Monday, January 23, 2017

አትነጋገሩ ብሎ መምከር ጥሩ ፖለቲካ አይደለም – ፍቃደ ሸዋቀና


   

አትነጋገሩ ብሎ መምከር ጥሩ ፖለቲካ አይደለም – ፍቃደ ሸዋቀና
የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ተቃዋሚዎችን ለድርድር መጥራታቸውን መቃወምም ሆነ እንዳይሳተፉ መምከር ጥሩ ፖለቲካ አይደለም። በመርህ ደረጃ አላማው ምንም ይሁን ምን ማንም ተቃዋሚውን ለውይይትም ይሁን ለድርድር ሲጠራ መቃወም ብልህ ፖለቲካ አይደለም። ፖለቲካ አኮ በትርጉም ደረጃ የመደራደር ጥበብ ( the art of compromise) ነው።
ትልቁ ነገር በድርድሩ መድረክ ላይ የሚቀርበው ጉዳይ ነው። ማወቅና ማረጋገጥ ያለብን በድርድር ጊዜ ተደራዳሪ ወገን ከድርድሩ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት የማድረግን ጉዳይ ነው። ተቃዋሚዎች መሰረታዊ የሚሉዋቸውን የሚታገሉላቸውንና እንዲለወጡ የሚፈልጉዋቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮርና ቢያንስ በከፊል ወይም በሙሉ መልስ የማያገኙ ከሆነ ድርድሩን ተገቢ መግለጫ አውጥተው ማቋረጥ ከቻሉ የፖለቲካው ትርፍ የነሱ የሆናል። የፖለቲካ አሸናፊነቱን ተቀዳጁ ማለት ነው። ገዝዎቹም ተመሳሳይ አላማ ይዘው ስለሚመጡ ከቀናቸው አሸናፊ መሆን ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለሚፈጽሙት እብሪት ሁሉ ይሁንታ እንዳገኙ የሚቆጥሩበት ሁኔታ ለራሳቸው ይፈጥራሉ። ጥልቅ ተብዬው ተሀድሷቸውና የማናውቃቸውን መስለው ለመታየት የሚያደርጉት ሙከራ ተጠናቀቀላቸው ማለት ነው።
የፖለቲካ እስረኞችና ጋዜጠኞችን እንዲፈቱ የመጠየቅ ቅድመ ሁኔታ ልድርድሩ የመነሻ ሃሳብ መሆን አለበት። ዋናዎቹ ተደራዳሪዎች መሪዎች በወህኒ ባሉበት ሁኔታ በመሰረቱ ድርድር እናድርግ ማለት ቀልድ ነው። ይህ ከተሙዋላ የነጻ ምርጫ ቦርድ ጥይቄ፣ መንግስት በግፍ ሰለግደላቸው ወገኖች ስላሰራቸውና ስላንገላታቸው ወገኖች በዝርዝር የሚያጣራ ነጻ መርማሪ ኮሚሺን ስለሚቋቋምበት ሁኔታና ወንጀል የፈጸሙ ባለስልጣኖች ተጠያቂ ስለሚሆኑበት ሁኔታ መደራደር ያስፈልጋል። በሀገራችን ከነጻ ምርጫ ይልቅ ባሪያ ፍንገላ የሚመስለው ዲሞክራሲ ተብዬ ምርጫ ፈጽሞ መቀየር እንዳለበትና በአለም ላይ ፍጹም እምባገነኖች ብቻ የሚያገኙት የፓርላማ መቀመጫን መቶ ፐርሰንት መቆጣጠር የሚወገዝ ጸረ ዴሞክራሲ ተግባር መሆኑን ተደራዳሪ ወገኖች አምነው እንዲያወግዙ ተቃዋሚዎች መጠየቅ አለባቸው። የመንግስት ሀይሎች ህጋዊ ሰላማዊ ሰልፎችን ስብሰባዎችን ለማደናቀፍ ያደረጉዋቸው ሙከራዎች ተዘርዝረው ገዥው ወገን ይቅርታ እንዲጠይቅ ማድረግ ተገቢ የድርድር መነሻ ነው። አንዱ መሰረታዊ የሀገሪቱ ችግር ከአፓርታይድ ባልተናነሰ ሁኔታ የሀገሪቱን የመከላከያ የደህንነትና የኢኮኖሚ ተቁዋማት በህወሀት የበላይነትና ባንድ ብሄረሰብ ተወላጆች እጅ ስር በመሆኑ ይህ ሁኔታ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ለተመልካችና ለሰሚ የሚቀፍ አሰራር መወገድ እንደላበት መስማማትና ባጭር የጊዜ ገደብ ውስጥ ሙሉ ለውጥ እንዲደረግ መጠየቅ የተቀዋሚዎች ትልቅ ጥያቄ ሊሆን ይገባል። ሀገሪቱ ውስጥ ያለው ምሬት እንዱና ዋናው ይህ መረን የለቀቀ በዚህ ዘመን ሊታይ የማይገባው አሳፋሪ አፓርታይድ ስርዓት መሆኑ ገሀድ ከሆነ ቆይቱዋል። ይህን ለመቀየር የማይታገል ተቃዋሚ ሀገሪቱ ጥፋት ላይ የሚተባበር መሆኑን ማወቅ ይኖርበታል።
ድርድሩ የጸረሽብር ህግ የሚባለው ሀግና ባሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶች አፈራረጅ እንደገና ተመርምሮ በስካሁኑ መልኩ ያለው አተገባበር እንዲለወጥ። ባሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶች የድርድሩ አካል እንዲሆኑ መጠየቅ ለዘላቂው የሀገሪቱ ሰላም አስፈላጊ መሆኑን የመንግስት ወገን እንዲቀበል ማድረግ ያሻል።
ገዥውቻችን ድርድር የፈለጉበት ምክንያት ይገባናል። ነገሩ “የጥልቁ ተሀድሶ” አካል ነው። ለተደራዳሪ ፓርቲዎች ጊዚያዊ መሸንገያ የሚሆኑ ነገሮችን ሰጥተው ፣ የፖለቲካ ሂሳብ የከፈሉ መስለው ተሀድሶ የሚሉት የማላገጥ ስራ የምር መስሎ እንዲታይላቸው ለማድረግ ነው። ይህንን ለወገንም ለባዕድም ለመሸጥና ለራሳቸው ስልጣን አገዛዝ አዲስ ሊዝ ለመቀዳጀት መሆኑ ይገባናል። ያልገባን ካለን ሊገባን ይገባል። ይህ ዶሮ ጭራ ልታወጣው የምትችል ምስጢር ነው። ድርድሩ እነዚህን ከላይ ያነሳናቸውን ቅድመ ሁኔታዎችና አጀንዳዎች ካላካተተ ዋጋ ቢስ ነው። ተቃዋሚዎች ይህን ተረድተው እነዚህ ነገሮች ድርድር ካልገቡ አንወያይም ብለው ረግጠው ቢወጡ አሸናፊዎችና ይህዝብ ወገኖች መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። በታሪክም ትልቅ ሬኮርድ ያስመዘግባሉ።
በዚህ ድርድር ውስጥ በግልጽና በጥንካሬ የሚታገሉ ፓሪቲዎች ያሉትን ያህል እንደነ አየለ ጫሚሶ ያሉ ሀፍረት የማያውቁ ራሳቸውን አገልጋይ የሆኑ የፓሪቲ መሪዎችና ፓርቲዎች መኖራቸውንና መንግስት ካላቸው ቃል ውልፍት እንደማይሉ እናውቃለን። እነዚህ የፈለጉትን ይወስኑ። ድርድሩ በአሸናፊነት እንዲያልቅ የመታገል ነገር የምር ተቃዋሚ ነኝ ከሚሉትና ነን ከሚሉን ብቻ የምንጠብቀው ነው። እንዴውም የምር ተቃዋሚ ለመለየት ጥሩ እድል ተገኝቷል።

No comments:

Post a Comment