Wednesday, January 11, 2017

በቅንነት እና ለውጥ ይመጣል በማለት በኤርትራ የሚሰቃዩ ወገኖቻችን ሃላፊነቱን ማን ይውሰድ ? ኄኖክ የሺጥላ


ነፃነት እውነት ላይ መሰረት ሲያደርግ ድል ቅርብ ይሆናል ። በቅንነት እና ለውጥ ይመጣል በማለት በኤርትራ የሚሰቃዩ ወገኖቻችን ሃላፊነቱን ማን ይውሰድ ? ማን ነው ተጠያቂ መሆን ያለበት ? እስከ መቼ እየዋሹን ? እስከ መቼስ አዳራሽ ከበን እያጨበጨብን እንኖራለን ?
==== ኄኖክ የሺጥላ -======
አንዳርጋቸው ፅጌ ከተያዘ ልክ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እዚህ ሳኖ’ሆዜ የኢትዮጵያዊያኖች እግር ኳስ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። በዚያ ዝግጅት ላይ ለኢሳት የገቢ ማሰባሰቢያ ተገኝተን ነበር ። በወቅቱ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ባደረገው ንግግር የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቆ ነበር ። እኛም በአንዳርጋቸው መያዝ የተስማንን ጥልቅ ሃዘን ገልጠናል ።
አንዳርጋቸው ከመያዙ በፊት ፥ « ብርሃኑ ነጋ ለምንድን ነው ጫካ የማይገባው ?» ለሚለው መልስ የድርጅታችን ሰዎች ይሰጡ የነበረው መልስ « ሁሉም ሰው ጫካ መግባት የለበትም » የሚልም እንደነበር አስታውሳለሁ። አንዳርጋቸው ከተያዘ በኋላ ግን የበርሃው አመራር ላይ አንድ አብይ ( መሰረታዊ ክፍተት ) ያለ በማስመሰል ያንን ለመሙላት ሲባል ብርሃኑ ነጋ « በርሃ መውረድ» እናዳለበት ፥ እሱም ብርሃኑ ይህንን ማድረግ እንደሚያስፈልገው ጭምጭምታዎች ብቅ ይሉ ጀመር ። ከአንዳርጋቸው መይዝ በፊት በኤርትራ በርሃ መሰረታዊ የትግል እውቀት ያለው ፥ በዘመናዊ ትምህርትም ቢሆን በማዕረግ የተመረቀው ዘመነ ካሴ ፥ የአንዳርጋቸው ዕጌን ቦታ ተክቶ መስራት እንደሚችል ቢታወቅም ፥ የአንዳርጋቸው መያዝ እንደሚሉን « አንዳርጋቸው መስራት ያለበትን ሰርቶ ከሆነ የተያዘው » በምትኩ ዘመነ ካሴን ሾሞ በኤርትራ የሚደረገውን ትግል ቀጣይ ማድረግ ይቻል ነበር ። ይህ እንዲሆን ያልተፈለገበት ምክንያት ዘመነ ካሴ አቅሙ ስለሌለው ሳይሆን ፥ በነብርሃኑ ቁና ሲለካ ዘመነ የወጣለት አማራ ነው ! ዘመነ ካሴ የሚያስፈልገው የጎጃም ልጆችን አባብሎ ወደ በርሃ እንዲያስገባ እንጂ ከዚያ ባለፈ ወደፊት መጥቶ የመሪነት ቦታ ላይ እንዲቀመጥ አልነበረም ! በውህደቱም ጊዜ ሆን ተብሎ እነ መዓዘው ጌጡን የአርበኞች ግንቦት ሰባት ምክትል ሊቀመንበር ተደርገው የተመረጡበት አብዩ ጉዳይ መዓዘው በአግባቡ መራመድ የማይችል እና ስፓይናል ኮርዱ ከመኪና ላይ ወድቆ የተቀጠቀጠ ሰው እንደመሆኑ ቢሾም ምንም ተፅኖ ማምጣት የማይችል ፥ ተኩሶ የማይገል ፥ ተናግሮ የማያሳምን ፥ መክሮ የማይሰማ እንደሆነ በደንብ ስለሚረዱ ነበር ።
ለምሳሌ ለረጅም ግዜ ከኔ ጋር በፌስ ቡክ የመልዕክት ልውውጥ ስናደርግ የነበረው አርበኛ ኑርጀባ ፥ ባንድ የፌስ ቡክ ውይይታችን ( ወደፊት አወጣዋለሁ ) አብዛኛውን ጊዜውን አስመራ እንደሚያሳልፍ አጫውቶኛል ። በወድሜ ሲሳይ አጌና አገናኝነት ፥ አንድ መንግስቱ ከሚባል እና አሁንም ኤርትራ ( አስመራ ውስጥ ) ከሚኖር የቀድሞ የአርበኞች ግንባር አካል ከነበረ ሰው ጋም ያደረግነው የመልዕክት ልውውጥ ተመሳሳይ ነው ።
እዚህ አማሪካ ዳላስ ነዋሪ የነበረ ፥ ስሙ ሸዋ የተባለ ( በጣም ቅን እና ጥሩ ልጅ ) አንዳርጋቸው በተያዘበት ሰሞን እዚህ ሳን ሆዜ መጥቶ ስለ ትግሉ ለደጋፊዎች ማብራሪያ እና ገለፃ ሲሰጥ ፥ በወቅቱ ከትህዴን ጋር ሊኖር ስለሚችለው ውህደት በሰፊው አብራርቶ ነበር ። ከስብሰባው በኋላ እኔ እና እሱ ( ሁለታችን ብቻ ) በአንድ የኢትዮጵያ ሬስቶራን ገብተን ስለ አስመራ ትግል ለረጅም ሰዓት ተወያይተን ነበር። ሸዋን እንዴት በርሃ መግባት ፈለግህ ስለው የሰጠኝ መልስ « እኔ እንጃ!» የሚል ነበር ። በይበልጥ በርሃ ከመግባቱ ጥቂት ቀናቶች ( ወር ) በዳላስ የግንቦት ሰባት ደጋፊዎች እንዳይደውሉለት ስልኩን አጥፎ እንደነበርም አጫውቶኛል ። በይበልጥ ግን ከውይይታችን ውስጥ ሁሌም ከጭንቅላቴ የማይጠፋው « እኔ ኤርትራ መሄድ እፈልጋለሁ ፥ በዚህ ላይ ያንተ ምክር ምንድን ነው ?» ብዬ ለጠየቅሁት « ሄኖክ እኔም እንዳንተ ሴት ልጅ አለችኝ ፥ ልጄን በጣም ነው የምናፍቃት ፥ ናፍቆቱ ይሁን ምንም አይደለም ፥ እኔን በጣም ያመመኝ ይህንን ሁሉ መስዕዋትነት የከፈልኩለት ድርጅት ይህ ነው የሚባል ነገር እንዳልሰራ እዛ ስደርስ ነው የተገነዘብኩት ፥ ያም ሆኖ ፍላጎትህ ከሆነ አታድርገው አልልህም ፥ እንደ ወንድም የምመክርህ ግን ለልጅህ ጊዜ ስጣት ፥ ልጄን እንዴት እንደምናፍቃት ልነግርህ አልችልም » በማለት ትልቁን ጥያቄ ጭሮብኝ አልፏል !
ነፃነት እውነት ላይ መሰረት ሲያደርግ ድል ቅርብ ይሆናል ። በቅንነት እና ለውጥ ይመጣል በማለት በኤርትራ የሚሰቃዩ ወገኖቻችን ሃላፊነቱን ማን ይውሰድ ? ማን ነው ተጠያቂ መሆን ያለበት ? እስከ መቼ እየዋሹን ? እስከ መቼስ አዳራሽ ከበን እያጨበጨብን እንኖራለን ?
ግንቦት ሰባት እንደ ድርጅት የመሪውን የአንዳርጋቸው ፅጌን አያያዝ እና ሚስጢሩ ያፈተለከበትን ሁኔታ እስከ አሁን ሊገልፅልን አልፈቀደም ! ምክንያት አይታወቅም ? ምክንያት አይጠየቁም ! ምክንያት ይህንን ማወቅ አደገኛ ነውና !!!!
ኄኖክ የሺጥላ

No comments:

Post a Comment