Monday, January 30, 2017

በማህበራዊ ድረገጾች ትኩረትን የሳበ መነጋገሪያ ጉዳይ የጥንዶቹ ሰርግ


 .
ፍቅር እንጂ ቤሳቢስቲን የሌላቸው ኬንያውያን ጥንዶች…
ከተስፋ በቀር ይህ ነው የሚሉት ጥሪት ያልቋጠሩ ፍቅረኛሞች ዊልሰን እና አን ሙቱራ!…
ፍራፍሬ በማዞር አስር አምስት እየለቀመ ኑሮውን የሚገፋው የ27 አመቱ ዊልሰን እና የ24 አመቷ አን፣ ከተዋወቁና የፍቅርን አክርማ መቅጨት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡
ከሶስት አመታት በላይ በፍቅረኝነት የዘለቁት ጥንዶቹ፣ ትዳር መስርተው በአንድ ጎጆ ለመኖር ካሰቡ ሶስት አመታት አልፏቸዋል፡፡
ችግሩ ግን፣ የመጋባት ፍላጎት እንጂ የመጋቢያ ገንዘብ አልነበራቸውም፡፡ እንደሌሎቹ ኬንያውያን ሰርግ ደግሰው ለመጋባት ይቅርና፣ ለመፈራረሚያ የሚሆነውን የመዘጋጃቤት ክፍያ የሚሸፍንላቸው 300 ዶላር አልነበራቸውም፡፡
ከዛሬ ነገ ይሞላልናል በሚል ተስፋ ብዙ ጠበቁ…
እንዳሰቡት ግን አልሞላላቸውም!…
ጥንዶቹ ያቺን 300 ዶላር ሊያገኙ ባለመቻላቸው፣ ጋብቻቸውን ለሁለት ጊዜ አራዝመዋል…
ተስፋ እያደረጉ መዋደዳቸውን ቀጠሉ…
.
በስተመጨረሻ ግን…
ከወራት በፊት፣ ዊልሰን እና አን ተስማሙ…
ቀለል ባለ ሰርግ ለመጋባት ወሰኑ!….
ለጥንዶቹ ቀለል ያለ ሰርግ ማለት፣ 1 ዶላር ብቻ የሚወጣበት ሰርግ ማለት ነው!…
ባለፈው እሁድ ማለዳ…
ሙሽሮቹ ዊልሰን እና አን ሙቱራ ያቀዱትን እውን ሊያደርጉ ተነሱ…
.
ሱፉን ግጥም ያላደረገ፣ በክራባት ያልታነቀ፣ ካረጀች ስስ ቲሸርት በቀር ያልደረበ ሙሽራ ዊልሰን… ያልተኳለች፣ ቬሎ ያልለበሰች፣ አበባ ያልታቀፈች፣ አለምሽ ዛሬ ነው እያለ የሚያጅባት ዘመድ ወዳጅ የሌላት ሙሽራውን ይዞ ከቤቱ ወጣ…
ሙሽራውና ሙሽሪት፣ ያለ ሊሙዚን፣ ያለ አጃቢ፣ ያለ አበባ በታኝ፣ ያለ ሻማ አብሪ በፍቅር ብቻ ደምቀው ወደ ቤተ ክርስቲያን አመሩ…
በሃይማኖታዊ ስርዓት ቃል ተገባብተው ተጋቡ…
በአንድ ዶላር የገዟቸውን የብረት ቀለበቶች አንደኛቸው በሌላኛቸው ጣት ላይ አጠለቁ!…
ሰርጋቸውን አጠናቀቁ!…
.

Image may contain: 4 people, people smiling, text
ይህን ተከትሎ

ጥንዶቹ የአለም መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆኑ!…
በአነስተኛ ወጪ የተከናወነው የዓለማችን ሰርግ ተባለ – የዊልሰን እና የአን ጋብቻ!…
ቢቢሲ ቅድም እንደዘገበው…
የጥንዶቹ ሰርግ በማህበራዊ ድረገጾች ትኩረትን የሳበ መነጋገሪያ ጉዳይ ሆኗል…
“ፍቅር ይበቃል!… ፍቅረኛሞች ትዳር ለመመስረት ፍቅር እንጂ፣ ገንዘብ እስኪኖራቸው መጠበቅ የለባቸውም!… ሳያመነቱ በፍቅር ይጋቡ… ኦና ቤታቸውን ፈጣሪ አምላክ ይሞላዋል!…” ብላለች አን ለቢቢሲ፡፡
የሁለቱ ጋብቻ በመገናኛ ብዙሃን ይፋ መደረጉን ተከትሎ…

በርካታ ግለሰቦችና ኩባንያዎች ለእነዚህ ድንቅ ጥንዶች የአድናቆት እና የስጦታ መዓት ማዥጎድጎድ ጀምረዋል
ቦንፋየር አድቬንቸርስ የተባለ ታወቂ የኬንያ አስጎብኝ ድርጅት፣ ጭር ባለ ማለዳ የተጋቡት ሙሽሮቹ፣ በአንድ ታዋቂ የናይሮቢ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ውስጥ ለአምስት ቀናት ለሚያደርጉት የጫጉላ ሽርሽር ሙሉ ወጫቸውን እንደሚሸፍንላቸው ቃል ገብቶላቸዋል
ሌላ የኬንያ ድርጅትም ሌላ ሰርግ ሊደግስላቸው ተፍ ተፍ እያለ ነው፡፡
ይሄው ድርጅት የሙሽሮቹ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች የሚታደሙበት ሌላ ድል ያለ ድግስ ደግሶ በደመቀ ሰርግ ዳግም ሊሞሽራቸው ቃል ገብቷል፡፡ ሌላ ኩባንያ ደግሞ፣ የሁለተኛውን ሰርግ የፎቶግራፍና የቪዲዮ ስራ ለእኔ ተውልኝ… ቤሳቢስቲን ሳላስከፍል አሽቀብንኜ እሰራላችኋለሁ ብሏቸዋል፡፡
በአሜሪካ የምትኖር አንዲት ኬኒያዊም ለስራ መጀመሪያ የሚሆናቸውን መነሻ ካፒታል ልትሰጣቸው ቃል ገብታለች…
የኬክ፣ የበግ፣ የልብስና የጌጣጌጥ ስጦታውማ አይነሳ!…
.
ፍቅር ይበቃል!…

No comments:

Post a Comment