Tuesday, January 31, 2017

በኔ እምነት በማህበራዊ ሜድያው እጅግ ተሸንፈናል። Wondemagegnehu Addis


ኢትዮጲያ እንድትበታተን እንቅልፍ አጥተው ከሚያድሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ምን እንጠብቅ እንደነበር አልገባኝም? አንዳች በጎ ነገር? ምን እንደምንጠብቅ ባለማወቃችን ሽንፈታችን በመደበኛነት እየታየ መጥቷል። እኛ ሳናውቃቸው እነሱ ግን ልባችንን በርብረው ስላወቁት አጠቃላይ አካሄዳችንን ተቆጣጥረውታል።
አንድ ሁለት አረረፍተ ነገር ወርወር ያደርጉና 1ወር ያንጫጩናል። እኛ ለነሱ መልስ ስንሰጥ በመንጋ ተከታዮቻቸው እንወረራለን። አንዳንዶቻችን አፀፋችንን ተመጣጣኝ ያደረግን እየመሰለን እነሱ በሄዱበት መንገድ ምላሽ ስንሰጥ ወጥመዳቸው ውስጥ እንገባላቸዋለን። እነሱም ሲጀመርም ይሄንን ትርፍ አስልተው ነው የሚያደርጉትን የሚያደርጉት። እሰጥ አገባው በርካታ ቁስሎችን በማህበረሰቦቻችን መሀል ፈጥሮ ያልፋል።
ትንሽ አረፍ ስንል ሌላው ደሞ በሆነች ሀረግ ጠቅ ያደርገንና ዞር ይላል። እኛም ወደተለመደው ተግባራችን እንመለሳለን። ለኛ የቤት ስራ ሰጥቶን እሱ ስራውን ይሰራል።
እስኪ እናስተውል ከንዲህ አይነት ድግግሞሽ እስካሁን ያተረፍነው ነገር ምንድነው? ድንገት ብቅ እያሉ እንደፈለጋቸው ሲያንጋጉን፣ ወዲያና ወዲህ ሲያመላልሱን እንዴት መንቃት ተሳነን? ሁሌ መከላከል አይበቃንም ወይ?ከነሱ ምንም አይነት ሀላፊነት የተሞላው ድርጊት መጠበቅ የለብንም። ከሚነሳው አቧራ እነሱ የሚያጋብሱት ፋይዳ እንጂ የሚያጎሉት ምንም የለም። እኛ ግን ብዙ እናጎላለን። ጠላትን ማበሳጨትና ማሳሳት የሚለውን ስሌት በሚገባ እየተገበሩት ነው። አሁን ለኛ የሚጠቅመን ትግሉ ላይ ማተኮር ብቻ ነው። እዚያ ላይ ጊዜያችንን እና አቅማችንን ልናውል ይገባል። ወቅታዊ ከሆኑት እንኩዋን የቅማንት ፣ የቴድሮው አድሀኖም አረ መአት ጉዳዮች ጉዳዮች አሉን።

በኢትዮጲያ አንድነት እናምናለን የምንል ወገኖች መጀመሪያ በመሀከላችን ያለውን ቀዳዳ እንድፈን። ያልሰራናቸው በርካታ የቤት ስራዎች አሉን። እንደ ኢትዮጲያዊ ጠንክረን ስንወጣና በልዩነቶቻችን ተከባብረን መታየት ስንችል ትርጉም ያለው ተፅእኖ ልንፈጥር እንችላለን። በቀላሉ የማንደፈርና የማንገሰስ እንሆናለን። እንከበራለን እንታፈራለንም። ያን ጊዜ የምንለው ይሰማል። አጀንዳ መስጠት የኛ ተራ ይሆናል።
ስለዚህ ትኩረት የምንሰጣቸውን ጉዳዮች እንለይ። አላስፈላጊ በሆነ ጉዳይ ተጠምደን አስፈላጊውን ጉዳይ እያሳደርን ለአፍራሾች ኢላማ አንመቻች።

No comments:

Post a Comment