Tuesday, January 3, 2017

ለማንነታችን መከታ ያልሆነን፣ ለመጠቃታችን ምክንያት እየሆነ ነው! – ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት


ዛሬ በኢትዮጵያ ምድር ዘረኛው የትግሬ ወያኔ አገዛዝ በሕዝባችን ላይ፣ በተለይም በዐማራው ነገድ ላይ የሚፈጽመው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በ«አርበኞች ግንቦት 7»  እያመካኘ ነው።  ለዚህም ምክንያት የሆነው አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ በሚቆጣጠረው የብዙኃን መገናኛ ያላደረገውን አደረኩ፣ ያላዘመተውን ወታደር አዘመትኩ፣ «የክተት አዋጁ ፊሽካ ተነፋ»፣ በሁሉም ሕዝባዊ እንቢተኝነት እንቅስቃሴዎች እኔ አለሁበት፣ የምመራው እኔ ነኝ፣ የሚለው ወሬ ቀድሞ መነዛቱ ነው።  ወሬው በትንሽ ተግባር ቢደገፍ ኖሮ ባልከፋ። ክፋቱ ምንም ዓይነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሳይጀምር፣ ኤርትራ በረሃ ከትሟል የሚባለው ፋኖ፣ የተከዜን ወንዝ ሳይሻገር፣ የወያኔ አገዛዝ አንገሽግሾት ባመቸውና በመሰለው መንገድ ጥይት የተኮሰውን ሁሉ የእኔ ነው ማለቱ፣ «ለወያኔ ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ፣ ጂግራ ናት ይሏታል» እንዲል ሠፊ በር ከፍቶለታል። በመሆኑም በርካታ ዐማሮች  በአርበኞች ግንቦት 7 ስም ለሞት፣ ለእስር፣ ለእንግልትና ለስደት እንዲጋለጡ ምክንያት እየሆነ መምጣቱና ይህም  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ በመሄዱ፣ የዐማራው ነገድ ‘አርበኞች ግንቦት 7 ለማንነታችን መከታ ያልሆነ ድርጅት፣ ለጥቃታችን ምክንያት  ባይሆን ምናለበት?’ የሚል ጥያቄ እንዲያነሳ ግድ ብሎታል።
የኢትዮጵያን ፖለቲካና የወያኔን እንቅስቃሴ አዘውትረው የሚከታተሉ ሰዎች ሊያስታውሱት እንደሚችሉት፣በነጄኔራል ተፈራ ማሞ ተጠነሰሰ ለተባለው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራና ተፈራ ማሞን ጨምሮ ወይዘሮ እማዋይሽ ዓለሙ፣ ጀኔራል አሳምነው ጽጌ እና በርካታ ዐማራዎችን ለከፍተኛ ድብደባ፣ሥቃይና የዕድሜ ልክ እስራት መነሻ ምክንያቱ ግንቦት 7 መሆኑ ይታወቃል።  ሰሞኑን ደግሞ፣ ጉዳዩ «ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ» መሆኑ ቢታወቅም፣ የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄን፣ ያነሱ ወገኖች፣ ጥያቄአቸው ሕገመንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት፣ ልክ ለስልጢዎች፤ አገዎችና ቅማንቶቹ እንደተደረገው ሁሉ የእኛም የዐማራ ማንነታችን ይከበርልን ብለው በሕጋዊ መንገድ ጥያቄ ባቀረቡት የሕዝብ ተወካዮች ላይ፣ ወያኔ በአሸባሪነት ክስ የመሠረተባቸው አርበኞች ግንቦት 7  ወያኔን ለማስወገድ የትጥቅ ትግል ጀምሬአለሁ በማለት የሚያራምደው በተግባር ያልታየ ፕሮፓጋንዳ ምክንያት እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው።
ወያኔ የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ላቀረቡት ሕጋዊ የማንነት ጥያቄ ተገቢ መልስ ከመስጠት ፋንታ፣ የማንነት ጥያቄ አቅራቢዎቹን የዐማራውን ክልል መስተዳድር እንደምንም ባለመቁጠር፣ «ጌታዋና የተማመነች በግ ላቷን ውጭ ታሳድራለች» እንደሚሉት፣  ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት በተላኩ የትግሬ አፋኝ ቡድኖች የአስተባባሪ ኮሚቴውን ለማፈን ባደረጉት ሙከራ፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ የሆነው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ሕጋዊ ባልሆነ መገንገድ ሊያፍኑት ለመጡት አፋኞች እጄን አልሰጥም በማለቱ በተነሳው የአፍናለሁ አልታፈንም ግብግብ በተተኮሰ ጥይት የጎንደር ከተማን ሕዝብ የዘመናት የታመቀ ችግር መክደኛውን ገልብጦ እንዲወጣ ሰበብ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ሰበብ በመላ ጎንደር፣ ጎጃምና መሰል አካባቢዎች መዛመት ብርክ የሰደደበት ወያኔ፣ «ለብሔር/ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  ዕኩልነትና አንድነት ዋስተና የሆነ፣ በሕዝቡ ፍላጎት የጸደቀ» እያለ ጧት ማታ የሚፎገላበትን ሕገመንግሥት አግዶ፣ የዐማራውን ነገድ በጠራራ ፀሐይ የትግሬ ሚሊሻ እንደፈለገው የሚገድልበት፣ የሚደበድብበት፣ የሚያስርበት  ወታደራዊ አገዛዝ ሙሉ መብት የሚሰጥ አዋጅ አውጆ፣ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የሸዋና የወሎ የዐማራ ልጆችን በገፍ እየገደለና እያሰረ ይገኛል። በመሆኑም አዋጁ ከታወጀ እስከዛሬ ድረስ ከአንድ ሺ በላይ ዐማሮች ሲገደሉ፣ ከ30,000 (ሰላሳ ሺ) በላይ ወጣቶችና አዛውንቶች ታስረው የመከራን ጥዋ በመጎንጨት ላይ ይገኛሉ። ለዚህ ሁሉ ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው አርበኞች ግንቦት 7 ነው።
ለዚህ ድርጅት አመራሮችና በድርጅቱ ውስጥ አለን ለምትሉ ዐማሮች የሞረሽ ወገኔ ዐማራ ድርጅት ግልጽ መልዕክት ሊያስተላልፍ ይወዳል። የድርጅቱን እንቅስቃሴ ከጅምሩ እስካሁን ድረስ በሚገባ ተከታትለናል። በክትትላችን ያገኘነው ውጤት አርበኞች ግንቦት ሰባት በራሱ ማንነት ላይ ያልቆመ፣ ማንነቱን ከሌሎች ጋር በሚፈጥረው «ጥምረት፣ ውሕደት፣ ቅንጅት »ወዘተ ለማሳደግ የሚጥር፣ ተፈጠረ የሚባለው ጥምረት የት እንደደረሰ ሳያታወቅና የመጀመሪያው ጥምረት ፊርማ ሳይደርቅ፣ ሌሎች ጥምረቶች የሚፈሉበት መሆኑን ታዝበናል። ከሁሉም በላይ የሚገርመው ጥምረት የሚመሠርተው ዐማራውን በዐውራ ጠላትነት ከፈረጁ ብሔርተኛ ድርጅቶች ጋር መሆኑ እርሱም በተዘዋዋሪ መንገድ የዐማራው ጠላት መሆኑን እያሳየ መጥቷል። ለምሳሌ በከማል ከልጁ ከሚመራው ኦነግ ጋር፣ ዐማራውን በጠላትነት ከመፈረጅ አልፎ፣ የሽግግር መንግሥት ተብየውን ያረቀቀውንና ኢትዮጵያ ዛሬ ያለችበትን ሁኔታ ካመቻቹት፣ በአሰቦት ገዳም፣ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ ፤ በአርባጉጉ፣ ወተር፣ በወለጋ ወዘተ በገፍ ለተገደሉት ዐማሮች  አመራር የሰጡትን የነሌንጮ ለታ ቡድንና ከተገንጣዮቹ የሲዳማ ንቅናቄዎች ጋር የፈጠረው ሽርክና ፀረ-ዐማራ ብቻ ሳይሆን፣ ፀረ-ነባሯ ኢትዮጵያ መሆኑን በተግባሩ እያሳየ ነው። ከዚሁሉ አልፎ በአመራሩ አንድም የዐማራ ተወካይ በሌለበት ሁኔታ በወሳኝነት ዐማራው በሚኖርባቸው አካባቢዎች ከኤርትራ ተስፈንጥሬ አዲስ አበባ እገባለሁ የሚለው ሕልሙ ዐማራውን በአርበኞች ግንቦት 7 ስም ለእልቂት እየዳረገ ነው።  በመሆኑም ሁኔታውን  ቆም ብሎ በማሰብ ያለበትን ሁኔታ መርምሮ  ዐማራው በእርሱ ስበብ ተጠቂ ሳይሆን፣ መከታው የሚሆንበትን መንገድ ይከተል። ወይም አለኝ የሚለውን ኃይሉን አሰልፎ ወያኔን ይፋለም። ለዚህም የዐማራው ልጆች በአመራሩ ወሳኝ ቦታዎችን ይስጥ። ይህ ሲሆን እኛም  ወያኔን ለማስወገድ የምንችለውን ለማድረግ እንጥራለን። ይህ ካልሆነ፣ አርበኞች ግንቦት 7 መከታችን ካልሆነ መጠቂያችን እንዲሆን የማንፈቅድ መሆኑ እንዲታወቅ እንሻለን።
ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!

No comments:

Post a Comment