Monday, January 30, 2017

ተቃዋሚዎች በድርድር ቅድመ ሁኔታዎቻቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ይጠይቃሉ


   

አዲስ አድማስ
ተቃዋሚዎች ከኢህአዴግ ጋር ቅድሚያ ሰጥተው ሊደራደሩባቸው የሚሿቸውን አጀንዳዎች ለአዲስ አድማስ የገለፁ ሲሆን፤ ሁሉም ፓርቲዎች የጋራ አቋም ላይ ለመድረስ ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
መኢአድና ሰማያዊ ፓርቲ፤ ከኢህአዴግ ጋር ወደ ሌላ ውይይት ከመግባታቸው በፊት የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ እንደሚጠይቁ ገልጸው፤ ማንኛውንም የህዝብ ጥቅም በድርድሩ አሳልፈው እንደማይሰጡ ተናግረዋል፡፡
ኢዴፓ በበኩሉ፤ ከምንም አስቀድሞ፣ ላለፉት 25 ዓመታት ኢህአዴግ በተቃዋሚዎች ላይ ሲፈፅም የነበረውን የመብት ጥሰት አምኖ እንዲቀበል እደራደራለሁ፤ ብሏል፡፡
የመኢአድ ዋና ፀሐፊ አቶ አዳነ ጥላሁን፤ በተጀመረው ድርድርና ውይይት ከተቃዋሚዎች ባሻገር በሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ቡድኖችና ግለሰቦችም መሳተፍ አለባቸው፤ የሚል አቋም እንዳለው ጠቁመው፤ “የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና በፖለቲካ ሰበብ የተመሰረተ ክስ እንዲቋረጥ” የሚሉ ጥያቄዎችን ለድርድር እናቀርባለን፤ ብለዋል፡፡
በተጨማሪም፣ አሁን በስራ ላይ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳና የፀረ ሽብር አዋጁ ለፓርቲዎች እንቅስቃሴ እንቅፋት በመሆኑ እንዲፈተሽ ወይም እንዲሰረዝ የሚል አቋም ይዘው ወደ ድርድሩ እንደሚገቡ ዋና ጸሐፊው ጠቁመዋል።
መኢአድ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው ግጭት እንዲበርድና የፖለቲካ ድርድር እንዲካሄድ ተቋማት ጣልቃ ገብተው እንዲሸመግሉ፤ ለሁሉም ዋና ዋና የእምነት ተቋማት ማመልከቻ አስገብቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አዳነ፤ በጎ ምላሽ የሰጠችው ግን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ነበረች፤ ብለዋል፡፡
“ይህን የመሳሰሉ ጥረቶች ስናደርግ የቆየን በመሆኑ፣ ወደ ድርድሩ ልንገባ ችለናል፤” ያሉት አቶ አዳነ፤ “በአንዳንድ የማህበረሰብ ሚዲያዎች፣ መኢአድ የህዝብን ጥቅም አሳልፎ እንደሸጠ መቆጠሩ አግባብ አይደለም፤” ሲል ወቅሰዋል፡፡
ኢዴፓ በበኩሉ፤ ወደ ድርድር ከመገባቱ በፊት፣ ባለፉት 25 ዓመታት በተቃዋሚዎች ላይ ከህገ መንግስቱ ውጪ ለተፈፀመባቸው በደል መንግስት ተጠያቂ መሆኑንና ስህተት መስራቱን አምኖ መቀበል አለበት፤ የሚል አቋም መያዙን፣ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ተሾመ አስታውቀዋል፡፡“ብዙዎቹ ሲጣሱ የነበሩ መብቶች፣ በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩ ናቸው” የሚሉት አቶ ወንድወሰን፤ “መንግስት ህገ – መንግስቱን፣ በመጣስ ፓርቲዎችን ሲበድል መቆየቱን መቀበል አለበት፤” ብለዋል፡፡ “ህዝብ ሲያነሳቸው የነበሩ ሁሉም ጥያቄዎች መመመለስ አለባቸው” የሚል አቋም ይዞ ወደ ድርድሩ እንደሚገባ የገለፁት ኃላፊው፤ እነዚህንም ለማሳካት በፅናት እንደሚደራደር አመልክተዋል፡፡
የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር፤ (በሊቀመንበርነታቸው ጉዳይ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ይጠበቃል) አቶ የሸዋስ አሰፋ፣ በአርቲስት ዘለቀ ገሠሠ የሚመራ ቡድንን ጨምሮ ሌሎች ቡድኖች በተደጋጋሚ ለድርድሩ እንዲቀርቡ እያነጋገሯቸው እንደነበርና ጥሪውንም ከኢህአዴግ ሳይሆን ከነዚህ ወገኖች ይጠብቁ እንደነበር አብራርተው፣ አሁን በኢህአዴግ መጠራቱ ያልጠበቁት መሆኑን ይገልፃሉ።
ፓርቲያቸው ከዚህ ድርድር የሚጠብቀው ውጤት ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የሚደረግ ሽግግር መሆኑን የጠቆሙት አቶ የሸዋስ፤ “ዋናው አላማችን ሃገርና ህዝብን ማዳን፣ የህዝብን ጥያቄ ማስመለስና ለህዝብ መብቶች መከራከር ነው፤” ብለዋል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹በድርድሩ ተሳታፊ መሆን የነበረባቸው በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታሠሩ ሰዎች በቅድሚያ እንዲለቀቁ›› የሚል አቋም ይዞ ወደ ድርድሩ እንደሚገባ አቶ የሸዋስ አስታውቀዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም እንዲነሳ ጥያቄ እንደሚያቀርብ አቶ የሸዋስ ጠቁመዋል፡፡
ፓርቲዎች፣ “ማን ድርድሩን ይምራ፤ እነማን ይታዘቡት፤ ሚዲያዎች እንዴት ይዘግቡት፤›› በሚሉ ጉዳዮችና በድርድሩ እንዲወያዩባቸው የሚፈልጓቸውን ርዕሠ ጉዳዮች በዝርዝር በማዘጋጀት እስከ ጥር 25 ለፓርላማ ጽ/ቤት እንደሚያስገቡ ይጠበቃል፡፡

No comments:

Post a Comment