Saturday, January 28, 2017

ኢሳት ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦን ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል! -አቻምየለህ ታምሩ


      


ኢሳት ነፃ ሜዲያ ነኝ የሚል ከሆነ ስራው ሀሳብ አለኝ የሚልን ሁሉ ሀሳቡን እንዲያንሸራሽር መፍቀድና መድረክ ማመቻቸት እንጂ ያለ ስራው እየገባ የማባበልና ባለስፈላጊ ሁኔታ በመግለጫ ስም ማስተባበያ አይሉት ይቅርታ ማቅረብ አይደለም።
ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ
ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ እንደ ታሪክ ሊቅነታቸው በታሪክ «የተመዘገቡ ናቸው» ያሏቸውን ማስረጃዎች እያወሱ ለተጠየቁት ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል። የኢሳት ሚና የፕሮፌሰሩን መልስ ለመድረክ ማብቃት ብቻ ነው። የፕሮፌሰሩን ንግግር በሚመለከት መግለጫ ማውጣት የኢሳት ስራ አይደለም። ፕሮፌሰሩ በንግግራቸውና በሰጡት መልስ የሚቀየምና የማይስማማ ሊኖር ይችላል። እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር «የሚዲያው» ኢሳት መፍትሔ መሆን ያለበት ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ካቀረቡት የተለየ ሞጋች ኃሳብ ላለው የታሪክ ሊቅ መድረክ ማመቻቸትና ከተቻለም ከፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ ጋር ማከራከር እንጂ በፕሮፌሰር ኃይሌ አቀራረብ ላይ ተመስርቶ በመግለጫ ስም ማስተባበያ አይሉት የይቅርታ አዋጅ ማንበብ አይደለም።
የኢሳት የዛሬው ያልተገባ መግለጫ የአካዳሚክ ነጻነቱን ተጠቅሞ በሚያስተምር የታሪክ ምሁር ላይ የተወሰደ አጸፋዊ የአፈና እርምጃ ነው። ይህ ያልተገባ መግለጫ ፕሮፌሰሩንም መናቅ ነው።
የታሪክ ምሑር በታሪክ የተመዘገቡለትን ቃላትን እየጠቀሰ እንዳያስተምር በሚዴያ በታገዘ ዘመቻ አበሳውን የሚያይ ከሆነ ምንም ነገር ማስተማርና መናገር አይችልም ማለት ነው። የታሪክ ምሑሩ ተመዝግበው ባገኟቸው ስሞች ዛሬ መጠራት አንፈልግም ያለን አካል ያለ ፍላጎቱ መጥራት ትክክል አይደለም። ዛሬ በዚያ ስም ቢጠራ ያቃቅራል። ተቃቅሮ ደግሞ አብሮ መኖር አይቻልም። የታሪክ ምሁር ግን ስራው የተመዘገቡለትን ቃላት ሁሉ ማስተማር ነው።
ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ እንደ ታሪክ አዋቂነታቸው የተመዘገቡላቸውን ቃላት በመናገራቸው ኢሳት «አይነኬዎቼ» ተቀየሙ ብሎ የሚያስብላቸው ከሆነና ይቅርታ መጠየቅ ካሰኘው ራሱን ተጠያቂ ማድረግ ይችላል እንጂ በሰው ሀሳብና አቀራረብ አስተያየትም ሆነ መግለጫ ማቅረብ የእርጎ ዝንብ መሆን ነው።
ስለዚህ ኢሳት በፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ የአከዳሚክ ነጻነት ላይ ስላደረሰው ጉዳት፤ በፕሮፌሰሩ ክብር ላይ ስለፈጸመው በደል፤ በሞያ መታመናቸውን [integrity] ስለመጋፋቱ፣ ስላካሄደባቸው የመብት ገፈፋና ሀሳባቸውን ባለማክበር በሞያዊ ልቀታቸው ላይ ስላሳየው ንቀት ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦን በሌላ መግለጫ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል።

No comments:

Post a Comment