Monday, January 30, 2017

የዶናልድ ትራምፕ ትርጉም፣ በኢትዮጵያና በኬንያ! ዮሃንስ ሰ.



• ድሮ… አሜሪካን እየተሳደብንም ቢሆን፣ እርዳታ አይቀርብንም ነበር
• (“የአሜሪካ ወዳጅነት መሆን ሌላ! የአሜሪካ እርዳታ መቀበል ሌላ!”)
• ዘንድሮ… የእርዳታ ገንዘብ የዶናልድ ትራምፕ ኢላማ ውስጥ ገብቷል።
• “ነገር ለሚፈልጉን፣ እርዳታ አንሰጥም”… እያሉ ነው – ሰውዬው።
“ሌሎች አገሮች ላይ፣ ጫና አናደርግም። እንዲህ አድርጉ… እንዲያ ሁኑ አንልም” የሚለው የዶናልድ ትራምፕ ንግግር፣ ለብዙ የአፍሪካ መንግስታት፣ በጣም አስደሳች ሊሆን ይችላል። ይህም ብቻ አይደለም። ሃሙስ እለት ለጉብኝት አሜሪካ የገቡት፣ የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴረሳ ሜይ፣ ተመሳሳይ ሃሳብ ሰንዝረዋል። “ሌሎች አገሮችን በኛ አምሳል ለመቅረፅ ጣልቃ መግባት… ከእንግዲህ አይደገምም” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሯ። “ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። ጊዜው አልፎበታል” የሚል መልእክት ነው ያስተላለፉት።
የአፍሪካ መንግስታት፣ “ጣልቃ ገብነትም ሆነ ጫና፣ ከእንግዲህ አይኖርም” የሚል ንግግር ሲሰሙ፣ አብዛኞቹ እንደሚደሰቱ ባያጠራጥርም፤ ሌላ ጣጣ አለባቸው። የእርዳታ ገንዘብም፣ እንደ ድሮው እንደዘበት አንመድብም ብለዋል ትራምፕ። ይሄ፣ ለብዙ የአፍሪካ መንግስታት፣ በጣም አሳሳቢ ይሆንባቸዋል – ለኢትዮጵያም ጭምር።
ለበርካታ ተከታታይ ዓመታት፣ ከአሜሪካ መንግስት፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እርዳታ በማግኘት ከሚጠቀሱ ቀዳሚ 10 አገራት መካከል፣ ኢትዮጵያ አንዷ ናት። አምና ደግሞ፣ አፍጋኒስታንን በመከተል፣ በ2ኛ ደረጃ የምትጠቀስ፣ ዋና እርዳታ ተቀባይ ሆናለች። 770 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ደርሷታል (ከ17 ቢሊዮን ብር ገደማ)።
ለነገሩ ለኬንያና ለደቡብ ሱዳን፣ ለናይጄሪያና ለላይቤሪያ፣… ከአፍሪካ ውጭ ደግሞ ለዮርዳኖስና ለፓኪስታን የተለገሰው እርዳታም ቀላል አይደለም (እያንዳንዳቸው ከ4 እስከ 5 መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ እርዳታ ከአሜሪካ ተቀብለዋል።)
አስገራሚው ነገር ይሄ አይደለም። ምክንያቱም፣ የአሜሪካ እርዳታ፣ ከአመት አመት የማይቋረጥ ከመሆኑ የተነሳ፣ እንደ መደበኛ የገቢ ምንጭ የሚታይ ሆኗል። በቃ፣ ከአሜሪካ መንግስት እርዳታ መቀበል፣ በየአመቱ የተለመደ አይቀሬ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ኢትዮጵያ፣ ባለፉት ሰባት ተከታታይ ዓመታት፣ ሳንቲም አልጎደለባትም። ከአሜሪካ የሚመደብላት የእርዳታ ገንዘብ፣ ከ650 ሚሊዮን ዶላር በታች ሆኖባት አያውቅም። በሰባት ዓመታት ውስጥ 5 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ አፍሳለች – ከአሜሪካ። እነ ዮርዳኖስና ፓኪስታን፣ ኬንያና ናይጄሪያም… እርዳታው ተቋርጦባቸው አያውቅም።
አዎ… እርዳታ እንደ መደበኛ የገቢ ምንጭ መታየቱ፣… “የሆነ የሚገርም ነገር” እንዳለው አልክድም። ግን፣ የተለመደ ጉዳይ ስለሆነ፣… እንደ ጉድ አይወራም።
አስገራሚው ነገር ሌላ ነው። ዋናዎቹ እርዳታ ተቀባይ አገራት፣ በአደባባይ… በዓለም መድረክ… የአሜሪካ “ወዳጆች” አለመምሰላቸው ነው አስገራሚው ነገር። በደፈናው፣ “የአሜሪካ አድናቂዎች አይደሉም” ብዬ ጥቅል የስሜት ድምዳሜ እየተናገርኩ እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ። በቁጥር የተሰራ መረጃ አይቼ ነው የማቀርብላችሁ – በስሜት የተመራ ሳይሆን በስሌት የተቀመረ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ።
ባለፈው ሐምሌ ወር፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፣ በ72 ገፅ ሰንዶ ያቀረበው ሪፖርት፣ ምን ላይ ያተኮረ መሰላችሁ? በተባበሩት መንግስታት ጉባኤዎች ላይ፣ ከየአገሩ የመጡ የመንግስት ተወካዮች፣ ምን ምን ውሳኔዎችን እንደደገፉና እንደተቃወሙ ነው፣ ሪፖርቱ የሚዘረዝረው።
ሪፖርቱ እንደገለፀው፣ የዩኤን ጠቅላላ ጉባኤ፣ በአንድ አመት ውስጥ፣  79 ውሳኔዎችን አስተናግዷል። እያንዳንዱ ውሳኔ የሚተላለፈውም፣… የሁሉም አገራት ተወካዮች በሚሰጡት የድጋፍና የተቃውሞ ድምፅ ነው። እንግዲህ፣… ወዳጅና ጠላት የሚለየው እዚህ ላይ ነው።
ወዳጅ እና “ወዳጅ መሳይ”
ያው… እንደ ውሳኔው አይነት፣ የአሜሪካ መንግስት፣ አቋሙን ይገልፃል። በተቃውሞ ውሳኔውን ውድቅ ለማድረግ፣ ወይም ደግሞ ውሳኔውን ለማፅደቅ የድጋፍ ድምፅ ይሰጣል። ዋናዎቹ የአሜሪካ ወዳጆች፣ ብዙውን ጊዜ፣ የአሜሪካ አይነት ተመሳሳይ አቋም በመያዝ፣ ድምፃቸውን ይሰጣሉ። ድሮስ? ወዳጅነታቸው የተመሰረተው፣ ተቀራራቢ አስተሳሰብና አቋም በመያዛቸው አይደል? እናም በዩኤን መድረክ ላይ፣… ለምሳሌ… የካናዳ መንግስት አቋም ብዙውን ጊዜ ከአሜሪካ መንግስት ጋር ተመሳሳይ ነው። በቁጥር እንግለፀው።
የካናዳ መንግስት፣ በ65 ውሳኔዎች ላይ፣ ከአሜሪካ አቋሞች ጎን ቆሟል። በ5 ውሳኔዎች ላይ ግን፣ ተቃራኒ አቋም ይዟል። በአጭሩ፣ የካናዳ መንግስት፣ 90% ከአሜሪካ ጎን የሚቆም አስተማማኝ ወዳጅ ነው ማለት ይቻላል። የሚያለያይ ነገር የላቸውም ማለት አይደለም። አለ። ግን፣ ከሚያቃርን ይልቅ የሚያቀራርባቸው ነገር ይበልጣል። ወዳጅነታቸው የሚለካውም በዚሁ የሃሳብና የአቋም ቅርርባቸው ነው።
አውስትራሊያ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይም፣ ብዙውን ጊዜ ከአሜሪካ ጎን ነው የሚቆሙት (በ80% ውሳኔዎች ላይ)። በሌላ አነጋገር፣ ከሚያለያያቸው ነገር ይልቅ፣ የሚያስማማቸው ነገር ይበዛል – አራት እጥፍ ያህል ነው። እነ ሃንጋሪና ፖላንድ ደግሞ፣ ከ70% በላይ ከአሜሪካ ጎን ይቆማሉ። ከካናዳና ከእንግሊዝ ጀምሮ፣ እነዚህን የመሳሰሉ አገራት  ናቸው ዋናዎቹ የአሜሪካ ወዳጆች። ግን ብዙ አይደሉም።
አምና፣ በዩኤን መድረክ፣ ከ50% በላይ በሆኑ ጉዳዮች ላይ፣ የአሜሪካ ጎን የቆሙ አገራት፣ 54 ብቻ ናቸው።
ከእነዚህ ቀጥላ የተጠቀሰችው አገር፣ ሩዋንዳ ናት። ሩዋንዳ፣ በ21 ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ጎን ቆማለች። በ23 ጉዳዮች ላይ ደግሞ፣ ከአሜሪካ ጋር የሚቃረን ሃሳብ በመያዝ ድምፅ ሰጥታለች። ለአሜሪካ፣ የሩዋንዳ ወዳጅነት፣ “ግማሽ ግማሽ ነው” ልንለው እንችላለን።
ሌሎቹ 137 አገራትስ? ባላንጣ?
አብዛኞቹ የአለማችን አገራት፣ ብዙውን ጊዜ የአሜሪካ መንግስትን አቋም በመቃወም፣ ተቃራኒ ድምፅ የሚሰጡ አገራት ናቸው። ታዲያ፣ በሁሉም ነገር ላይ፣ የአሜሪካ ተቃራኒ ይሆናሉ ማለት አይደለም። ለምሳሌ የራሺያን አቋም መጥቀስ ይቻላል።
በ27 ጉዳዮች ላይ፣ የራሺያ አቋም፣ ከአሜሪካ አቋም ጋር አንድ አይነት ነበር። በ38 ጉዳዮች ላይ ግን፣ የራሺያ አቋም፣ ከአሜሪካ አቋም ጋር ይቃረናል። ከሚያስማማቸው ነገር ይልቅ፣ የሚያለያያቸው ነገር በዛ ማለት ነው። ነገር ግን፣ “ራሺያ የአሜሪካ ጠላት ናት” ብሎ ለመፈረጅ ይከብዳል። ለምን በሉ?
የአሜሪካ አቋምን በመቃወም፣ ሌሎች ብዙ አገራት፣ ከራሺያ የባሱ ናቸው። እንዴት ብትሉ፣ ከራሺያ በባሰ ሁኔታ፣ አሜሪካን የሚቃወሙ አገራት፣ 125 ናቸው።
ለምሳሌ፣ እዚያው አሜሪካ አጠገብ ያለችውን ሜክሲኮ መጥቀስ ይቻላል። በ29 ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ጋር በመስማማት ድምፅ ብትሰጥም፣ በ45 ጉዳዮች ላይ፣ ከአሜሪካ ጋር የሚቃረን አቋም ይዛለች። እንዲያም ሆኖ፣ ሜክሲኮ፣ በየአመቱ ከአሜሪካ፣ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ ታገኛለች። መች ይሄ ብቻ!
ኢትዮጵያና ኬንያ
በዓመት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ ከአሜሪካ የሚመደብለት የኬንያ መንግስትን ተመልከቱ። የኬንያ መንግስት በ23 ጉዳዮች ላይ፣ የአሜሪካ አቋምን የደገፈ ቢሆንም፣ በ48 ጉዳዮች ላይ የአሜሪካ አቋምን ሲቃወም ታይቷል። ከሚያስማማ ነገር ይልቅ፣ የሚያቃርን ነገራቸው ይበልጣል – ከእጥፍ በላይ።
እንግዲህ ይታያችሁ። ከአሜሪካ፣ እጅግ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እርዳታ በማግኘት በኩል፣ አምናና ካቻምና በአራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች አገር ናት – ኬንያ። በሰባት አመታት ውስጥ እንደ ኢትዮጵያ፣ 5 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ እርዳታ ከአሜሪካ አግኝታለች።
እንዲያም ሆኖ፣ በአለማቀፉ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ መድረክ፣ አሜሪካን ለመደገፍ ሳይሆን፣ አሜሪካን ለመቃወም የምትሰጠው ድምፅ ይበልጣል – ለዚያውም እጥፍ ያህል።
የኢትዮጵያ አሰላለፍስ እንዴት ነው?
ያው እንደኬንያ ነው። በ22 ጉዳዮች ላይ፣ የኢትዮጵያ አቋም፣ ከአሜሪካ ጋር የሚስማማ ነበር። በ48 ጉዳዮች ላይ ግን፣ ከአሜሪካ ጋር የሚቃረን አቋም!
ሌሎቹ የዘወትር እርዳታ ተቀባዮች፣… እነኡጋንዳ፣ ባንግላዲሽ፣ ኢራቅ፣ ናይጄሪያ፣ የመሳሰሉ አገራት ባህርይም፣ ከኬንያና ከኢትዮጵያ ጋር ይመሳሰላል። ይሄ አያስገርምም? በየዓመቱ ከአሜሪካ ብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላር እርዳታ የሚቀበሉ ቢሆኑም፤ በየአመቱ የሚይዙት አቋም ግን፣ የአሜሪካ ዋና ባላንጣ ያስመስላቸዋል።
ምናለፋችሁ!… የነ ኢትዮጵያና የነኬንያ አቋም፣ በአብዛኛው ከለየላቸው የአሜሪካ ባላንጣዎች ጋር… ማለትም ከቬኔዝዌላና ከኩባ፣ ከዚምባብዌና ከቻይና ጋር በጣም ይቀራረባል። ለምሳሌ፣ ኩባ፣ በ18 ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ጋር የሚስማማ አቋም ይዛ ነው፣ በ52 ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ጋር የሚቃረን አቋም ያስተጋባችው። ያው፣ ቁጥሮቹን ስናያቸው… ከኢትዮጵያና ከኬንያ ቁጥሮች ጋር ተቀራራቢ ናቸው። ይሄ ተገቢ አይደለም።
በአንድ ጎን እርዳታ እየተቀበሉ፣ በሌላ በኩሉ ደግሞ የጎን ውጋት መሆን… በቃ አያምርም። እነ ኢትዮጵያና እነ ኬንያ፣ በጭራሽ… በጭራሽ፣ እንደ ኩባና እንደ ቬኔዝዌላ፣ በዩኤን መድረክ፣ የአሜሪካ ባላንጣ መሆን አልነበረባቸውም። አዎ፣ እንዲያ “መሆን አልነበረባቸውም”።
ካሁን በኋላ ግን፣ እንደ ድሮው፣ መሆን የሚችሉ አይመስልም።
ዶናልድ ትራምፕ፣ የድሮውን የእርዳታ አመዳደብ ለመቀየር እንዳቀዱ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል። እንዴት? “የአሜሪካ አቋምን አዘውትረው የሚቃወሙ መንግስታት በርካታ ናቸው፤ በየአመቱ የምንሰጣቸውን እርዳታ መቀነስ አለብን” የሚል ነው የትራምፕ ሃሳብ።

No comments:

Post a Comment