፈጽመዋል የተባሉ መጭበርበሮችን እንዲጣራ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። በምርመራው የተገኘውን ውጤት መሰረት በማድረግም፣ የአገሪቱን የምርጫ ድምጽ አሰጣጥ ስርዓት የምናስተካክል ይሆናል ብለዋል ትራምፕ፡፡
ትራምፕ ተፈጽሟል የተባለውን መጭበርበር አጣራለሁ ይበሉ እንጂ፣ የመንግስት ባለስልጣናትና የምርጫ ሃላፊዎች በምርጫው ሂደት መጭበርበር መፈጸሙን የሚያመለክቱ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃዎች አለመቅረባቸውን ሲናገሩ መቆየታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህን መግለጫ ያወጡት ባለፈው ማክሰኞ በተደረገው የዋይት ሃውስ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቃል አቀባዩ ሻን ስፓይሰር፤” በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህገወጥ ስደተኞች በምርጫው ድምጻቸውን ሰጥተዋል” ብለው መናገራቸውን ተከትሎ እንደሆነ ዘገባው ገልጧል፡፡
ቢቢሲ በበኩሉ፤ ትራምፕ የምርጫው ሰሞን ጀምሮ መጭበርበር መፈጸሙን በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ሲገልጹና “በምርጫው አምስት ሚሊዮን ያህል ህገ-ወጥ መራጮች ለሄላሪ ድምጻቸውን ሰጥተዋል” የሚል ክስ ሲያቀርቡ እንደነበር አስታውሶ፣ ይህን ክሳቸውን የሚደግፍ ምንም አይነት ማረጋገጫ አለማቅረባቸውን ዘግቧል፡፡
No comments:
Post a Comment