Monday, January 2, 2017

ዉጥረትን ለማርገብ (በሔኖክ የሺጥላ ሃሳብ ላይና የእሱን ሀሳብ በማይጋሩት ላይ የተሰጠ አስተያየት)


ዉጥረትን ለማርገብ (በሔኖክ የሺጥላ ሃሳብ ላይና የእሱን ሀሳብ በማይጋሩት ላይ የተሰጠ አስተያየት)
ሰመረ አለሙ (semere.alemu@yahoo.com)
ሰሞኑን ሔኖክ የሺጥላ አልፎ አልፎ በሚልከዉ መልእክቱና ለእሱ ምላሸ ከግምቦት 7ና የእነሱን ሃሳብ ከሚጋሩት ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በሚደረገዉ እሰጥ አገባ ወላፈኑ አይሎ ጥግ ይዞ ነገሩን ማስተዋል ቢያስመርጥም ነገሩ ጊዜ ይገዛበት እንደሆን እንጂ የሚሸሺበት ስላልሆነና በርዶም ወደ ቦታዉ የሚመለስ መስሎ ስላልታየኝ ከእይታዬ አንጻር ወገን ግንዛቤየን እንዲያብላላዉ አስቤ ጣቴን ከኮምፒተር በማገኛኘት መልእክቴን ወደ ድር ጥንጥን ልኬዋለሁ።
እንደ ሔኖክ የሺጥላ አባባል አማራዉ ሲጋዝ፤ሲገደል፤ሲዋከብ ጆሮ ያልሰጡት የግምቦት7 ድርጂት አባሎቹና የፖለቲካ ልሳኑ ኢሳት ዛሬ አማራዉ ትእግስቱ አልቆ፤ ልጆቹን አሰባስቦ፤ እራሱን ከጥቃትና ከጥፋት ጠብቆ፤ አማራንና ኢትዮጵያን ለማዳን ላይ ታች በሚልበት ጊዜ ደንቃራ ሁነዉበታል ብሎ ያማርራል። ሔኖክ እዚህ ላይ አላቆመመ የግምቦት 7 የማእዘን ደንጋይ የሆነዉ አማራዉ ከዉዥንብር፤ ከሻቢያና ህወአት ደባ ተላቅቆ ለግምቦት 7ና ኢሳት የሚያዉለዉን የገንዘብ ድጎማና የፖለቲካ ድጋፍ ወደ ወገኑ ቢስብ በየቦታዉ እንደ አዉሬ የሚሳደደዉና የሚታደነው አማራ መብቱ ተጠብቆ ኢትዮጵያም ኢትዮጵያን ሁና ትኖራለች በማለት ሀሳቡን በአጽንኦት ያቀርባል ።
የሔኖክ ተቃዋሚዎች በአንጻሩ የሔኖክን ሀሳብ በተመጣጠነ ሃሳብ ከማክሸፍ ይልቅ በዘለፋና በስድብ በማሸማቀቅ፤ ከህወአት ጋር በማያያዝና ከፖለቲካዉ ምህዳር ለማራቅ በፓል፤በራዲዮ፤ በጽሁፍ ዉንጀላዉን ተያይዘዉታል። ይህን ሀሳባቸዉን ለማንሸራሸር የተጠቀሙበት ዘዴ ግን በረጂም እይታ ሲለካ ሚዛን የሚደፋ ካለመሆኑም በላይ ይህን አባባላቸዉን ያስደገፉበት ማስረጃም በእጅጉ ቀላላ ሁኖ ተገኝቷል። ሔኖክ ቀደም ባለዉ ጊዜ የሰጠዉን አገልግሎት ዉሀ በመቸለስ ባልተወለደ አንጀት ማጣጣል ሔኖክን ሳይሆን የሚያሳጣዉ ያልተመጣጠነና ሚዛን የጎደለዉ ሀሳበ የሚሰጡትን ተቺዎቹን ነው። ጸረ ሔኖክያዉያን የአማራው የሆነ ሁሉ አይጥማቸውም ለሌሎች የነገድ ድርጅቶች የሰጡት ድጋፍ አማራው ላይ ሲደርስ ዘረኝነት ተብሎ ልዩ ስም ይሰጠዋል። ያማራዉ የራዲዮ ፕሮግራም ሲጀመርም አገር ቀዉጢ ሆኗል እንደ ዛሬው ሔኖክ ሁሉ ደምስ በለጠም ተብጠልጥሏል ።
ገንዘብ ሰብስቡ፤ ለአንዳርጋቸው ጽጌ፤ ለበቀለ ገርባ በጋ ክክረምት ሰልፍ ውጡ የሚሉን የጂ7 አስተባባሪዎች ኮለኔል ታደሰ፤ኮለኔል ደመቀ፤የኔ ሰዉ ገብሬና ሌሎች ያማራ ታሳሪዎች ላይ ሲደረስ ለነገሩ ምንም ትኩረት አይሰጡትም። ሌላዉ ቢቀር አማሮች የድርጅት አባሎቻቸዉ ስለአማራ እንዳያነሱ የሀሳብ ጫና ያደርጉባቸዋል።
አንድ ድርጅት ሐገራዊ በሆነ ጉዳይ ላይ ኦፊሴላዊ አቁዋሙን ያስታውቃል። ሌላዉን ወደጎን ትተን ወልቃይት አማራ ነኝ ድረሱልኝ ብሎ የወልቃይት ህዝብ ላነሳዉ ጥያቄ እንዲሁም አስመራ ስለታገቱብን ዜጎቻችንና የአሰብን የባለቤትነት ጥያቄ ለግምቦት 7 አመራር ጥያቄ ቢቀርብም እነሱ ግን ይህን መሰረታዊ ጥያቄ ከአንድ ብርጌድ ጦር በላይ በመፍራት ዝምታን መርጠዋል። ስለጉዳዩም ላለማንሳትን በእጂጉ ይጠነቀቃሉ ስለዚህ ጉዳይ የሚያነሳዉንም በወያኔነት ይፈርጃሉ።
ዛሬ ሔኖክ በጸረ ኢትዮጵያዊነት ሊከሰስ አይችልም ራሱን ወደ አዲሱ ምእራፍ የገፋዉም አማራዉ የሚደረስለት ስላጣና ክጊዜ ወደ ጊዜ የሚሸረብበት ሴራና ሸምቀቆ ከሁሉም አቅጣጫ በመጥበቁ ነዉ። ቀደም ባለው ጊዜማ እሱም ለግምቦት 7 ድጋፉን የሰጠ ዜጋ ነበር። በአሁኑ ወቅት አማራዉ የደረሰበት የእድገት ደረጃ እንደ መጋዣ ታስሮ ተዋርዶ ከመሞት ይልቅ እንደ ቀደሙት ወገኖቹ ታሪክን ሰርቶ መሞትን ነዉ። ለዚህም ታሪካዊ ተልእኮ እንደ ሔኖክ አይነት ውርደትን የተጠየፉ ያማራ ወጣቶች እኔም ሔኖክ ነኝ ብለው ላማራዉ ወገናቸዉ ተነስተዋል። ይህንንም መቀበል ምርጫ የሌለው አማራጭ በመሆኑ ግምቦቶች ሊቀበሉት ግድ ይላል። ያንቀላፋዉ ያማራዉ ወጣትም ድጋፉን በገሀድ አሳይቷል ብዙ ሔኖኮችም ተፈልፍለዋል። ከጅምሩ እዚህ ከደረሰ ጊዜ አልፎ ጊዜ ሲተካ ሔኖክና መሰሎቹ ከአንጋፋ ወገኖቻቸው እዉቀትን ካካበቱ ለቆሙለት ህዝብና ሀገር ብዙ መስራት እንደሚችሉ ጥርጥር አይኖርም። አንድ የማይካድ ነገር ግን ሔኖክና መሰሎቹ ከአማራዉ ሰቆቃ አልፎ እይታቸዉ ኢትዮጵያ መሆኑን ደጋግመዉ ገልጸዋል ተቃዋሚዎቻቸዉ ግን ይህንን ያለመስማት ወይም አጣምሞ የመተርጎም መብታቸዉ የተጠበቀ ነዉ።
በኢሳትና በግሞቦቴዎች አማካይነት ከሞት ወደ ህይወት የተሸጋገሩ ጸረ ኢትዮጵያ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን በሰፋት ተመልክተናል፤ የኢትዮጵያ ባንዲራ ህልዉናዉ ከሞተ ድርጅት ጎን ለጎን ተሰቅሎ አገር ለዉርደት ተዳርጎም ታዝበናል።በግምቦት 7 አቀንቃኞች ሻቢያ የኢትዮጵያ ነጻ አዉጭ ሁኖ ተሰብኳል፡ በቪዠን ኢትዮጵያ አንዳንድ አሳፋሪ ዜጎች ለሻቢያ ሲሰግዱም ተመልክተናል። በቅርቡ እንኳን ዶር ታደሰ ብሩ ከርሰሞ ሻቢያን ነኩብኝ ብለዉ አማርረዉ ጽፈዋል። አቶ ነአምን ዘለቀም በቪዢን ኢትዮጵያ (ቪዢን ኤርትራ ቢሉት ይሻል ነበር) አንድ ሀገር ወዳድ በደም ፍላት እስከ መቼ ሻቢያን በአንቀልባ አዝለን እኖዛራለን በማለቱ ትእግስታቸዉ አልቆ ወደ መድረኩ ተንደርድረዉ ተናጋሪዉን ከማነቃቸዉ በፊት ተናጋሪዉ ድምጽ ማጉያዉን አስረክቦ ከዉርደት ድነናል።
ኢሳት ከግምቦት 7 ጋር ይህ ነዉ የማይባል ቁርኝት አለዉ በቪዢን ኢትዮጵያ ላይ ሻቢያ ተነካብኝ ብለዉ በግልግል ወደቦታቸዉ የተመለሱት አቶ ነአምን ዘለቅ የኢሳትና የግምቦት 7 ከፍተኛ አባል ናቸው። አቶ አንዳርጋቸዉ ወደ እስር ከተወረወሩ በሗላም አቶ አበበ ገላዉ የግምቦት 7 አባል መሆኑን ኦፊሴላዊ አድርጓል በተከታዩም የኢሳት ቦርድ ከፍተኛ ባለ ሰልጣን ሁኖ ተሹሟል። ችግሩ እነዚህ ግለሰቦች ለምን የግምቦት 7 አባል ሆኑ አይደለም ጥያቄዉ ይህንን ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል የሚዲያ ተቋም በነዚህ ከፍተኛ በሆኑ በግምቦት 7 መሪዎች ስር ማዋሉ ኢሳትን ነጻና ገለልተኛ ካለማድረጉም በላይ አገራችን ዉስጥ በሚደረገዉ ትግል ሚዛኑን ያስታል ከሚል እውነታ የመነጨ ነዉ።
ባጠቃላይ ከላይ የተመለክቱትን ተያያዢ ሁኔታዎችን ስናገጣጥም ግምቦት 7 ኢሳት ነዉ ኢሳትም ግምቦት 7 ነዉ።እዚህ ላይ አንድ የሚዲያ ተቋም በአንድ የድርጂት ፍልስፍና ከተቃኘ የድርጅቱ ልሳን እንጂ ነጻ የሚዲያ ተቋም ሊሆን አይችልም ድርጅቱን የሚቆጣጠረው አካል ሚዲያዉን ይቆጣጠረዋል፤ ሚዲያውም ቅኝቱ ከድርጅቱ ፍልሰፍና ይዋሀዳል እውነታን የሚያይበትም በድርጅቱ መነጽር በቻ ይሆናል። ብሄራዊ ሚዲያዎች ከብሄራዊ ፖለቲካ ድርጂቶች ነጻ ከሆኑ የሚያዩትን የሚሰሙትን ያለምንም ይሎኝታ ያጋልጣሉ፤ እርምት እንዲወሰድ ያሳስባሉ፤ ሚዛን ያስጠብቃሉ ባጠቃላይ ነጻና ገለልተኛ ይሆናሉ ይህም ጠቃሚነቱ ለሀገርና ለህዝብ ይሆናል ማለት ነው። ኢሳት ግን በዚህ መንፈስ ባለመዋቀሩ የአማራዉ ተወካዮች ስለደረሰባቸዉ በደል ለህዘብ ለማሳወቅ ወደ ቢሮዋቸው በሚመጡበት ጊዜ ለሌሎች ድርጂቶች የሚሰጡትን ከለላ ነፍገዋቸዉ ይባስ ብለዉ በሚመራ ጥያቄ (leading question) በማዋረድ፤ በማዋከብ ስብእና የሚነኩ ጥያቄዎችን በመጠየቅ፤ አማራዉ ላይ የደረሰዉን በደል በማጣጣል በባይተዋርነት ያሰናብቱዋቸዋል።
ዛሬ ሔኖክን የሚከስሱ ወገኖች የግምቦት 7 መሪ ዶር ብርሀኑ ነጋ ላንቃቸዉ እስኪደክም ለህወአት የዘመሩ፤ የተቆረጠች ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ በመጻፋቸዉ ለህዝብ ያስተዋወቁ፤ መለሰ ዜናዊ ቢሮ ያለ ቀጠሮ ወጣ ገባ ይሉ እንደነበር የዘነጉ ይመስላል። ይህች ፎቶም ስለ ዶር ብርሀኑ ብዙ ትናገራለችና ብትታይ አትጎዳም( http://www.smgebru.com/2007/09/twice-benefit.html#!/2007/09/twice-benefit.html)። ከህወአት ቤተኝነታቸዉ ከተገለሉ በሗላ ዶር ብርሐኑ በየስብሰባዉ የአማራዉን ጨቋኝ አባርሬ የትግሬን ጨቋኝ ለመተካት አይደለም ብለዉ ያለ ማስተዋል የወረወሩትን ዘለፋ አባሎቻቸዉ አቃልለዉ ተመልክተዉት ይሆናል። ይህን ሀሳብ በጥላቻ ትኩሳት ከመወርወር ባሻገር የአማራዉን ጨቋኝነት በምሁራዊ ትንታኔና በተጨባጭ ያስረዱበት ወይም ደግሞ በድፍረት ካቻዎቻቸው ጋር ቦታና ጊዜ መርጠው ለመፋለም የጠየቁበት ጊዜ የለም። ዶር ብርሐኑ ቆርጠው ይህን ፍልሚያ በልበ ሙሉነት ከመረጡ ያለቅድሚያ ዝግጅት የአንድነት ሀይሉን ወክሎ ዶር አሰፋ ነጋሽ እሳቸው በመረጡት የምሁር ደብር ተገኝቶ እንደሚፋለም በልበ ሙሉነት ማረጋገጥ ይቻላል እምነትም አለን። ዛሬ አማራዉ እሳቸዉ ከመለስ ዜናዊ ጋር በቀመሩት ቀመር ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስበት ያንን ሳያገናዝቡ አንድ በአስተሳሰብ የተጎዳ ተራ ዜጋ ሊናገረዉ የማይደፍረዉን መናጋራቸዉ ከማዘን አልፎ ጊዜዉ ሲደርስ ሊያስጠይቃቸዉም ይችላል ባይ ነኝ።
በሌላዉ አንጻር ሔኖክ እንደ ዶር ብርሀኑ ወይም እንደ አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌ የህወአት በረከት ተቋዳሸ አይደለም ። ቀደም ባለዉ ጊዜም ተወልዶ ተራማጂ ተራጋጭ በሚል የጥራዝ ነጠቅ ፖለቲካ ዉስጥ ገብቶ የኢትዮጵያ ጀግኖችን አስገድሎ አገርን በዘር የሚያምስ ፍልስፍናም ላይ አሻራዉ አላረፈም። ያለ መታደል ሁኖ አእምሮዉን በእዉቀት በሚያጎለበትበት እድሜዉ ሀገሩንና ወገኑን ለማዳን ከታላላቆቹ ጋር በጨበጣ ዉጊያ ተሰልፏል። ሔኖክ ላይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለሚወረወርበት ጥቃት የአማራ ጉዳይ ያገባኛል የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ዜጋ ሁሉ ሊመክትለት ይገባል።
ጁዋር መሀመድ፤ሰየ አብረሀ፤አረጋዊ በርሄ፤አለምሰገድ ገ/አምላክ፤ሌንጮዎችን የመሳሰሉት ከግምቦቶች ክብርና ሙገሳ ሲቸራቸው ሔኖክ ላይ የተቀነባበረ ጥቃት ማድረስ አሁንም መዳረሻዉ ሔኖክ ሳይሆን አማራና ኢትዮጵያዊነት ላይ መሆኑን መዘንጋት የለበትም። ሔኖክ በቅርቡ በለቀቀዉ ጽሁፉም አማራዉ አክብሮ ብቻ ሳይሆን ተከብሮም የሚኖርባትን ኢትዮጵያን ለመፍጠር በርትቶ መደራጀትና መታገል እንዳለበት ጥቃት ለደረሰበት ለአማራዉ ወገኑ አስገንዝቧል በዚህም መልእክቱ ስፍር ቁጥር የሌለዉ የአማራ ተወላጂ ከጎኑ መቆሙን በተግባር አሳይቷል። ቀደም እንዳለዉ ጊዜ አማራዉ ያፍ ማሟሻ ሁኖ ያለ መቅረቱንና ለተወረወረዉ ድንጋይ ሁሉ ምላሽ መሰጠቱን ከሰሞኑ ግብግብና የሔኖክ ደቀመዝሙሮች ለሔኖክ የሰጡትን የተግባር አንድነት የሔኖክ ተፋላሚዎች ጉዳዩ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ሊገነዘቡት ይገባል። የመዉጊያዉን ብረት ብትቋቋም ላንተ ይብስብሀል የሚለዉን የመጽሃፍ ጥቅስም አብሮ ማገናዘብ ጥቅም ያለው ይመስላል።
በፈረንጆቹና ባንዳነት አንገታቸዉን ባስደፋቸዉ የባንዳ ልጆች አማራው ላይ የተቀነባበር ጥቃት ተከፍቷል ይህን ተከትሎ አማራዉ እራሱን ከጥቃት እንዳይከላከል የሚሰነዘሩት የማጃጃያ ሀሳቦች ብዙ ናቸዉ። እስከዛሬ ለመከራዉ ጆሮ ያልሰጡት ሃሳብ ሰጭዎች በአማራነት መደራጀት ኢትዮጵያዊነትን አያሳንስም ወይ ብለው ይጠይቃሉ? አዎ በጣም ያሳንሳል ነገር ግን አማራዉ በነገዱ ሲደራጂ የመጨረሻዉ ነገድ እንጅ የመጀመሪያዉ አይደለም ሌሎች በነገዳቸዉ ሲደራጁ ጭቆናን ለመከላከል የሚል ሽፋን የሰጡት ግምቦቴዎች አማራዉ ሲሞክረዉ ግን ዘረኛ ብለዉ ይፈርጃሉ። በአማራዉ ላይ የሚደረገዉ ግፍና በደል ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ አማራው በኢኮኖሚ፤ በማህበራዊ ኑሮዉ፤ ከብሄራዊ ጥቅሙ ከመገለሉም ባሻገር ቀጥታ የሆነ የዘር ማጥፋት እርምጃ በህዋአትና ደጋፊዎቹ እየተፈጸመበት ይገኛል። ይህ ነገር ከጅምሩ የገባችው ፕሮፌሰር አስራት እንዳሉት ቢታገልም ባይታግለም በኢትዮጵያ ጠላቶች ስለሚገደል ያለው ምርጫ ታሪከን ሰርቶ እራሱን አስክብሮ ወደማይቀረው አለም መጉዋዝ ብቻ ይሆናል። ይህም እንደ በላይ ዘለቀና ሌሎች ወገኖቹ ስሙን ከመቃብር በላይ ያዉለዋል።
ከላይ በተገለጸዉ መሰረት ህወአት አማራ እሳከለ ድረስ ትግሬ ትግሬን ሁኖ መኖር አይችልም ብሎ በፖሊሲ ደረጃ በነደፈዉ ጽንፈ ሀሳብና ይህን ሀሳብ እንዲጋሩት በፈለፈላቸዉ የነገድ ድርጅቶች አማራውን ከገደል በመወረወር፤በእሳት በማጋየት፤በእምነት ቦታዉ በእሳትና በስለት በመቁረጥ፤በመግደል ፤ ከኖረበት አገሩ በማፈናቀል በዘመናችን ሊደርስ የማይታሰብ ግፍና ሰቆቃ አድርሰውበታል። (https://www.youtube.com/watch?v=A-ZynRrv0uU)።
ዛሬ የኔ ሰዉ ገብሬ በወጣትነቱ ማንኛዉም ዜጋ እንደ ህልም የሚያየዉን ሙያዉን ትቶ የህወአትን ዘረኝነት ለማጋለጥ በወሰደዉ እርምጃ ወደ እስር ተወርዉሯል የሚያሳዝነዉ በዛዉ አገር በተደጋጋሚ አቶ አንዳርጋቸዉ እንዲፈታ ምልጃ ሲደረግ ሰለየኔ ሰዉ ገብሬ ግምቦት 7ና ኢሳት ዝምታን መርጠዋል የኔ ሰዉ ገብሬ የኮንጎ ተወላጂ እንደ ሆነ ሁሉ። ለመሆኑ የግምቦት 7 አባሎች ወይም የኢሳት ጋዜጠኞች የኔ ሰው ገብሬን አይነት የበራ እድልና ስራ ቢኖራቸዉ እሱ ያደረገዉን እርምጃ ይሞከሩት ይሆን? በፍጹም አይሞከሩትም ከብዙዎቹ እንተዋወቃለንና። በእዉነት የኔ ሰዉ ገብሬ፤ኮለኔል ደመቀ፤ኮለኔል ታደሰ ሙሉነህ ገድል ከለሊሳ ፈይሳ፤ ከበቀለ ገርባ አስተዋጽኦ አንሶ ይሆን ለስራቸዉ ሺፋን ያልተሰጠዉ? በፍጹም መልሱ እነዚህ ግለሰቦች አማራ በመሆናቸዉ አስተዋጽዋቸዉ የግምቦት 7 ድርጅትንም ሆነ የኢሳት ጋዜጠኞቹን ቀልብ ሊስብ ባለመቻሉ ነው።አሁን ግን የአማራዉ ህመም ህመሙ የሆነዉ ድርጅትና ህዝብ ተጋድሎዋቸዉን ይዘክረዋል።
ወደ ማጠቃለያው ሲመጣ
ኢሳትን በተመለክተ
ኢሳት በልምድም በስርጭትም ጎልብቷል ነገር ግን ኢሳት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንዲዉል ከተፈለገ የግምቦት 7 አባሎች ባስቸኳይ ከኤዲቶሪያል ቦርዱ እንዲለቁ ሁነዉ በነጻ አመለካከታቸዉና በህዝብ ዘንድ ከበሬታ ያላቸዉ በምሁር መመዘኛ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ፍቅር ያላቸዉ ግለሰቦች ተመርጠው ቦታዉን እንዲይዙት ማድረግና የግምቦት 7 አቀንቃኝ ጋዜጠኖች ከድርጅት መንፈስ በጸዱ ጋዜጠኞች እንዲተኩ ማድረግ። ኢሳት በኢትዮጵያዉያን መዋጮ እንጂ በግምቦት 7 መዋጮ የሚካሔድ የሚዲያ ተቋም ባለመሆኑ ዜጎች ለምንጠይቀዉ የማሻሻያ እርምጃ በቀና መንገድ ጉዳዩ ታይቶ የማሻሻያ እርምጃ ቢወሰድ ጠቃሚነቱ ለኢሳትም ጭምር መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን። ነገር ግን ኢዉነትም መንገድም በኛ በኩል ነዉ ተከተሉ እንጂ አትጠይቁ ከተባለ የኢሳት መጻኢ ጊዜ ክማንም በላይ ለኢሳት አስቸጋሪ ጊዜ የሚገጥመዉ መሆኑን ልናስገነዘብ እንወዳለን።
ሔኖከን በተመለከተ
ሔኖክ ወጣትና በድር ጥንጥን እንደምናያቸዉ ጸሃፍት ቀደም ባለዉ ጊዜ ተቧድነህ ዜጋ በእጂህ ያለፈ ወጣት አይደለህም በሀገርህም ላይ ግፍን አልሰራህም በዚሀ ልትኮራ ይገባሃል። የነገርን ሙዳ ሲቆርጡና ጥለፈዉ ጣለውን አሰራር ክተቀኙት ጋር ሞራልሀን ማቆሸሺና እራስሀን ወዳልፈለግኸዉና ወዳላሰብክው መንገድ መጠለፍህ ላንተ የሚበጂ አይመስልም። ለሀገርሀ ባቅምህና በእዉቀትህ ስራ። ለሀገር ለወገን በሚጠቀም ጉዳይ ላይ ምከር አንጂ ባለፈዉ እንዳደረጉህ አንተን ጭቃ ለመለወስ ክሚደረገው ውይይት፤ቃለመጠይቅ፤ክጽሁፍ እሰጥ አገባ መልስ እራስህን አርቅ። መኖርህን በእዉቀት መተናጸህን የሚፈልግ አገርና ህዝብ ስላለህ በርትትህ ተማር። በትምህርትህ ተቀናቃኞችህ ሳይፈልጉ በግድ እንዲያከብሩህ ይገደዳሉ። በዚህ አጋጣሚ በየሀገሩ ደቀመዛሙርትህ ስለተበራክቱ በማንኛዉም መንገድ ሞዴላቸዉ ሁነህ ተገኝ በትምህርት እራስህን አንጽ።
ግምቦት 7ን በተመለክተ
ባጠቃላይ ግምቦት 7 ዉስጥ እንደማንኛችንም በሀገር ፍቅር ስሜት የነደዱ ብዙ ዜጎች ይገኙበታል በዚያዉ ልክ ኢትዮጵያ ክእጃቸዉ ያመለጠችባቸዉ ኤርትራዉያንም ግምቦት 7ን ታክከዉ ጉዳያቸዉን ሊያሰፈጽሙ ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ። የዘር ድርጂቶችም ከአንድነት ይልቅ ለነሱ ከፋፋይ አላማ የተምበረከከ ስለሚመስላቸዉ ስራዉን በአሉታ ይመለከቱታል ድጋፋቸዉንም ይለግሱታል። የአንድነት ሐይሎች ግን በሻቢያ በኩል ጤናማ ነገር እንደማይገኝ አጥብቀዉ ያምናሉ ስለዚህም የግምቦት 7 አካሄድ አይመቻቸዉም ልሳኑ ኢሳትም የግምቦት 7ን ተንበርካኪነት ስለሚያስተጋባ አጥብቀዉ ይጠሉታል፤ ህወአትና ሻቢያ ትላንተ ባገራቸዉ ላይ የፈጸሙትንም እንዲህ ባጭር ጊዜ የሚረሱት አይሆንም። ለዚህም የሚያቀርቡት ምክንያት ቀደም ባለው ጊዜ በኤርትራ በኩል ነጻነት ሊመጣ ይችላል በሚል ወደዛዉ ተጉዘዉ በኢሳይያስ አፈወርቅ ኤርትራ የተንገላቱትን የሞቱትን በእሰር የሚማቅቁትን ዜጎች ክግምት በማስገባት ነው።
ነገሩን ወደ አንድ ወገን ሲሸክፍ ግምቦት 7 ኢትዮጵያዊ ድርጅት ሁኖ እንዲወጣ ትግሉን ኢትዮጵያዊ ማድረግ ይኖርበታል ለትላንትናዋ ክፍለ ሐገራችን ኤርትራ ተንበርክኮ ጥንታዊት ኢትዮጵያን ማዋረድ አይገባዉም። ትግሉን በሀገሩ ጫካ፤ሜዳ፤ወንዝና ሸንተረር አድርጎ የሚታይ ስራ መስራት አለበት ገንዘብ ብቻ አዋጡ አትተቹኝ አትጠይቁኝ የሚለዉ አባባል የትም አያደርሰዉም። እንደዉም አመራሩም እንደ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ወደ ንግስና እያመራ ስለሆን በአዲስ አባላቱ ቢተካ ለጥንካሬዉ ይበጃል ባይ ነኝ። በተረፈ አገርን ነጻ ከማውጣት ይልቅ ተቹኝ በሚላቸዉ ላይ ብቻ ካነጣጠረ መጨረሻዉ እንደማያምር ለመናገር ሊቅ መሆን አያስፈልግምና ትኩረታችሁ ታላቅዋ ኢትዮጵያ ላይ እንጂ በንፋስ አድራሹ ታሪክ ተመስርታችሁ መሆን እነደሌለበት ልናስገነዝብ እንወዳለን። ተፈለገም ተጠላም ዶር ሐይሌ ላሬቦ እንዳለዉ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያን ሁና ትቀጥላለች ተረተኞችም በአንድ ወቅት እንዲህ ተሞክሮ ነበር በሚል ገጽ በታሪክ ቦታቸዉን ይይዛሉ።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ለማንኛዉም ለትችት፤ለእርማት፤ለመማማር ክላይ በጻፍኳት አድራሻ ፈልጉኝ። መልካም ገና እና አዲሰ አመት

No comments:

Post a Comment