Monday, January 2, 2017

ለቡ አካባቢ ቁራጭ መሬት በ49 ሚሊዮን ብር ተሸጠ ፣ 25ኛው የሊዝ ጨረታ ዉጤት ይፋ ኾነ

  • ለአንድ ካሬ የመኖርያ ቦታ 50ሺህ ብር ቀርቧል
ዋዜማ ራዲዮ- ሦስት ክፍለ ከተሞችን ብቻ ባሳተፈው የ25ኛው ዙር የሊዝ ገበያ በከተማዋ ድንበር ላይ ያሉ ቦታዎች ባልተለመደ ኹኔታ ከፍ ያለ ዋጋ ቀርቦባቸዋል፡፡ ኮልፌ ቀራንዮ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ለዚህ ዙር በድምሩ 107 ቦታዎችን ለቢዝነስ፣ ለመኖርያ ቤትና ለቅይጥ አገልግሎት አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ዉስጥ ንፋስ ስልክ ላፍቶ 20 ቦታዎች፣ ኮልፌ ቀራንዮ 11 ቦታዎችን ብቻ ለጨረታ ሲያቀርቡ አቃቂ ቃሊቲ 96 ቦታዎችን በሊዝ አገበያይቷል፡፡
ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሰፈሮች ለቡ ሰፈር በተደጋጋሚ ውድ ዋጋ የሚቀርብበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አካባቢው የብዙ ባለሐብቶች አይን የሚያርፍበትና ለኑሮ ምቹ የተባሉ ዘመናዊ ቤቶች የተገነቡበት ከመሆኑም ባሻገር የቫርኔሮ ዉድ አፓርትመንቶች የሚገኙበት ዘመናዊ ሰፈር ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የሚወጡ ቦታዎች ከፍ ያለ ዋጋ የሚስቡትም ለዚሁ ነው፡፡
ቀድሞ እንደተፈራውም በዚህ ዙር ለቡ አካባቢ አስደንጋጭ ዉጤት ተመዝግቦበታል፡፡  በኮድ 12309 አገልግሎቱ ለመኖርያ ቤት የኾነ፣ ስፋቱ 208 ካሬ ቦታ፣ አቶ አብረሀም የተባሉ ግለሰብ ለአንድ ካሬ 50ሺ 250 ብር በመስጠት ይህን ጠባብ መሬት በ10 ሚሊዮን 452ሺ ብር የግላቸው አድርገውታል፡፡ በዚህ አካባቢ የቀረቡ ሌሎች አምስት ቦታዎችም በተመሳሳይ ከፍ ያለ ዋጋ የቀረበባቸው ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment